1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከእውነት የተኳረፈ ማኅበረ-ፖለቲካ

ዓርብ፣ ነሐሴ 22 2012

"በኢትዮጵያ የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ሰዎችን ለሹመት እና ለሽረት፣ ለመውደድና ጥላቻ፣ ለስኬት እና ውድቀት እያመቻቸ ነው" የሚለው በፍቃዱ ኃይሉ ለዶይቼ ቬለ በጻፈው የግል አስተያየት ይኸው ጉዳይ "የረጋ ፖለቲካዊ ምኅዳር እንዳይኖር አድርጓል" ሲል ይሞግታል።

https://p.dw.com/p/3hcUa
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

በሥራ ጉዳይ ስለተዛቡ መረጃዎች ጉዳይ ሳነብ እና ከሰዎች ጋር ስወያይ ነው የከረምኩት። አንዳንዶች ዘመኑን የድኅረ-እውነት ዘመን ይሉታል። የድኅረ-እውነታ ዘመን የሚባለው ሰዎች መረጃን የሚዳኙት ስሜታቸውን በኮረኮረበት ልክ እንጂ፥ እውነታውን መሠረት አድርገው ባለመሆኑ ነው። ሌሎች ጉዳዩን ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር ያቆራኙታል። እንደ እውነቱ ግን ችግሩ የዚህ ዘመን ልዩ ክስተት አይደለም። መረጃን ማዛባት ማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠረው ነገርም አይደለም። በሐሰት ማኅበረ-ፖለቲካዎችን መመሥረት የነበረ፣ ያለ እና ምናልባትም ወደ ፊትም የሚኖር ነገር ነው። ነገር ግን በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት እና ኋላ ቀርነት በሚጎትታቸው አገራት ውስጥ ክፋቱ የትየለሌ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ነጋ ጠባ የምንመለከተውም የተዛቡ መረጃዎችን ጦስ ነው። በኢትዮጵያ የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ሰዎችን ለሹመት እና ለሽረት፣ ለመውደድና ጥላቻ፣ ለስኬት እና ውድቀት እያመቻቸ ነው። የተዛቡ መረጃዎች በሁሉም ወገን እየተደጎሙ ይፈሳሉ። በዚህ ዘመን ማንም ጦር-ሰብቆ ከሚያሸንፈው በላይ የተዛባ መረጃ ነዝቶ ድል የመቀዳጀት ዕድሉ ሰፊ ነው። ይህ የረጋ ፖለቲካዊ ምኅዳር እንዳይኖር አድርጓል። ይህንን በከፊል የመመከት አቅሙ የሌላቸው ተቋማት አለመኖር ደግሞ ወትሮም የሚዋልለውን ምኅዳር በማዕበል እንዲናጥ ፈርዶበታል። ከዚህ ማዕበል በቅርቡ እና በሰላም እንወጣ ይሆን? እንዴት?

የመረጃ ‘ሞኖፖሊ’ መሰበር

የመረጃ ማዛባት ጉዳይ አዲስ አይደለም። ዓለም የተገነባችው በበርካታ የተዛቡ መረጃዎች ላይ ነው። የእልፍ አእላፍ እምነቶች መቋቋም፣ ብሔረሰባዊ መነቃቃቶች፣ የአገረ መንግሥታት ምሥረታዎች ሁሉም የሆነ ፍላጎት የወለዳቸው ምኞቶች፣ ተረታ-ተረቶች እና ሌሎችም የፈጠሯቸው ናቸው። ሃይማኖቶች፣ ብሔረሰቦች እና አገረ መንግሥታት ሰዎችን አሰባስበው ባንድ ያኖሩ የማኅበረ-ፖለቲካ መጠለያዎች ናቸው። ነገር ግን ዛሬ ዛሬ እንኳን አዲስ ማኅበረ ፖለቲካ መመሥረት ቀርቶ፣ የነበሩትንም ባሉበት ማቆየት እስኪከብድ ድረስ መረጃዎች የተቋማቱን ምሰሦዎች እያፈረሱ ነው። አንዳንዶቹ የማኅበረ-ፖለቲካ ተቋማት በእውነት ይፈርሳሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በውሸት።

ድሮ ድሮ የመረጃ የበላይነት (‘ሞኖፖሊ’) ሀብት እና ሥልጣን በተቆጣጠሩ ሰዎች እጅ ነበር። ዛሬ ታሪክ ብለን የምንሠማው ወይም የምንረዳው የድሮ ኀያላን ታሪክ ብለው ያኖሩልንን ነው። የታሪክ ምሁራን በርካታ ማስረጃዎችን እያሰባሰቡ እውነቱን ለማንጠር ይሞክራሉ። ነገር ግን እውነታን እንኳን ከዘመናት በኋላ እና በወቅቱ እንኳን ማንጠር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በዚህ ዘመን የሚፈጠሩ የሐሰተኛ መረጃዎችን ‘ሐሰትነት’ የማረጋገጥ ፈተናዎች ያሳያሉ። ሐሰት እንደሆኑ ከተረጋገጡልን ዜናዎች በላይ ሐሰት መሆናቸውን በቅጡ እንኳን ሳናስተውላቸው የሚያልፉት የትየለሌ ናቸው።

አሁን ይህ የመረጃ የበላይነት ተሰብሯል። አንድ መንገድ የነበረው የመረጃ ሰጪ እና ተቀባይነት፣ በዘመንና ቴክኖሎጂ የሚመራ ሁሉንም መረጃ ሰጪ፣ ሁሉንም መረጃ ተቀባይ ያደረገ ዘመን ላይ ደርሰናል። ሰዎች መንግሥትንም ተቀናቃኞቻቸውንም አያምኑም። ከዚያ ይልቅ በሴራ ትንተናዎች ይማረካሉ። 

የማኅበራዊ ሚዲያ ሚና

አፈ እንግሊዞቹ ‘ዳታ አዲሱ ነዳጅ ነው’ (‘data is the new oil’) የሚል ፈሊጣዊ አባባል ፈጥረዋል። አባባሉ የዲጂታል ዘመን ካፒታሊዝምን የገቢ ምንጭ በቅጡ የተረዳ አባባል ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ምንም እንኳን “በነጻ” እንድትስተናገዱ ቢፈቅዱላችሁም፣ የግንኙነት መረባችሁን ቢያሰፉላችሁም፣ የምትፈልጉትን መረጃ ከሥር ከሥር እያቀረቡ ቢያስገርሟችሁም፣ ያንን ሁሉ የሚያደርጉላችሁ በነጻ አይደለም። ውድ የሆነውን የግል መረጃችሁን፣ ዝንባሌያችሁን እና ምናልባትም እናንተ ያላስተዋላችሁትን ባሕሪያችሁን ሁሉ እየቸበቸቡ ትርፍ እያተረፉ ነው።

ነገሩ እንዲህ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያ ውስጠ ቀመር (‘አልጎሪዝም’) የሚሠራው በዕለት ተዕለት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችሁ ላይ ተመርኩዞ ነው። ስለዚህ እናንተ በቀጥታ የምትናገሩትን ብቻ ሳይሆን በቅጡ ሳታስቡበት የምታደርጉትን ነገር በሙሉ በመሰብሰብ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የልብ አውቃ መስለው የምትፈልጉትን ያቀርቡላችኋል። ስለዚህ እናንተም ከዚያ መድረክ አትጠፉም፣ ማስታወቂያቸውን ትከታተላላችሁ፣ በሌላም ሌላም ተግባር ትጠመዳላችሁ። በማኅበራዊ ሚዲያ የግል ግድግዳችሁ ላይ የምታዩት ነገር በሙሉ ውስጠ ቀመሩ የለት’ተዕለት እንቅስቃሴያችሁን አይቶ የምትወዱት፣ ወይም የሚማርካችሁ ነገር ነው እያለ የሚያቀርብላችሁ ስጦታ ነው። በምላሹ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎቹ በርካታ ደንበኞችን ያፈራሉ። አሁን አሁን ኮርፖሬቶች ምን ዓይነት ማስታወቂያ፣ በየትኛው መድረክ፣ መቼ እና ለማን ማቅረብ እንዳለባቸው እንቅጩን ያውቃሉ። ምክንያቱም የማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጠ ቀመር በነጻ የሰበሰባቸውን ዳታዎች ቀምሮ ለደንበኞቹ ያቀርባል። የተዛቡ መረጃዎችም እንደ ሰደድ እሳት የሚባዙት በደስታ ወይም በንዴት የሚያባዟቸውን እናንተኑ የመሰሉ ተጠቃሚዎችን ተንተርሰው ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያ ደንበኞች የንግድ ኮርፖሬቶች ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ፖለቲከኞችም ሐሳባቸውን አዋደው የሚሸጡበት፣ በርካታ ተከታይ የሚሸምቱበት ነው። ሳይንስ ያልተማሩ ሳይንቲስቶች፣ ቅዱስ መጽሐፍ ያላነበቡ የእምነት መሪዎች፣ አንድ የፖሊሲ መሥመር የሌላቸው ፖለቲከኞች የሚፈልቁበት መድረክ ነው። ለዚህ ነው ማኅበራዊ ሚዲያ ከእውነት የተጣሉ፣ የፈለገውን ያክል ማስረጃ ቢደረደርላቸው ሐሳባቸውን የማይለውጡ ‘አክራሪዎች’ የበዙበት ነው የሚባለው። ቀድሞ የነበረው ከእውነት ይልቅ ስሜትን የመከተል አዝማሚያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ትክክለኛ ቦታውን አግኝቷል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ተወደደም ተጠላም ማኅበራዊ ሚዲያ ሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን አያቆምም። በዘመነ ማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን የምንመለከትበትን መንገድ እንድንቀይር አስገድዶናል። ቀላል፣ ቀልጣፋ እና ሁሉን እኩል አድራጊ መድረክ ነው። ነገር ግን ሁሉም ታማኝ ነው ማለት አይደለም። መረጃዎች ስሜት ያዘሉ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል። መረጃዎች በመረጃ ሰጪዎቹ ፍላጎት ልክ እንደሚሰፉ መታወቅ አለበት። ጋዜጦች፣ ሬዲዮኖች እና ቴሌቪዥኖች በበዙባቸው ጊዜያት በአርትኦት ውስጥ አልፈው ለሕዝብ የሚደርሱት በአንዱ ወገን ተናጋሪነት፣ በሌላው አድማጭ አንባቢነት ነበር። አሁን ግን እዚያው በዚያው መልስ ያገኛሉ። ሰዎች መረጃው የሚሰጣቸው ስሜት ሳይቀዘቅዝ ምላሻቸውን ባሻቸው መንገድ የሚያቀርቡበት ጊዜ ስለሆነ ስሜታዊ ንግግሮች እንጂ በእውነት የታሹ፣ አመክኗዊ ሙግቶች የበለጠ ተደራሲ አይማርኩም።

ከዚህ ዓይነቱ ከእውነት የተኳረፈ የመረጃ ልውውጥ ባሕል ሁሉም ሰው ራሱን መጠበቅ አለበት፤ ነገር ግን ፈተናው በግለሰብ ደረጃ አይመከትም። በዴሞክራሲ ስርዓት በምጣኔ ሀብት የበለፀጉ አገራት በተዛቡ መረጃዎች የሚደርስባቸው ጉዳት፣ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ድሃ እና ኋላ ቀር አገራት ጋር የሚወዳደር አይደለም። እነርሱ የተዛቡ መረጃዎችን ለመረዳት የሚችሉ ማኅበረሰቦችን የሚገነቡ ሲቪል ማኅበራት አሏቸው፣ ኢትዮጵያ እነዚህ የሏትም። እነርሱ የባለሥልጣናትን፣ የፖለቲከኞችን እና የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ንግግር ከሥር ከሥር እየተነተኑ እና እየመረመሩ ሐቅ የሚያነጥሩ ጠንካራ ብዙኀን መገናኛዎችና ንቁ ጋዜጠኞች አሏቸው፤ ኢትዮጵያ እነዚህም የሏትም። እነርሱ  የመንግሥት እና የግል ተቋሞቻቸው ግልጽ እና ተጠያቂ የሚሆኑባቸው ተቋማት አሏቸው፤ ኢትዮጵያ የላትም። እነርሱ በተዛቡ መረጃዎች የተነዳ አመፅ እና ነውጥ ቢኖር መቆጣጠር የሚችል የፀጥታ መዋቅር አላቸው፤ የኢትዮጵያ የፀጥታ መዋቅር በተዛቡ መረጃዎች ተነድቶ የባሰ አመፅ እና ነውጥ እንደማይፈጥር እርግጠኛ መሆን አይችልም።

ከላይ የጠቀስኳቸው ተራ መላ ምቶች አይደሉም። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሲፈጠሩ ላየናቸው አገር ለፈተኑ ክስተቶች በአገር ዐቀፍ ደረጃ ልንስማማባቸው የምንችላቸው እውነቶች ካለመኖራቸው የመነጩ ድምዳሜዎች ናቸው። ይኸውም እንዲህ ያሉ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭቶችን ወጀብ ለመመከት የሚያስችሉ ተቋማት ቀድመን ባለመገንባታችን የመጣ ችግር ነው። መፍትሔውም፣ ተቋማቱን መገንባት ላይ መሽቀዳደም ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ዘመኑን የዋጀ መፍትሔ ይገኛል። አለበለዚያ ግን “ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው እንዲሉ” የኢትዮጵያ አገራዊ ኅልውና በዚህ ብቻ ሊፈተን ይችላል።

በፍቃዱ ኃይሉ

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።