1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኢትዮጵያ ፖሊስ እጅ ያመለጠው ኤርትራዊ የሰዎች አዘዋዋሪ ሱዳን ውስጥ ተያዘ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 28 2015

ስደተኞችን የሚያፍን፣ የሚዘርፍ እና የሚገድል የወንጀለኞች ቡድን መሪ ነበር የተባለ ኤርትራዊ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ኪዳነ ዘካርያስ የተባለው የሰዎች አዘዋዋሪ በየካቲት 2013 ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ ያመለጠ ነው። በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ስደተኞችን በማስራብ እና በማሰቃየት ተከሶ በሌለበት ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ነበር

https://p.dw.com/p/4Lq5A
Logo Interpol
ምስል EPA/WALLACE WOON/dpa/picture alliance

በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድ ፖሊስ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ኤርትራዊ የሰዎች አዘዋዋሪ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስታወቀ።

ከዘጠኝ ወራት የዓለም አቀፍ ፖሊስ አሰሳ በኋላ የ39 ዓመቱ ኪዳነ ዘካርያስ ሐብተማርያም ባለፈው እሁድ በቁጥጥር ሥር የዋለው በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በጠረጠረችው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጥቆማ ነው። 

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሸይክ ሳይፍ ቢን ዛይድ አል ናህያን ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ኪዳነ በቁጥጥር ሥር የዋለው ሔኖክ ዘካሪያስ ከተባለ ወንድሙ ጋር ነው። 

ኤርትራዊው ኪዳነ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ በኢንተርፖል ሲፈለግ የነበረ ሲሆን በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአገር ወደ አገር እንዳዘዋወረ ይታመናል። ኢንተርፖል ትላንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪው በሊቢያ በኩል የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞችን የሚያፍን፣ የሚዘርፍ እና የሚገድል የወንጀለኞች ቡድን መሪ ነበር ሲል ከሶታል።

የኪዳነ መታሰር ወደ አውሮፓ ለሚደረገው ሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ድርጊት ትልቅ ጉዳት እንደሚሆን የገለጸው ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወንጀለኛው ቡድን እንዳይበዘበዙ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክትም እምነቱን ገልጿል። 

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባለሥልጣናት በተጠርጣሪው ቤተሰቦች ላይ ባደረጉት ክትትል የደረሱበት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መረብ ወደ ሱዳን መርቷቸው ኪዳነ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢንተርፖል መግለጫ ይጠቁማል። 

ኪዳነ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ስደተኞችን በማስራብ እና በማሰቃየት ተከሶ በሌለበት ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ነበር። ኤርትራዊው ግን በቁጥጥር ሥር በዋለባት አዲስ አበባ የተጠረጠረበትን የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ጉዳይ ሲከታተል ቆይቶ ከውሳኔው በፊት የካቲት 11 ቀን 2013 ከፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ አምልጧል። 

የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል "ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ" ያሉትን ኤርትራዊ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገውን "ከፍተኛ ጥረት" አድንቀዋል። የኔዘርላንድ ዐቃቤ ሕጎች በበኩላቸው ኪዳነ በአገራቸው በተጠረጠረበት የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ፍርድ ቤት ለማቆም ተላልፎ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።  በቅድሚያ ግን ኪዳነ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ፍርድ ቤት ልታቆመው ለምትፈልገው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ተላልፎ ተሰጥቷል።

እየተካሔዱ በሚገኙ ምርመራዎች እና የኢንተርፖል አባል አገራት ትብብር ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ይውላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም አስታውቋል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ