1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከፍተኛ የግብር ገቢ የሚጠበቅበት የ 2016 ዓ. ም በጀት

ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015

ለሀገር ውስጥ እዳ ክፍያ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና ለመልሶ ማቋቋም እንዲሁም ለማዳበሪያ ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ የተያዘበት መሆኑ የተነገረለት የ 2016 ዓ.ም በጀት በአንፃሩ የመከላከያ ሠራዊትንና የዩኒቨርሲቲዎችን ወጪ ትርጉም ባለው መጠን የቀነሰ ነው ተባለ።

https://p.dw.com/p/4T57S
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

"በ 2016 ዓ.ም ለመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ የካፒታል በጀት ዝቅ እንዲል ተደርጓል"

ለሀገር ውስጥ እዳ ክፍያ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና ለመልሶ ማቋቋም እንዲሁም ለማዳበሪያ ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ የተያዘበት መሆኑ የተነገረለት የ 2016 ዓ.ም በጀት በአንፃሩ የመከላከያ ሠራዊትንና የዩኒቨርሲቲዎችን ወጪ ትርጉም ባለው መጠን የቀነሰ ነው ተባለ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 801.6 ቢሊየን ብር አድርጎ ባቀረበው የ2016 በጀት ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮችና የተቋማት መሪዎች ጋር በዝርዝር ተወያይቶበታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በጀቱ በዋናነት "የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር" እንዲውል ታስቦ መዘጋጀቱን በመግለጽ በዚህ ምክንያት ለመሰረተ ልማቶች ዝርጋታ የካፒታል በጀት ዝቅ እንዲል መደረጉን አስታውቋል።

በውይይቱ "በጀቱ የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ ነው ብለን አናምንም" የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል። በተለይ በተለያየ አካባቢ ተጀምረው ዓመታትን ላስቆጠሩ የመንገድ ግንባታዎች በበጀት ድልድል ዝርዝሩ እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ መመደቡ ሕዝብን ማሳዘኑ ተጠቅሶ ጥያቄ ቀርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ በፈረንሳይ በተደረገ አለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን ጨምሮ የብዙ ታዳጊ ሀገሮች ራስ ምታት የሆነው ልማት ሳይሆን እዳን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለው መሆኑን ገልፀዋል።

Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ከማህደር ፤ የኢትዮጵያ ፓርላማ ምስል Solomon Muchie/DW

በሌላ በኩል በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት እየተንከባለሉ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለ 2016 ዓ.ም ከቀረበው 801.6 ቢሊዮን ብር የወጪ ረቂቅ  በጀት ውስጥ 520 ቢሊዮን ያህሉ አጠቃላይ ገቢ ሲሆን በዋናነት ከግብር የሚሰበሰብ፣ ቀሪው ከእርዳታ የሚገኝ ነው ተብሏል። ይህ ማለት መንግሥት ለወጪ ከያዘው በጀት የ281 ቢሊዮን ብር ጉድለት አለበት ማለት ነው።
በጥሬ ገንዘብ እጥረት ብዙ ፕሮጀክቶችን እያንከባለለች ያለችው ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ አበዳሪዎች ያለባት ከፍተኛ እዳ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ተዳምሮ ይህንን እዳ ለመክፈል የሚያስችል የታክስ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አጠቃላይ ገቢውን ለመሰብሰብ የያዘችው ቁልፍ ተግባር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው ኢዮብ ተካልኝ ገልፀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል። የበጀት ክፍፍል እና ድልድል ፍትሐዊነት ጉዳይ በትለይ በአዳዲስ ክልሌች ላይ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ነው የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።
በዚህ ዓመት የመከላከያ ሠራዊት በጀት እንዲቀንስ መደረጉ በውይይቱ ተነግሯል።
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት 30 ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸው የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዚህ ዓመት በጀታቸው 13 ቢሊዮን ብር ተቀንሶ 17 ቢሊዮን ብር እንደተመደበላቸው ተገልጿል። በገንዘብ ሚኒስትር የበጀት ጉዳዮች የሥራ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ደመቀ በቀጣዩ ዓመት የመንግሥት ሠራተኛ ቅጥር ለምን እንደማይኖር ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ሲሰጡ ባለው የሰው ኃይል መጠቀም የሚል የመንግሥት አቋም በመያዙ መሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ፈረንሳይ ውስጥ  በተካሄደ የፋይናንስ ጉባኤ በአሁኑ ወቅት ከልማት ጉዳይ ይልቅ ዕዳ የአስተዳደራቸው ዋነኛ ራስ ምታት መሆኑን ፣ ይህ ችግር የብዙ ታዳጉ ሀገራት ጭምር መሆኑንም ገልፀዋል።

በዛሬው ውይይት ለወጪ ከቀረበው ረቂቅ የ 2016 በጀት ውስጥ በገቢነት ከግብር የሰበሰባል ተብሎ ከተያዘው 477.8 ቢሊየን ብር ወደ 72 ቢሊዮኑ በተለያዩ ምክንያቶች የማይሰበሰብ ጊቢ መሆኑም ተገልጿል።


ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ