1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኩሚ ናይዱ

ዓርብ፣ ነሐሴ 4 2010

ናይዱን የሚያውቁ የትግል ስልታቸውን ፣በ1970 ዎቹ በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድን ስርዓት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ይካሄዱ ከነበሩ ተቃውሞዎች ጋር ያመሳስሉታል። «ጓድ ኩሚ»ም በመባል የሚታወቁት ናይዱ ሥራውን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ  የሚያካሂደውን የአምነስቲን ህግ አክብረው ሥራቸውን ማከናወን አለማከናወናቸው ከወዲሁ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/32zKy
Faces of climate change Kumi Naidoo
ምስል DW/T.Walker

ኩሚ ናይዱ

የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን መሪነት ከሳምንት በፊት የተረከቡት ደቡብ አፍሪቃዊው ኩሚ ናይዱ ለዚህ ሃላፊነት በመብቃት የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ናቸው። ናይዱ የዚህ ድርጅት ሃላፊ ከመሆናቸው በፊት ለፖለቲካ ለውጦች ለማህበራዊ ፍትህ እና ለአካባቢ ጥበቃ ባካሄዷቸው ትግሎች ይታወቃሉ። ከመካከላቸው ለተፈጥሮ ጥበቃ  በሚከራከረው ግሪን ፒስ በተባለው ድርጅት ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት ይገኙበታል። ኩሚ ናይዱ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን  ከጎርጎሮሳዊው 2010 አንስቶ የመሩትን ሳሊ ሼቲን ሐምሌ 25፣2010 ዓም ተክተዋል። ባለፈው ታህሳስ ድርጅቱ ለዚህ ሃላፊነት የመረጣቸው ናይዱ ህይወታቸውን  በሙሉ  በመብት ተሟጋችነት ያሳለፉ ሰው ናቸው። ናይዱ ዋና ጽህፈት ቤቱ ለንደን ብሪታንያ ለሚገኘው ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል መሪነት እንደተመረጡ በሰጡት አስተያየት በዓለማችን እየተባባሱ የሄዱትን በመሠረታዊ ነጻነቶች እና በሲቪል ማህበራት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መመከት እንደሚገባ አሳስበዋል። ናይዱ በአምነስቲ ትልቁን ሃላፊነት ከመረከባቸው ከቀናት በፊት ልጃገረዶችን ከትምህርት የሚያስቀሩ ችግሮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማስገንዘብ ኪሊማንጃሮ ተረራ ላይ ወጥተው ነበር። ከፍታ መውጣት ለርሳቸው አዲስ አይደለም። ከዛሬ 6 ዓመት በፊትም የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪው ድርጅት ግሪን ፒስ ኢንተርናሽናል ዋና ስራ አስኪያጅ ሳሉ ሩስያ በአርክቲክ የምታካሂደውን የነዳጅ ዘይት ፍለጋ በመጻረር በዚያ በተተከለው የነዳጅ ዘይት መፈለግያ መሣሪያ ላይ ወጥተው ተቃውሞአቸውን ገልጸው ነበር። የዛሬ 9 ዓመት ደግሞ በዚምባብዌ የተፈጠረውን የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት በመቃወም የረሃብ አድማ መተዋል። በናይዱ እምነት አንድን የጋራ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከተናጠል ይልቅ የጋራ ጥረት ውጤት ይኖረዋል። 
«በርግጥ በህብረት ልናከናውናቸው በሚገቡ ተግባራት ራሳችንን መገደብ እንደማይገባን ልናጤን ይገባል። ምክንያቱም እያንዳንዶቹ ሀገሮቻችን ጠንካራ የሚባሉትን ዩናይትድ ስቴትስን እና የአውሮጳ ህብረትን  መቋቋም አይችሉም።» 
ናይዱን የሚያውቁ የትግል ስልታቸውን ፣በ1970 ዎቹ በደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድን ስርዓት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ይካሄዱ ከነበሩ ተቃውሞዎች ጋር ያመሳስሉታል። እናም ናይዱ የግሪንፒስ መሪ መሆናቸው ጥሩ ስጦታ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የግሪን ፒስ አራማጆች ናይዱን ምንም ነገር የማይፈሩ መሪ አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው። መቀመጫውን አምስተርዳም ሆላንድ ላደረገው ግሪን ፒስ አቅጣጫ በማስቀመጥ እና ኃይሉን በማደስም ይወደሳሉ።«ጓድ ኩሚ»ም በመባል የሚታወቁት ናይዱ ሥራውን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ  የሚያካሂደውን የአምነስቲን ህግ እና ደንቦች አክብረው ሥራቸውን ማከናወን አለማከናወናቸው ከወዲሁ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል። አምነስቲ በተለያዩ ጊዜያት በአንዳንድ የምዕራባውያን መንግሥታት አቋሞች ላይ በሚይዘው የተዛባ አመለካከት ይወቀሳል። ከመካከላቸው አንዱ በእሥራኤል ላይ ያለው አቋም ነው። ናይዱ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኙ እንደ ርሳቸው ትውልድ የመብት ተሟጋቾች ሁሉ እሥራኤል፣ ፍልስጤማውያንን የምትይዝበትን መንገድ አጥብቀው ይኮንናሉ። ከዚህ ቀደም AFRICA RISING የተባለው ድርጅት ሊቀመንበር ሳሉ እሥራኤል በሀገርዋ በሚገኙ አፍሪቃውያን ላይ ትፈጽማለች የሚባለውን ዘረኝነት ተቃውመዋል። ደርባን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በጎርጎሮሳዊው 1965  የተወለዱት ናይዱ በደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የሆኑት በወጣትነታቸው በአፓርታይድ ዘመን ነበር። በዘር መድልዎ ስርዓት በተደጋጋሚ የታሰሩት ናይዱ በተሰደዱበት ብሪታንያ  ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሶስዮሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ ከያዘ በኋላ የዘር መድልዎ ስርዓት ሲፈረካከስ ከሌሎች መሰል ስደተኞች ጋር በ1990 ነበር ወደ ሀገራቸው የተመለሱት። ናይዱ በስደት እያሉ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ይመሩ ነበር። ከ10 ቀናት አንስቶ ናይዱ የሚመሩት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከ70 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ቅርንጫፎች ያሉት ከዓለም ትልቁ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ነው። በዓለም ዙሪያ 2600 ሠራተኞች እና 7 ሚሊዮን አባላት፣ በጎ ፈቃደኞች እና ደጋፊችም አሉት።

Südafrika Chef von Greenpeace International Kumi Naidoo
ምስል Reuters
Greenpeace UN Ban-Ki Moon
ምስል Michael Nagle /Greenpeace
Davos WEF Weltwirtschaftsforum 2014 The Public Eye Awards 2014
ምስል picture-alliance/dpa

ቤኒታ ፋን አይዘን /ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ