1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

መተገበሪያው ከአምስት ዶላር ጀምሮ መላክ ያስችላል

ረቡዕ፣ ኅዳር 29 2014

በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራው ይህ ሀገር በቀል መተግበሪያ፤ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሀገር ቤት ላሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከአምስት የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችው በየትኛውም ጊዜና ቦታ በቀላሉ ገንዘብ መላክ የሚችሉበት ነው።

https://p.dw.com/p/43z7F
Äthiopien | Cash Go Logo
ምስል privat

መተገበሪያው ከአምስት ዶላር ጀምሮ መላክ ያስችላል

 
የዕለት ተዕለት ህይወትን  በማቃለል ረገድ ቴክኖሎጅዎች የሚጫውቱት ሚና ቀላል አይደለም። በቅርቡም  ጊዜን እና ወጭን ይቆጥባል የተባለ «ካሽ ጎ» የተሰኘ የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ በኢትዮጵያውያን  ባለሙያዎች ተሰርቷል። ይህ መተግበሪያ ከአምስት የአሜሪካን  ዶላር ጀምሮ  በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን በየትኛውም ጊዜና ቦታ በቀላሉ ገንዘብ መላክ የሚያስችል ነው ተብሏል። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በዚህ መተግበሪያ ላይ ያተኩራል።  
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ቴክኖሎጅ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። በተለይ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚጫኑ መተግበሪያዎች በገንዘብ ተቋማት ላይ በጎ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንን በመገንዘብ ይመስላል  የ«ካሽ ጎ»/ Cash Go/ እና «ጉዞ ጎ» /Guzo Go / መተግበሪያዎች መስራችና ባለቤት አቶ ቲዎድሮስ ሽፈራው፤ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩባቸው ጃፓን እና ቻይና ከዛሬ አስር ዓመት ግድም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በእነዚህ ሀገራት የተመለከቱት የቴክኖሎጅው ሚና ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር የማድረግ ሀሳብ ይዘው ወደ ሀገራቸው የገቡት። ይህንን ሀሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ የሚያደርግ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ።
 « የጀመርኩበት አጋጣሚ እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አሜሪካ ሄደው አንድ ሀሳብ አምንጭተው ነበር።ከኢትዮጵያ ውጭ ያለው «ዲያስፖራ »ከሚያኪያቶ የሚመለሰውን አንድ ዶላር  ወደ ሀገሩ ቢልክ ምን ያህል ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊጠቅም እንደሚችል በገለፁ ጊዜ፤ የተባለውን ነገር ለመተግበር  እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር።እና በዚያ ጊዜ ውስጥ ሳስበው አንድ ዶላር ወይም አምስት ዶላር መላክ የሚያስችል «ፕላት ፎርም»አለ ወይ ብዬ ነበር ያሰብኩት።እና አንዳንድ መረጃዎችን ማገላበጥ ጀመርኩኝ።እኛ ሀገር ካሉ ቴክኖሎጅ ላይ ከሚሰሩ ኩባንያዎች  ጋርም ውይይት ጀመርን።በምናይበት ስዓት ኢትዮጵያ ወይም አፍሪቃ ውስጥ «ሪሚታንስ» ላይ ምንም አይነት ገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ የለም።» ብለዋል።
በዚህ መልኩ ባደረጉት ጥናት በአፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ በቀላሉ ገንዘብ መላክ የሚያስችል ሀገር በቀል መተግበሪያ ካለመኖሩ ባሻገር፤ የውጭ ሀገር የገንዘብ መላኪያ መንገዶቹም ቢሆኑ ለመላኪያ የሚያስከፍሉት የገንዘብ ተመን በዋጋ ደረጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ይገልፃሉ።እንደ አቶ ቲዎድሮስ ይህ የገንዘብ አላላክ ዘዴ ኢትዮጵያን በዓመት ከ700 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ያሳጣታል። ይህም  ሀገር በቀል የገንዘብ መላኪያ መተግበሪያ  ለማበልፀግ ሌላው  ምክንያንያታቸው  ነው። 

Äthiopien Tewodros Sheferaw
ምስል privat

በዚህ መንገድ የችግሩን ስፋት ከተገነዘቡ በኋላ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ ባለሙያዎችንና  ኩባንያዎችን ጋር በመሆን የተለያዩ ቴክኖሎጅ አማራጮችን በመፈተሽ ካሽ ጎ / Cash Go /የተሰኘውን መተግበሪያ እንዲበለፅግ አደረጉ።«ካሽ ጎ» ከማስተርና ቪዛ ዓለም አቀፍ ካርዶች ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባንኮች አማካኝነት በበይነ መረብ ገንዘብ የሚያስተላልፍ መተግበሪያ ሲሆን፤ ከሌሎች የገንዘብ መላኪያ ዘዴዎች  የተለዬ የሚያደርገው እንደ አቶ ቲዎድሮስ  ወጭና ጊዜን የሚቆጥብ እንዲሁም ከአምስት የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መላክ የሚያስችል መሆኑ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ከመላው ዓለም ሆነው  ሀገር ቤት ላሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብ ለሚሰጡት ባንኮች መጠነኛ የአገልግሎት ክፍያ በመክፈል ብቻ በእጅ ስልኮቻቸው በቀላሉ ገንዘብ  መላክ እንደሚችሉ ገልፀዋል። 
አንድ ቴክኖሎጅ  ከጊዜ ቆጣቢነቱ በተጨማሪ የአጠቃቀም ምቹነቱ ውጤታማነቱ ከሚለካባቸው መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ነው።በዚህ ረገድ  መተግበሪያውን ከአንሮይድ ወይም ከጎግል ፕሌይ  በማውረድ በተንቀሳቃሽ ስልክ በቀላሉ አካውንት መክፈት እንደሚቻል አስረድተዋል።
«አጠቃቀሙ ኢንተርኔት ይፈልጋል።በመጀመሪያ «ካሽ ጎ»/ Cash Go/ የሚለውን «አፕሊኬሽን»ከአንሮይድ ወይም ከ «አይ ኦ ኤስ»ላይ ወይም ከ « ፕሌይ ስቶር»ማውረድ ነው።ያንን ካደረጉ በኋላ የመጀመሪያ አካውንት ለመክፈት የሚጠይቁ መስፈርቶች አሉ።ልክ ሌሎች ባንክ ወይም የራሳችን የጎግል አካውንት እንደምንከፍተው ነወ።» 
በዚህ ሁኔታ በተከፈተው አካውንት ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ በተንቀሳቃሽ ስልክ በቀላሉ ገንዘብ መቆጠብና ማስተላለፍ የሚችሉ ሲሆን፤ከተላከ በኋላም መተግበሪያው ለላኪውና ለተቀባዩ ማረጋገጫ መልዕክት እንዲልክ ተደርጎ የተዘጋጄ በመሆኑ አስተማማኝ ነው ይላሉ። በአጠቃቀም ችግር ቢያጋጥም እንኳ ለመተግበሪው የመፍቻ ዘዴ ተዘጋጅቶለታል ።
«አንዳንድ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳ 24 ስዓት «ቻት» የሚደረግበት «ፕላትፎርም» ስለተከፈተ በቀጥታ «ቻት» በማድረግ ባንኮቹን ያገኟቸዋል።እነሱ መልስ ይሰጣሉ።ያጋጠማቸው ችግር ካለ ደግሞ«ሆት ላይን» አለ መልስ ይሰጣሉ።»በማለት ገልፀዋል።

Äthiopien | Guzo Go Logo
ምስል privat

አቶ ቲዎድሮስ ከዚህ ቀደምም «ጉዞ ጎ »የተሰኘ መተግበሪያ በኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጅ ባለሙያዎች እንዲበለፅግ በማድረግ ከመላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች በቀላሉ የዓየር ትኬት መግዛት የሚችሉበትን የቴክኖሎጅ አማራጭ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል።በዚህም ሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ  መደረጉን ገልፀዋል። ይህ መተግበሪያ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች የሚሰራ  ሲሆን፤በአሁኑ ወቅት ከ25,000 በላይ ተጠቃሚዎች ያሉትን አዲሱን መተግበሪያ «ካሽ ጎ»ንም በዚሁ መንገድ የማሻሻል ሀሳብ አላቸው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት የአንድ ሀገር ልማትና እድገት የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ፈጠራና ሀሳብ ነው።ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ በርካታ የፈጠራ ስዎች ሀገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎቻቸው በገንዘብ እጥረት የተነሳ  ወደ ስራና ተግባር ሳይለወጡ ሸልፍ ላይ ይቀራሉ።እንደ አቶ ቲዎድሮስ ባለሀብቶች እና የገንዘብ ተቋማት የፈጠራ ሀሳብ ላይ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈሱ ችግሩን መፍታት ይቻላል።ለዚህም የእሳቸው ተግባር ምሳሌ ነው። ያ ካልሆነ ግን የሀገር ውስጥ ሀሳብና ፈጠራን ችላ ብሎ ቴክኖሎጅን ከውጭ ሀገር በመግዛት ሀገርን ማሳደግ እንደማይቻል ተናግረዋል።


  
ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ