1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአፍሪቃዉያን ለትራምፕ፤ አሁን ፀያፍ ስያሜ የሚገባዉ ማነዉ? 

ቅዳሜ፣ ጥር 1 2013

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሰሙኑን በአሜሪካ ትቅደም «America First» ፖለቲካቸዉ አሜሪካን ቁልቁል እየነድዋት መሆኑ እየተነገረ ነዉ። በአፍሪቃ ምንም በሚባል ደረጃ ወዳጅ ያላፈሩት ትራምፕ የአፍሪቃና ሃይቲ መጤዎቹን በማንቋሸሽ ተጠቀሙት የተባለው ፀያፍ አነጋገራቸዉ በአፍሪቃ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበር አይዘነጋም።

https://p.dw.com/p/3ni0V
USA | Präsidentschaftswahl | Demonstranten im Capitol
ምስል Leah Millis/REUTERS

የፅንፈኝነት መጨረሻዉ ይሄ ነዉ

የዴሞክራሲ ቁንጮ፤ የብልጽግና ጫፍ ፤ የመናገር ነፃነት ቀንዲል የሚባልላት ሃገረ አሚሪካ ጥቁር ጠል፤ ዘረኛ ከዓመት ገደማ በፊት ደግሞ ወፈፊ በሚል መጠርያ የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሰሙኑን በአሜሪካ ትቅደም «America First» ፖለቲካቸዉ አሜሪካን ቁልቁል እየነድዋት መሆኑ እየተነገረ ነዉ።

ትራምፕ አይደለም የሌላዉ የዓለም ሃገራት ነዋሪዎች አልያም የሃገራቸዉ ሕዝብ፤ የገዛ ፓርቲ አባላቶቻቸዉ እየተናገሩና እሸሽዋቸ ስልጣናቸዉን እየለቀቁ ነዉ።  የተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በያዝነዉ ሳምንት ረቡዕ ለሃሙስ አጥብያ በዋሽንግተን ዲሲ የሀገሪቱ ምክር ቤቶች የሚገኙበትን ካፒቶል ህንጻን መዉረራቸዉ እና ያገኙትን መሰባበራቸዉ ማበለሸታቸዉ በዓለም ዙሪያ ድንጋጤ እና ንዴትን የቀላቀለ አስተያየቶችን እያሰናዘረ ነዉ። ከምርጫዉ ማግስት ጀምሮ በምርጫ ድምጽ ቆጠራ ተጭበርብሪያለሁ በማለት ንዴት እና ዝልፍያ የቀላቀለ ንግግር እያሰሙ የሰነበቱት ትራምፕ ባለፈዉ ረቡዕ ምሽት  «አሜሪካንን ዳግም ከፍ እናድርግ » ሲሉ ከደጋፊዎቻቸዉ ጋር ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ዋሽንግተን  የአሜሪካ ምክር ቤቶች በሚገኙበት ካፒቶል ሕንጻ አካባቢ በጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ አሜሪካንን ከፍ ሳይሆን ዴሞክራሲዋን የተፈታተነ ተግባር መፈፀማቸዉ እያሶቀሳቸዉ ነዉ።  በዚህ ግጭት እና ወረራ እስካሁን የአምስት ሰዉ ሕይወት አልፎአል፤ ብዙዎች ተጎድተዋል። ድርጊቱ የአሜሪካንን አቋም አያንጸባርቅም፤ የአሜሪካ ዴሞክራሲ በሕገ ወጦች መሰናከል የለበትም ፤ የአብዛና ምዕራባዉያን መንግሥታት አስተያየት ነዉ። ሱዳን በቅርቡ ከአሜሪካ የሽብር ጥቁር መዝገብ ትፋቅ እንጂ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንደመጡ ሊቢያን ጨምሮ ከሱዳን እና ከሶማልያ የሚመጡ ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸዉ የሚታወስ ነዉ። በዚህም ግማሹ አሜሪካ ግማሹ ሱዳን አልያም ሶማልያ ቀርተዉ ተለያይተዉ ሲኖሩ በትራምፕ የስልጣን ዘመን ልክ አራት ዓመት ሊሆናቸዉ ነዉ። በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ምክር ቤት የተፈፀመዉን ወረራ አህጉረ አፍሪቃ በቴሌቭዥን መስኮት ተከታትሎአል። ስልጣን አለቅም ብለዉ ስለታገሉት ትራምፕ እና ደጋፊዎቻቸዉ ጉዳይ ከናይጀርያ የደረሰን አንድ አስተያየት እንዲህ ይደመጣል።  
«በዋሽንግተን በሁለቱ የፓርላማ መቀመጫ በሚገኝበት በካፒቶል ሂል የተከሰተዉ ነገር እጅግ እረፍት የማይሰጥ አስደንጋጭ ጉዳይ ነዉ። ይህን ሁሉ ዉዝግብ እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ምክንያት የሆነዉ ሰዉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ነዉ። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አይነት የትራምፕ አይነቶች በዓለማችን ተፈጥረዋል። በኔ ሃገር በናይጀርያም እንዲህ አይነት ሰዉ አለ። ልክ የትራምፕን አይነት ባህሪ ያላቸዉ ሰዎች እኛም ጋር እንዳሉ እያየን ነዉ። የኅብረተሰቡን ፍላጎት ከማስፈፀም ይልቅ ፍላጎቱ የማይቀበሉ እና የሚቀብሩ ሰዎች እናዳሉን አይተናል።»   
ዋሽንግተን ካፒቶል ሕንጻ ዉስጥ የሚገኘዉ የተወካዮች ምክር ቤት እና የመወሰኛ ምክር ቤቱ በትራምፕ ደጋፊዎች ወረራ ለአራት ሰዓታት ይጨናገፍ እንጂ ምክር ቤቶቹ ስብሰባቸዉን አካሂደዉ  ባለፈዉ ሕዳር የተመረጡትን የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ  ባይደንን በፕሬዝደንትነት፣ ካማላ ሐሪስ ደግሞ በምክትል ፕሬዝደንት  መመረጣቸዉን ዛሬ በይፋ አረጋግጠዋል። ሌላዉ ናይጀርያዊ አስተያየት ሰጭ ትራምፕ ተስፋ ቆርጠዋል ባይ ነዉ። 
«ያየነዉ ነገር ፀረ ዴሞክራሲ ነዉ። እርግጠኛ ነኝ ሰዉየዉ ከሕዝቡን ፍላጎት ዉጭ የሄደዉ ተስፋ በመቁረጡ ነዉ »   
አንዳንድ የአዉሮጳ ጋዜጦች አሜሪካ  ላለፉት 24 ሰዓታት ኢራቅ፤  ሶሪያ፤ የመን ፤ ሊቢያ እና ቤላሩስያን መስላ ውላለች ሲሉም በታሪክ በምንገኝበት እድሜ በአሜሪካ ያልታየ ሲሉ ላይ ትችቶቻቸዉን ሰንዝረዋል።  ኢትዮጵያዊዉ ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ በዋሽንግተን የታየዉ አሳፋሪ ጉዳይ እንደመጥፎ ምሳሌ እንዳይሆን የሚል ስጋት አለዉ። 

 Twitter gegen Trump | Karikatur | Sergey Elkin
ምስል S. Elkin

በአፍሪቃ ምንም በሚባል ደረጃ ወዳጅ ያላፈሩት ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪቃ እና ሃይቲ መጤዎቹን በማንቋሸሽ ተጠቀሙበት የተባለው ፀያፍ አነጋገር በአፍሪቃ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበር አይዘነጋም።  ትራምፕ ስልጣን ላይ ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ ቆሻሻ ቦታን ለመግለጽ የሚው ለውን ይህን ጸያፍ ቃል መጠቀማቸው አህጉሩ ስለሳቸው ያለውን አሉታዊ አመለካከት ከመጀርያዉ የሰፋ አድርጎትም ነበር።  በዚህም ነዉ  ብዙዎች  ትራምፕን ዘረኛ የሚልዋቸዉ። ዶናልድ ስልጣን በያዙ ሰሞን ደግሞ ብዙዎች ፣ በተለይ የሙስሊም ሀገራት ተወላጆች  ዩኤስ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ ሕግ የፈረሙበት ርምጃቸው በአፍሪቃ ብርቱ ቁጣን ቀስቅሶም ነበር።  ቁጣ ከታየባቸዉ ሃገራት መካከል ሶማልያ ቀዳሚዋ ነች። በዚህ ህግ ብቻ መጓዝ ያልቻሉት እና በኬንያ  ነዋሪ የሆኑት በየተራ አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል።     
«በአሜሪካ የታየዉ ነገር ጥሩ አልነበረም። ክስተቱ የአሜሪካ ዴሞክራሲ በሚባላዉ ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ ጥቃት ነበር። የጉዳዩ ሶማልያን ከገደላት የፊደራሊዝም አካሄድ ትንሽ ቢያንስ ነዉ። ማለትም የአሜሪካ መለያ ምልክት ነዉ የሚባለዉ ዴሞክራሲዋ እራስዋ  አሜሪካን እየገደላት ነዉ። ለተፈጠረዉ ቀዉስ ሁሉ ትራምፕ ሃላፊነቱን መዉሰድ አለበት። መልስ መስጠት አለበት»     
« በዋሽንግተን ያየነዉ ነገር እንደ አሜሪካ ካለች ልዕለ ኃያል ከተባለች እና ከበለፀገች ሃገር የሚጠበቅ አይደለም።» 
የባራክ ኦባማ ዘር ግንድ ከሚመዘዝበት ከኬንያ የመጡት የናይሮቢ ነዋሪ በበኩላቸዉ አሜሪካ ሁሉ ነገር ጥንቃቄ የተሞላበት አድርገዉ ይገምቱ ነበር። «አብዛኞቻችን የአሜሪካ ዴሞክራሲ ተቋማት ስራቸዉን በጥንቃቄ የሚሰሩና ፍፁም ናቸዉ ብለዉ ያሰቡ ነበር ። ነገር ግን በዋሽንግተን የነበረዉን ክስተት ካየን በኋላ ነገሩ እንደዛ አለመሆኑን ተረድተናል። » 
ዩጋንዳዊትዋ አስተያየት ሰጭ በበኩልዋ፤ ትራምፕ ይሰሩት የነበረዉን ስራ አይተን ከበፊቱ እንዲህ አይነት ነገር ሊከሰት ይችላል ብለን መገመት ነበረብን ባይ ናት።
« በእርግጥ በዋሽንግተን የተከሰተዉ ነገር እንደሚመጣ እያየነዉ የነበረ ጉዳይ በመሆኑ ማንኛችንም አሜሪካ ስለሆነዉ ነገር ልንደነቅ አይገባም። ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከወራቶች ጀምሮ ፀባዩ ወጣ ያለና በጣም የሚገርም አይነት ሆኖ አይተነዋል። ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ተሸንፎአል ። ይሁንና ምርጫዉን አልተሸነፍኩም እንደዉም ተጭበርብርያለሁ በማለት ዉጤቱን እንደማይቀበል እና የምርጫዉ  አሸናፊ እንደሆነ ነበር  ሲናገር ነዉ የከረመዉ።   
አሜሪካ እንደተባለላት የዴሞክራሲ ቁንጮ አይደለችም የሚሉ አፍሪቃዉያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ምዕራባዉያን ሃገሮች የሚናገሩት ነዉ። በተለይ በተለይ በትራም ዘመነ ስልጣን ።  
« እርግጥ በምርጫ የተሸነፉት ፕሬዚዳንቱ ስልጣኑን አለስረክብም ማለታቸዉ አልያም ሽንፈቴን አልቀበልም ማለታቸዉ የአሜሪካን ዴሞክራሲ ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ ነዉ?   
በዩጋንዳ ነዋሪ የሆነዉ ጎልማሳ ትራምፕ በሃገራቸዉ የቀሰቀሱት የመከፋፈል ፖለቲካ ለሌላዉ ዓለም እንዳይተርፍ ስጋት አለዉ። 
« በዓለም ዙርያ የሚገኙ ፀረ ዲሞክራሲ ሃይሎች በዩናይትድ ስቴትስ የታየዉን ያልተገባ ግጭት ቀስቃሽ ድርጊት መጠቀምያ በማድረግ የዴሞክራሲ ርምጃን ችላ እንዳይሉ ያሰጋል። በዩናትድ ስቴትስ የታየዉ የጥላቻ እና የግችት ወጀብ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለተቀረዉ ዓለም አደጋ አለዉ።    
በአሜሪካዉያን ዘንድ ትልቅ ክብርና ጥንቃቄ የሚሰጠዉ የአሜሪካ የሁለቱ ምክር ቤቶች ሕንጻ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መወረሩ ከአሜሪካ የማይጠበቅ የተባለዉን  ክስተት በቴሌቭዥን መስኮት የተከታተሉ አፍሪቃዉያን ይጠይቃሉ፤ፕሬዚዳንት ትራምፕ አህን በፀያፍ ቃል የሚጠራዉ ማን ነዉ? 
ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ በሰጠዉ ሁለተኛ አስተያየት የጽንፈኝነት መጨረሻዉ ይሄ ነዉ ሲል የዋሽንግተኑን ክስተት በምሳሌ ያነሳል። የጽንፈኝነት ፤ የአንድ ቡድን አመለካከት ሌሎችን የመደፍጠጥ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን አያመጣም። ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እናጋብዛለን!  

USA Mural von Donald Trump in New York
ምስል picture alliance/dpa/abaca/D. Van Tine
Cartoon Toonpool | Trump vs Biden
ምስል Bernd Pohlenz/toonpool

አዜብ ታደሰ 


ነጋሽ መሐመድ