1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በታሪኳ ለመጀመርያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ልታደርግ ነው

ቅዳሜ፣ የካቲት 13 2013

በኬንያ የባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች  ሰሞኑን ሰብሰብ ብለው  የአንበጣው መንጋ ያደረሰባቸውን ጉዳት ለመገምገም ወደ ማሳዎቻቸው ሄደው ነበር። የሆነው እና ያገኙት ነገር አስደንግጧቸዋል። የአንበጣው መንጋ በጥቂት ቀናት ብቻ ማሳዎቻቸውን ባዶ አድርጎ አገኙ።

https://p.dw.com/p/3pdhF
Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ

ኬንያ በሌላ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ስጋት ተይዛለች
የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችን በተለይ ነጥሎ በጥፋት በትሩ የመታው የበረሃ አንበጣ መንጋ አሁንም ድረስ አልጠፋም። እንዲያውም ቦታ እና ጊዜ እየቀያየረ በመከሰት የኮሮና ወረርሽኝን ጨምሮ በድርቅ እና ሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ሲጠቃ የነበረውን አካባቢ አሁንም ሌላ ፈተና ሌላ ስጋት ይዞ ስለመምጣቱ ምልክት አሳይቷል። ከሰሞኑ የኬንያ እና የኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው መንጋው ሌላ ጥፋት ይዞ እንዳይመጣ ከአሁኑ ስጋት አጭሯል። 
በኬንያ የባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች  ሰሞኑን ሰብሰብ ብለው  የአንበጣው መንጋ ያደረሰባቸውን ጉዳት ለመገምገም ወደ ማሳዎቻቸው ሄደው ነበር። የሆነው እና ያገኙት ነገር አስደንግጧቸዋል። የአንበጣው መንጋ በጥቂት ቀናት ብቻ ማሳዎቻቸውን ባዶ አድርጎ አገኙ። የአንበጣው መንጋ ጥቃት ከገመቱት እና ካሰቡት በላይ እጅጉን አስከፊ እንደነበር ጆህን ሙዞኪ ሲናገሩ   
«በወረራው እጅጉን  ተደናግጠናል። አንበጣዎች ከየትኛውም ቦታ መጥተው በእርሻችን ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ካሰብነው እና ከገመትነው የበለጠ ብዙ ናቸው። የበቆሎ ሰብል በልተው የአናናስ ተክል እና የማንጎ ዛፎችን ያጠፋሉ።»

Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የኬንያ የግብርና ሚኒስትር በታኅሣስ ወር በሀገሪቱ ቴሌቪዥን እንዳስጠነቀቀው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኙ በድጋሚ ሊከሰት እንደሚችል ነው። የግብርና ሚንስትሩ ፒተር ሙኒያ እንደሚሉት በአጎራባች ሃገራት በርካታ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ ሊፈለፈል እንደሚችል ስለሚገመት ወደ ኬንያ የመግባት ዕድሉ ሰፊ እንደነበር አስቀድሞ ይታወቅ ነበር።
«በእነዚህ ጎረቤት አገሮች ውስጥ በርካታ የአንበጣ መንጋዎች ሲፈለፈሉ እንደነበር መረጃው አለን።   በዚህ ምክንያት ፣ በታኅሣስ ወር ላይ ንፋሱ ወደ  ደቡብ አቅጣጫ መንፈስ ሲጀምር ሁለተኛ የወረራ ማዕበል ሊመታን እንደሚችል አስቀድመን ተንብየናል። ይህንኑ ተከትሎ በተለይ አሁን ዝናቡ ገና መጣል በመጀመሩ እና ቡቃያውም ገና በለጋነት ደረጃ ላይ በመሆኑ የወረርሽኙ ጥቃት እንዳይከፋ ያሰጋል።» 
እንደተሰጋው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኙ ተመልሶ መቷል። ኃይለኛ ነፋስ ከጎረቤት ሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ መንፈስ ጀምሯል።  ኬንያውያን ቀጣዩ ማዕበል ሌላ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል በስጋት ተይዘዋል። በሌላ በኩል የአንበጣው መንጋ ብዙም የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እንዳልሠራች ከሚነገርላት የመን ተነስተው በአረቢያ ባሕረ ገብ መሬት አቋርጠው ወደ ምሥራቃዊ የአፍሪካ ክፍል በተለይም ወደ ኬንያ አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነ ተመላክቷል።  የኬንያ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች  የግብርና ሥራዎች ኃላፊ ፍሬደሪክ ካይንግን መንጋው ወደ ኬንያ የባሕር ዳርቻዎች ሲደርሱ መድኃኒት በመርጨት የመከላከያ ሥራዎችን በመስራት እንደሚደግፉ ይናገራሉ። 
«ይህንን ማጽዳት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ብለን በመረጥናቸው  ሁለት ዘዴዎች ያሉንን የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች በመጠቀም   የኬሚካል ውህዶችን አሊያም ደረጃውን የጠበቀ ፀረ-ተባዮች ልንጠቀም እንችላለን ፡፡»
በ ባለፈው የጎርጎርዮሳዊ 2020 መጀመሪያ ላይ ግዙፍ የአንበጣ መንጋዎች ወደ ኬንያ ሲያቀኑ ለበርካታ በጎ ፈቃደኛ  ሠራተኞች በምድር ላይ ፀረ-ተባዮችን በመጠቀም እንዲከላከሉ ለማሰማራት ስልጠና ተሰጥቷቸው ነበር።. ነገር ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀረና የጸረ ነፍሳት ኬሚካሉ ከአንበጣው ውጭ ሌሎች ጉዳት የማያደርሱ ነፍሳትንም እንደሚገድል ታወቀ። እና አንዳንድ የአከባቢው ሰዎች በተፈጠረው ችግር ማጉረምረማቸው አልቀረም።  ነገር ግን በኬንያ ግብርና ሚኒስቴር የተባይ ማጥፊያ ባለሙያ የሆኑት እስታንሊ ኪፕኮች የኬሚካሉ ርጭት በአጠቃላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ ስለሚያመዝን  ያንኑ መንገድ መምረጡ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ።  
«ተባዩ በእውነቱ በጣም አጥፊ ተባይ ነው ፡፡ የሰውነቱን ክብደት ያህል ሲመገብ  እናያለን ፡፡  ስለ አንድ ተባይ ወደ 20 ግራም እየተናገርን ነው ፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ መንጋ ከ 30 እስከ 40 ሚሊዮን አካባቢ ይገመታል፤ እንግዲህ ጥፋቱ ምንያህል እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡  ለእንስሳቱ እና ለአርብቶ አደሩ ምግብነት ሊውል የሚችል በበርካታ ቶኖች የሚቆጠር ዕጽዋት እና ሰብሎችን ያወድማል ማለት ነው።» 
ያለፈው ጎርጎርሳዊው 2020 በምሥራቅ አፍሪካ የነበረው  የአየር ሁኔታ ለበረሃ አንበጣው  እጅጉን  ተስማሚ ነበር - ምክንያቱ ደግሞ የህንድ ውቅያኖስ ባልተለመደ ሁኔታ ሞቃታማ መሆኑ ፤ ያንን ተከትሎም ከባድ ዝናብን ማስከተሉ አንበጣው በእርጥበታማው አፈር ውስጥ እንቁላሉን ለመጣል አመቺ ሁኔታን በመፍጠሩ ነበር።  በወቅቱ ኬንያን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመንጋው ክፉኛ ተመተዋል። 

Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft | Bekämpfung mit Pestiziden
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images
Kenia Meru | Heuschreckenplage & Landwirtschaft | Bekämpfung mit Pestiziden
ምስል Yasuyyoshi Chiba/AFP/Getty Images

 

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በታሪኳ ለመጀመርያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ መሰናዳቷን መረጃዎች እያመለከቱ ነው።
በአካባቢው  ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንቶች ለሥልጣን ዘመናቸው የተቀመጡ የጊዜ ገደቦችን እንዳሻቸው በሚያደርጉበት  ክልል ውስጥ የኒጀሩ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ማሃማዱ ኢሱፉ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ መዘጋጀታቸው ሲሰማ በኒጀር አዲስ ምዕራፍ ሊከፈት ስለመቃረቡ በስፋት እየተነገረ ነው። የፕሬዚዳንቱ ተግባር ምናልባትም ለአዲሱ ተመራጭ ከባድ ሥራ ጥሎ ሳያልፍ እንደማይቀር ከወዲሁ ተገምቷል። 
ኒጀር ባሳለፍነው የታኅሣስ ወር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አካሂዳ የነበረ ቢሆንም ተወዳዳሪዎች አንዳቸውም አብላጫ ድምጽ ሳያገኙ በመቅረታቸው ለሌላ ሁለተኛ ምርጫ እንዲዘጋጁ አስገድዷቸው ነበር። እነሆ ግዜው ደረሰና  ነገ እሁድ የሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ አዲሱን የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ማንነት ይለያል ተብሎ ይጠበቃል።
በኒጀር የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት ጨምሮ በሀገር ውስጥ ቁልፍ የሥልጣን እርከኖች ሲያገለግሉ እንደነበር የተነገረላቸው እና ገዢው የሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲን ወክለው በቀረቡት መሐመድ ባዙም እና በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሀማኔ ኦስማን መካከል የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ውድድር ካሁኑ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። መሐመድ ባዙም ከገዢው ፓርቲ ተመርጠው ለውድድሩ ሲቀርቡ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ማሃማዱ የጀመሯቸውን ተግባራት ያስቀጥላሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸው ነው። ነገር ግን በመጀመርያው ውድድር እንደታየው ሁሉ ከተወዳዳሪያቸው ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል፤ ተብሏል። እጎአ በ1996 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን ተነጥቀው የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚደንት መሐማኔ ኦስማኔ በዚህ ምርጫ እኩል የማሸነፍ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። ዕጩ ተወዳዳሪው ቁልፍ የተባሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ድጋፍ ስለማግኘታቸውም ተዘግቧል።
የኒጀራውያን የነገውን ፕሬዚዳንታዊ ውድድር የምርጫ ሂደት እንዲሁም በድህረ የምርጫ ቀን የሚታዩ ሁኔታዎች ሰላማዊነታቸውን ያስጠበቁ መሆን አለመሆናቸው ምናልባትም ሀገሪቱ ያለፉትን አስር ዓመታት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የተጓዘችበትን ርቀት ሊወስን ይችላል። ኒጀር የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲኢዊ ሥርዓት የ10 ዓመታት ተሞክሮ ብቻ ነው ያላት። አሁን ሥልጣን ላይ የሚገኙት እና ከቀናት በኋላ በሌላ አዲስ ፕሬዚዳንት መተካታቸው የሚረጋገጠው ፕሬዚዳንት መሐመዱ ኢሱፉ ሁለት የአምስት ዓመት የሥልጣን ጊዜዎችን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸው እየተነገረላቸው ነው። ምናልባትም የሥልጣን ሽግግሩ በተሳካ ሁኔታ ከተከናወነ ሀገሪቱ ከፈረንሳይ ነጻነቷን ከተቀዳጀች እጎአ ከ1960 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚደረግ የሥልጣን ርክክብ ሆኖ በታሪክ ይመዘገብላታል። ታዋቂው የሕገ-መንሥት ጉዳዮች ጠበቃ እና የፖለቲካ ተንታኝ አማዱ ቦባከር ሀሰኔ እንደሚሉት የሥልጣን ሽግግሩ ዕለት ለኒጀራውያን ልዩ ትርጉም አለው።
 «ኒጀራውያን ከእነርሱ አልፎ የተቀረው ዓለም ስማቸውን በበጎ የሚያነሳበትን እና ታሪካዊውን ፕሬዚዳናታዊ የሥልጣን ሽግግር ሲደረግ ለማየት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።»
አማዱ ቦባከር ኒጀር የጀመረችው የዲሞክራሲ መንገድ እንዲህ ብልጭ ብሎ ድርግም እንደሚል ዓይነት ሳይሆን መሰረት ኖሮ ወደ ፊት የሚራመድ እንዲሆን ሊጠበቅ የሚገባው እንደሆነ ያሳስባሉ።
«ይህንን  በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የማሸጋገር ስኬት በማጠናከር የፖለቲካ እና ተቋማዊ የመረጋጋት ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ነው ፡፡»
በኒጀር ድህረ ቅኝ ግዛት ታሪክ ማሃማዱ ኢሱፉ እስከተመረጡበት ጊዜ ድረስ መሪዎች ሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎችን ይተኩ የነበሩት አንድም በመፈንቅለ መንግሥት አሊያም በኃይል ብቻ ነበር። ይህ እስካልተፈጠረ ድረስ መሪዎች ልክ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት እንደሚደረገው ሁሉ መቀመጫቸውን አደላድለው በኃይል መቆየትን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል። 
ፕሬዚዳንታዊ ውድድሩ በስኬት ከተጠናቀቀ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከሚጠብቃቸው በርካታ ተግባራት ከድህነት ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ዋነኛው እንደሆነ ነው የሚነገረው። ይህ ግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው እንደመጡ ጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ ፈተናው ቀላል አይሆንም።
በኒያሜ ጎዳናዎች የበሰለ ድንች በመሸጥ ኑሮውን የሚገፋው አቡበከር ናሜራ ማንም ተመረጠ ማን ለእንደርሱ አይነት ሰዎች ምንም ለውጥ አያመጣም ብሎ ያምናል።
«ማንም ወደ ሥልጣን ቢመጣ ለእኛ ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ስለ ድሆች ማሰብ አለባቸው» ብሏል።

Maman Sambo Sidikou ehemaliger Außenminister Niger
ምስል Getty Images/AFP/J. D. Kannah
Wahlen Niger Niamey | Präsidentschaftskandidat  Mohamed Bazoum
ምስል Issouf SANOGO/AFP
Niger Niamey | Wahlen
ምስል Issouf SANOGO/AFP

የዓለም ባንክ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኒጀር የድህነት መጠኑ  አሁንም ከፍተኛ ነው። ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ ቢያንስ 41 ከመቶው አሁንም ድረስ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይኖራል።
ሀጃራ ባጆ እንደሚሉት የድህነቱ መክፋት በተለይ በጨቅላ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃ የከፋ ነው ይላሉ። አዲሱ ተመራች ፕሬዚዳንት ይህን አስከፊ ሕይወት የመቀየር ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልጻሉ።
«ከ 0 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የሕፃናት ክብካቤ አሰቃቂ ነው ፡፡ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት የሕፃናትን ሕይወት ያሻሽላል ብዬ እጠብቃለሁ ፡»
የተባበሩት መንግሥታት የቁጥር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኒጀር ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ከሆኑ1000 ሕፃናት መካከል ሰማንያዎቹ ይሞታሉ። ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ማሀመዱ ኢሱፉ እጎአ በ2011 የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርት ከነበረበት የ8,7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 12,9 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጋቸው በስኬት ይወሳላቸዋል።
ኒጀር ምንም እንኳ ወደ ዴሞክራሲዊ ሥረዓት የምታደርገው ግስጋሴ በተምሳሌትነት ስሟ እንዲነሳ ቢያደርግም በሌላ በኩል አሁንም ድረስ የሳህል ሃገራት ስጋት ሆኖ የቀጠለው የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ እና ጥቃት ኒጀርን ዴሞክራሲዋን አሳድጋ ድህነቷን እንዳትቀርፍ አንዱ ማነቆ ሆኖባት ሊቆይ እንደሚችል በአካባቢው ዓመታትን የተሻገረው የሽብር ድርጊት እና ያስከተለውን መዘዝ በማሳያነት የሚጠቅሱ ወገኖች በርካቶች ናቸው። ባለፉት አስር ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው እና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከቄዬአቸው ያፈናቀለው የሽብርተኞች ድርጊትን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሳህል ሃገራት በአንድነት ጠይቀዋል።

Niger Wahllokal in Niamey Präsident Mahamadou Issoufou
ምስል Reuters/J. Penney

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ