1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትራምፕ መርሕ መዘዝ

ሰኞ፣ ግንቦት 6 2010

ትራምፕ ለዓለም ሠላም በጋራ የመቆም መርሕን እየተጣሱ፤ ዓለም አቀፍ ሥምምነት እና ዉሎችን አፍርሰዉ ሲጨርሱ ሐገራቸዉን እንዴት ሊመሯት እንዳቀዱ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። የእስካሁኑ እርምጃቸዉ የሐገራቸዉ የቅርብ ወዳጆን  የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራትን ጭምር ማስበርገጉ ግን ሐቅ ነዉ

https://p.dw.com/p/2xhvX
Israel Protesten in Gaza
ምስል Getty Images/S. Platt

ማሕደረ ዜና ፦ ከዓለም የተነጠለችዉ የዓለም መሪ

ሰዉዬዉ ሥለ ንግድ፤ ሥለተፈጥሮ ጥበቃ፤ ሥለ ፖለቲካ ይሁን ሥለዓለም አቀፍ ሥምምነት እንደ ልዕለ ኃያል ሐገር ዴሞክራሲያዊ መሪ ሳይሆን እንደለየለየለት አምባገነን ያሻቸዉን ይናገራሉ።የፈለጋቸዉን በሚፈልጉበት ጊዜ ያደርጋሉም።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።አድናቂ-ደጋፊዎቻቸዉ ይቦርቃሉ።ከግጭት፤ ዉጥረት፤ ጦርነት አትራፊዎች፤ጥቅም ቃራሚዎች፤ ርዳታ ጠባቂዎች ይደግፏቸዋል።የዓለም አቀፍ መርሕ ተገዢዎች ይቃወሟቸዋል።እሳቸዉን ግን ቀጥለዋል።ልጓም ያገኙ ይሆን? የትራምፕ አቋም፤ የዓለም መርሕ፤ እና የዓለም አቀፉ  ማሕበረሰብ መፍረክረክ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

1994 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ያኔ የዓለም ፌደራሊስት ማሕበር ይባል የነበረዉ የአሜሪካ ድርጅት በጣራዉ ስብሰባ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት አሜሪካዊ ፖለቲከኛ ጆን ቦልተን  እንዲሕ ብለዉ ነበር።«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብሎ ነገር የለም።ያለዉ በዓለም ላይ በቀረችዉ ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሐገር፤ በዩናይትድ ስቴትስ  የሚመራ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ነዉ።»

አላበቁም።«ኒዮርክ የሚገኘዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስሪያ ቤት 38 ፎቆች አሉት።አስሩን  ፎቅ ብታፈርሱት የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም።»

ቦልተን ምክትል ሚኒስትር፤ በተሳደቡት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነዉ አገልግለዋል።አሁን በሰባ ዓመታቸዉ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ናቸዉ።

Israel Eröffnung der US-Botschaft in Jerusalem | Videobotschaft von Donald Trump
ምስል picture-alliance/dpa/I. Yefimovich

ቦልተን ከአሜሪካ ሌላ፤ ሌላዉ ዓለም የአሜሪካ ተከታይ ከመሆን ዉጪ «ዋጋም የለዉ» ባሉ በ23ኛ ዓመቱ የዩናይትድ ስቴትስን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን የያዙት ቱጃሩ ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ዓላማ፤መርሕ ፍላጎታቸዉ የቦልተን ዓይነት የቀኝ ፅንፈኛ መሆኑን ደብቀዉ አያዉቁም።«አሜሪካ ትቅደም።

                       

«ዛሬ እዚሕ የተሰበሰብነዉ በመላዉ ከተማ፤ በመላዉ ዓለም ርዕሠ-ከተሞች፤ በመላዉ ዓለም ኃይላት ዘንድ  መሰማት ያለበት አዋጅ እናዉጃለን።ከዛሬ ጀምሮ ሐገራችንን የሚገዛዉ አዲስ ርዕዮት ነዉ።ከዛሬ ጀምሮ መርሐችን አንድ ነዉ።አሜሪካ ትቅደም።አሜሪካ ትቅደም።»

አሜሪካን ለማስቀደም ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በግንብ ከማሳጠር፤ ሙስሊሞች የሚበዙባቸዉ ሐገራት ዜጎች አሜሪካንን እንዳይረግጡ እስከ ማገድ፤ ቀይ ሕንዶች የሚባሉት የአሜሪካ አንጡራ ነዋሪዎች የእምነት ሥፍራን አቋርጦ የሚያልፍ የነዳጅ ዘይት ቧምቧ ከመዘርጋት፤አደገኛ  የከሰል ማዕድናትን እስከ መክፈት የሚደርሱ እርምጃዎችን ወሰዱ።

ሁሉም በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዘመን የታገዱ ነበሩ።«ኦባማ ኬር» ይባል የነበረዉን ለደሐዉ አሜሪካዊ የጤና ዋስትና የሚሰጠዉን ደንብ ሙሉ በሙሉ ማገድ ቢያቅታቸዉ አዳከሙት።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የአሜሪካን ነባር የዉስጥ መርሕ በመገለባበጣቸዉ የደገፋቸዉ እንጂ ከቴሌቪዥን ጫጫታ ባለፍ የተቃወማቸዉ አሜሪካዊ የለም።ምክንያታቸዉ ግን ላንዳዶች አጠያያቂ ነዉ።ለምን?

                               

የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ።ትራምፕ አጥብቆ የተቃወመ የለም።ልክ ናቸዉ።ወይም «ልክ ነኝ» አሉ።ቀጠሉም።ዩናይትድ ስቴትስ ጃፓንን ጨምሮ ከእስያ እና ከፓስፊክ አካባቢ ሐገራት ጋር ያደረገችዉን የንግድ ሥምምነት አፈረሱ።

ዓለም ታሕሳስ 2015 ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ የተፈራረመዉ የዓየር ንብረት ዉል ከ1997 ጀምሮ ሲደረግ የነበረ ንግግር፤ ድርድር፤ ዉይይት ዉጤት ነበር።የዓለምን የጋራ ሥጋት ለመቀነስ ዓለም በጋራ የመቆሙ አብነት፤ የዓለም አቀፋዊነት ምሳሌ ነበር።ዶናልድ ትራምፕ አሽቀንጥረዉ ጣሉት።ሰኔ 2017

                                 

«አሜሪካ እና ዜጎችዋን ለመከላከል ያለብኝን ክቡር ኃላፊነት ለማሟላት፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ሥምምነት ትወጣለች።»አድናቂ፤ደጋፊ፤አወዳሽ አጎንባሻቸዉ አጨበጨበ።የተቀረዉ ዓለም ዓለም ደነገጠ።አዉሮጶች ብዙ ለመኑ።ትራምፕ ቀጠሉ።ታሕሳስ 2017።

                                     

«ስለዚሕ እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሠ-ከተማ መሆኑን በይፋ እዉቅና የሚሰጥበት ጊዜ አሁን መሆኑን ወስኛለሁ።»የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመሩት መንግሥት በትራምፕ ዉሳኔ አለቅጥ ተደሰተ።ፍልስጤሞች 70 ዓመት እንደኖሩበት፤ የዓለም ትልቅ ሐገር ለሌላ እልቂት እንደማገዳቸዉ በግልፅ አወቁት።ለካይሮ-ሪያድ ገዢዎች በርግጥ ካንገት-ዝምታ፤ ካንጀት ደስታ ነዉ የሆነዉ።

እየሩሳሌምን እንደ ቅድስት ከተማዉ የሚያት ዓለም ቅሬታዉን፤ አዉሮጳ-እስያዎች ተቃዋሟቸዉን ማሰማታቸዉ አልቀረም።የሰማ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።ትራምፕ ልክ ናቸዉ።ወይም ልክ ነኝ አሉ ።ዉሳኔያቸዉ  ዛሬ ገቢር ሆነ።የአሜሪካ ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ዞረ።ምዕራብ እየሩሳሌም  ሲፈነጠዝ፤ ሲፈነደቅ፤ ሲጨበጨብ ጋዛ ሰርጥ አስከሬን ሲቆጠር፤ ሲረገድ ዋለ።የሰባ ዓመት ዑደት።የደም ጎርፍ።

Israel Protesten in Gaza
ምስል Getty Images/S. Platt

ኢትዮጵያዊዉ እስራኤላዊዉ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ራሕሚም አል አአዛር እንሚለዉ የፍልስጤሞች ኩርፊያም ሆነ የሌሎቹ ተቃዉሞ ከሳሚ ነዉ።

                    

የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር ለማስቆም በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ አምስቱ ሐገራት ጀርመንን ደብለዉ ድፍን 12 ዓመታት ከኢራን ጋር ተደራድረዋል።ድርድሩ በ2015 በተፈረመዉ ዉል ሲያሳርግ ለዓለም ሠላም ታላቅ ተስፋ፤ ጠብን በድርድር ለማስወገድ ሕያዉ አብነት፤የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንዳሉት ደግሞ ለዲፕሎማሲ ታላቅ ድል ነበር።

ትራምፕ ዉሉን እንዳያፈርሱ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ እና የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዋሽግተን ድረስ ሔደዉ ተማፅነዉ ነበር።የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬዛ ሜይ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአዉሮጳ ሕብረት ባለሥልጣናት በስልክ «ለማባበል» ሞከረዉ ነበር።ሰዉዬዉ አልሰሙም።ግንቦት ስምንት።«ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን የኑክሌር ሥምምነት መዉጣትዋን አስታዉቃለሁ።ይኸ ስምምነት ጨርሶ መደረግ አልነበረበትም።»

ከእስራኤል እና ከሳዑዲ አረቢያ በስተቀር የትራምፕን ዉሳኔ ያልተቃወመ መንግሥት የለም።ዉሳኔዉ እስራኤልና ኢራንን ማቆራቆስ ይዟል።ቁርቁሱ ድፍን ሰባ ዓመት በአረብ-አይሁድ ደም የጨቀየዉን ምድር በአይሁድ-አረብ-ፋርስ ደም ያጥበዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ረሕሚም እንደሚለዉ እስራኤሎች ለምደዉታል።

Israel Eröffnung der US-Botschaft in Jerusalem
ምስል picture-alliance/dpa/I. Yefimovich

                           

ትራምፕ ለዓለም ሠላም በጋራ የመቆም መርሕን እየተጣሱ፤ ዓለም አቀፍ ሥምምነት እና ዉሎችን አፍርሰዉ ሲጨርሱ ሐገራቸዉን እንዴት ሊመሯት እንዳቀዱ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። የእስካሁኑ እርምጃቸዉ የሐገራቸዉ የቅርብ ወዳጆን  የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራትን ጭምር ማስበርገጉ ግን ሐቅ ነዉ።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የነበረዉን የዓለም መርሕ ያዛባ ይለዋል።

                                    

የትራምፕ የ«አሜሪካ ብቻ ትቅደም» መርሕ የአዉሮጳ ኃያላን ሌላ አማራጭ እንዲያማትሩም እያስገደዳቸዉ ነዉ።እስካሁን የአሜሪካ ታማኝ ተሻራኪ የሆኑት እነ ፈረንሳይ፤ጀርመን፤ እና ሌሎቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት ፀጥታን በማስከበሩ ረገድ ከአሜሪካ ጥገኝነት የተላቀቀ የራሳቸዉ ኃይል ለማቋቋም አንድ-ሁለት እያሉ ማለታቸዉ በራሳቸዉ ለመቆም ባይወስኑ እንኳ መፈለጋቸዉን ጠቋሚ ነዉ።የትራምፕ መርሕ በዚሑ ከቀጠለ ደግሞ አዉሮጳ ሕብረት ከብሪታንያ፤ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ተቀራርበዉ ወይም ቤጂንግ እና ሞስኮን ትተዉ ለብቻቸዉ አሜሪካኖችን የሚፎካከር ሌላ ኃይል ሊፈጥሩ ይችላሉ ባዮችም አሉ።እንደገና ገበያዉ ንጉሴ።

Israel Protesten in Ramallah
ምስል picture-alliance/AP Photo/N. Nasser

                          

የፍትሕ አብነትዋ፤የዴሞክራሲ ቀንዲሊቱ፤ የነፃነት ጠበቃይቱ ሐገር ዩናይትድ ስቴትስ አንድ ሰዉ በፈለገዉ ሰዓት፤የፈለገዉን ሲያደርግባት ማየት፤ የዓለም አስተባባሪይቱ ሐገር በአንድ ሰዉ ዉሳኔu ከዓለም ስትነጠል  ማስተዋል በርግጥ ግራ አጋቢ ነዉ።ወይም አንድም ሥለለዚያች ሐገር የሚባል እና የሚደሶከረዉ ተረት-ተረት ነዉ። ሁለትም ሥለዓለም ስምምነት የሚነገረዉ ሐሰት ነዉ ያሰኛል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ