1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጎተ ጋር "ጥበብ ኦንላይን" 

ሐሙስ፣ ጥር 20 2013

ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀና በመማር ላይ ያሉ የዛሬ ወጣት እንግዶቻችን የሥዕል ወዳጆች ናቸው። ሥዕልን ይሥላሉ። ከወራት በፊት ዓለም የተጋፈጠችው የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት መሰል ተሰጥዖዎች የአደባባይ መድረክ ማግኘት እንዳይችሉ ከልክሏል።

https://p.dw.com/p/3oXhO
Äthiopien Addis Ababa | Goethe Kunst Klub | Künstler
ምስል Solomon Muchie/DW

ጥበብ ኦንላይን

ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀና በመማር ላይ ያሉ የዛሬ ወጣት እንግዶቻችን የሥዕል ወዳጆች ናቸው። ሥዕልን ይሥላሉ። ከወራት በፊት ዓለም የተጋፈጠችው የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት መሰል ተሰጥዖዎች የአደባባይ መድረክ ማግኘት እንዳይችሉ ከልክሏል።
በጎርጎሪያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1962 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተቋቋመው የጀርመኑ ጎተ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ በጀርመንና በጠቅላላው በአውሮጳ የባህል ትስስርን የማጠናከር አላማ ይዞ እየሠራ ያለ ነውና እነዚህን መሰል ወጣቶች ሥራዎቻቸውን ለጥበቡ ወዳጆች ማቅረብ የሚችሉበትን "ጥበብ ኦንላይን" የተባለ ፕሮጀክት ቀርፆ እድል አመቻችቶላቸዋል።
አዳጊና አዳዲስ የጥበብ ሰዎች ከዚህ በፊት ሥራዎቻቸውን በአካል ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር እየተነጋገሩ ይሠሩ ነበር። የኮሮና ተኅዋሲ ግን እክል ፈጥራል። ስለዚህም ሥራዎቻቸውን ሠርተው በበይነ መረብ እንዲለቁ ሆኗል። በዚህ ሥራ ውስጥ የተሳተፉት ወጣቶች " አዲስ ስትሬት አርት " የተባለ ሥዕልን ባደባባይ በግድግዳዎችና መሰል ስፍራዎች ላይ የማሳየት ውጥን ይዞ የተነሳው ስብስብ ነው።
ወጣቶቹ ከዚህ በፊትም ከጣልያን እና ከአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የባህል ተቋማት ጋር የሥዕል ሥራዎችን የመሥራት እድል ገጥሟቸዋል። አሁን የጀመሩት ጎዳናዎችን በሥዕል የማስዋብ ውጥን ውስጥም በጎ የዐይን እና የመንፈስ ምግብ የመፍጠር ውጥን አላቸው።
ሥዕል ከስቱዲዮ ውስጥ እና ከኤግዚቢሽን የመታያ ስፍራዎች በላይ መገኘት እንዳለበት የሚገልፁት እነዚህ ወጣቶች የወደፊት ውጥናቸውም ይሄው ነው። ቆሽሸው እና ዝገው የሚታዩ ክፍት የድልድዮች፣ የሕንፃዎች እና የአካፋይ መንገድ ግድግዳዎችን በየ ሥዕሎቻቸው የመሸፈን ሀሳብ አላቸው። ለዚህም እንደ ጎተ ኢንስቲቲዩት ያሉ አጋዥ ተቋሟትን ይጠቀማሉ። 
ጎተ ኢንስቲቲዩት በተለያዩ ዘርፎች የጥበብ ሥራዎችን ያበረታታል። ይደግፋል። ጥበብ ኦንላይን የተባለውን ፕሮጀክት ቀርፆ ለወጣቶች እድል መፍጠር ሲጀምር አላማው በኮሮና ተኅዋሲ መስፋፋት ምክንያት መሰባሰብ ላይ የተፈጠረው እቀባ መሰል የሥዕል ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ሥራዎቻቸውን እየሰሩ በበይነ መረብ እንዲለቁ ማገዝ ነው።
ይሄው የጥበብ ኦንላይን ሥራ በዚሁ በያዝነው የጎርጎርያኑ 2021 ዓ.ም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለሌሎች ወጣቶችም ሰፋ ባለ ሁኔታ አመቱን ሙሉ ማገልገልን እንደሚቀጥል አሳውቋል።

ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ