1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትዕግሥት የዩኒቨርስቲው ሽልማቶች በሙሉ ተበርክተውላታል

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 30 2013

የትዕግስት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ናዖድ መኮንን ትዕግስትን በቅርብ እንደሚያውቋትና ንቁ፣ በጣም ጎበዝ፣ ሌሎችን በእውቀቷ የምታግዝ ታታሪ ተማሪ እንደሆነች መስክረዋል፡፡ ውጤቷን በተመለከተ ረዳት ፕሮፌሰር ናዖድ ሲያስረዱ ከተማረቻቸው 39 ትምህርቶች መካከል 24A+,13A, 2A- ማስመዝገቧንና የምታኮራ ልጅ እንደሆነች አብራርተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3nhno
Äthiopien I Absolventin Tigist Mekonnen
ምስል Privat

ከወሉ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ትዕግሥት መኮንን


ትዕግስት መኮንን ተወላዳ ያደገችውና የተማረችው በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ “ቁር ቁር” በተባለ ሰፈር ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በመሩሐ ጥበብ፣ 9ነኛና 10ኛ ክፍልን ቅዳሜ ገበያና የመሰንዶ ትምህርቷን በመምህር አካለ ወልድ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ አባቷ በጥበቃ ስራ የሚተዳደሩ ሲሆኑ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ከአንድ ወንድምና ሶስት እህቶቿ መካከል የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ ዘንድሮ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል እጅግ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጃቸውን ሁሉንም ሽልማቶች በማሸነፍ “አስደናቂና ተዐምረኛ” ተብላለች።በ2010 ዓ ም ወሎ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅላ በፋይናንስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቅቃ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 23/2013 ዓም ተመርቃለች፡፡ ወጣቷ በቆይታዋ ውጤታማ አንደነበረችና ከዓመቱ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት ነው ትምህርቷን የጨረሰች፡፡ ለዚህ ውጤት ያበቃት ውጤት ትምህረቷን ባግባቡ መከታተሏና ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በጋራ መስራቷ እንደሆነም በስልክ ባደረግነው ጭውውት ነግራናለች፡ 
ተዕግስት በተመረቀችበት እለት 5 የተለያዩ ሽልማቶችን ሰብስባ ወስዳለች፣ ሽልማቱ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፈጥሮብኛል ያለችው ተመራቂዋ ከፋይናንስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አንደኛ በመሆን ሜዳሊያ፣ ከደሴ ካምፓስ አንደኛ በመውጣት ዋንጫና ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ከአጠቃላይ ከዩኒቨርሲቲው አንደኛ በመሆን ሌላ ዋንጫ፣ ከአጠቃላይ ሴቶች አንደኛ በመውጣት ሌላ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተሸልማለች፡፡በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የትዕግስት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ናዖድ መኮንን ትዕግስትን በቅርብ እንደሚያውቋትና ንቁ፣ በጣም ጎበዝ፣ ሌሎችን በእውቀቷ የምታግዝ ታታሪ ተማሪ እንደሆነች መስክረዋል፡፡ ውጤቷን በተመለከተ ረዳት ፕሮፌሰር ናዖድ ሲያስረዱ ከተማረቻቸው 39 ትምህርቶች መካከል 24A+,13A, 2A- ማስመዝገቧንና የምታኮራ ልጅ እንደሆነች አብራርተዋል፡፡በእለቱ ተመራቂዋና የትዕግስት የቅርብ ጓደኛ ዘነቡ ታመነ ስለጓደኛዋ ስትናገር ልቱ ካላት ጉብዝና አንፃር ሽልማቱ ሲያንሳት እንጂ የሚበዛባት አይደለም ብላለች፡፡ ወላጅ እናቷን ወ/ሮ ሽምብራ ሞገስ በጣም እንደተደሰቱና ዘመድ አዝማዱና ጎረቤቱ ሁሉ መደሰቱን ነግረውኛል፡፡ አጠቃላይ ውጤት 3.98 እንዳስመዘገበች የምትናገረው ትዕግስት ወደፊት በዩኒቨርሲቲው መምህር ሆና የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ተናገራለች፡፡ 
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ናዖድ መኮንን ከዚህ ዝግጅት ጥንቅር በኋላ በስልክ እንደገለፁልኝ የትምህርት ክፍሉ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ትዕግስትን በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ፣ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንድትቀጠር መስማማቱን፣ እርሷም ፈቃደኛ መሆኗንና የመጨረሻ ውሳኔ ከዩኒቨርሲቲው እየተጠበቀ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

Äthiopien I Absolventin Tigist Mekonnen
ምስል Privat
Äthiopien I Absolventin Tigist Mekonnen
ምስል Privat

አለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ