1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2009

የኢትዮጵያ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመኾን በጽ/ቤቱ ያደረጉት ጥያቄ እና መልስ፣ የአትሌት ምሩጽ ይፍጠር የጤንነት ኹኔታ፣ የዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ኾነው መመረጥ በስፋት አነጋጋግሯል።

https://p.dw.com/p/2SZMr
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከኾኑ ነጥቦች መካከል አራት ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል። የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኾኖ መመረጥ አንደኛው ርእስ ነው። 

የኢትዮጵያ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመኾን በጽ/ቤቱ ያደረጉት ጥያቄ እና መልስ ሌላኛው መነጋገሪያ ነበር። የአትሌት ምሩጽ ይፍጠር የጤንነት ኹኔታን በተመለከተ የቀረቡ ዘገባዎችም አነጋጋሪ ኾነዋል።

የዶናልድ ትራምፕ ባልተጠበቀ መልኩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ኾነው መመረጥ በስፋት አነጋጋግሯል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመኾን መመረጡ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ኾነው ከቆዩ ጉዳዮች አንዱ ነበር። ዘካርያስ ዘላለም በትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በርካት ጉዳዮች ተቆልለው ይጠብቁታል። ከእነዚያም መካከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተንሰራፋው ሙስና እና አትሌቶችን ስልታዊ በኾነ መልኩ መበደል ይገኝበታል። ከእንግዲህ ቀልድ እና ጨዋታ የለም» ሲል አስነብቧል። 
  
ሰማኸኝ ጋሹ አበበ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምርጫን በፌስቡክ ገጹ እንደሚከተለው ተችቷል። «የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት አድርጎ መርጦታል። ግለሰቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝባዊ ትግሉ ላይ የሚሰጣቸዉ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት ከስርአቱ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አንዳለዉ ነዉ። እንዲመረጥ ያስደረገዉም ይህ ለስርአቱ ያለዉ ድጋፍ ነዉ» ሲል ጽፏል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture alliance/ZB/Pedersen

ሰማኸኝ በመቀጠል ጽሑፉን ሲያብራራ፦ «ስርአቱ ከደረሰበት የፖለቲካ ኪሳራ ለመዉጣት እንዲህ አይነት ቁማር መጫወቱ የሚጠበቅ ነዉ። ምንም እንኳ ኃይሌ በአትሌቲክስ መስክ ያበረከተዉ አስተዋፅኦ ታሪካዊ ቢሆንም ከሕዝባችን መከራ አንፃር እሱም ቢሆን በአሁኑ ሰአት አንድ የምንታገለዉ እንጂ የምናጨበጭብለት ሰዉ አይደለም» በማለት ጽሑፉን አጠቃሏል። 

ፍስሀ ተገኝ ደግሞ በትዊተር ገጹ፥ «ገብረ-እግዚአብሔር ገብረ-ማርያም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነው። ፌዴሬሽኑ በቀድሞ ታላቅ አትሌቶች በመመራት የባየር ሙይንሽንን ሞዴል እየተከተለ ነው» ብሏል። 

የኢትዮጵያ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ቦታ ለመሾም እንደ ሌሎቹ ዕጩዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረበላቸውን አንዳንድ ጥያቄዎች  እንዲብራራላቸው ደጋግመው መጠየቃቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ከተሰራጨ በኋላ በስፋት መነጋገሪያ ኾኖ ነበር።  

 ናታሊ አሚዮት በትዊተር ቀጣዩን ባስነበበችው መልእክቷ፦ «ንጉሡ እርቃኑን ነው። ዶ/ር ቴድሮስ በግልጽ የሕወሃት ተጨማሪ ማጭበርበር እና ሐፍረት ነው» ብላለች።
ዳንኤል ብርሐኔ በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን መልእክት አስፍሯል። «ባለፈው ግዜ አባዱላ ከግብጽ ሚዲያ ጋር ያደረገውን ቃለ-መጠየቅ ቆራርጠው ሙድ ሲይዙ የነበሩ ሰዎች፤ ዛሬም የቴድሮስን ቪዲዮ ቆራርጠው ራሳቸውን እያስደሰቱ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር እነዚህ ሰዎች አሜሪካ እየኖሩ ለመግባቢያ የምትሆን እንግሊዝኛ መልመድ አቅቷቸው፤ ወይ ሀበሻ ድርጅት ውስጥ ነው የሚቀጠሩት አልያም በመንግስት ድጎማ ነው የሚኖሩት፡፡ የትራምፕ ደጋፊዎች እነዚህን ነው ‹ሰለቹን!› ያሏቸው» ብሏል።

እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል ግሎባል ቮይስ በተባለ ድረ-ገጽ ላይ ያሰፈረውን ዘለግ ያለ ጽሑፍ ትዊተር ገጹ ላይ አካፍሏል። ጽሑፉ «ይቅርታ፤ ጥያቄው ግልጽ አይደለም፤ ሊያብራሩት ይችላሉ?» የሚለውን የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጥያቄ እና አወያዩ ጥያቄውን በድጋሚ ለማብራራት መሞከራቸው የሚያሳፍር መኾኑን አካቷል። በኦሬገን ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የ4ኛ ዓመት ዶክትሬት ተማሪው እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል  በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የዶ/ር አድሃኖም ንግግርን በተመለከተ ሦስት ነገሮች በስፋት መወያያ እንደነበሩ አብራርቷል።

Symbolfoto Terrorismus und Social media
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Vucci

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ድረ-ገጽ አድራሻ የያዘ ዜና ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን፣ 2009 ዓም ኢንተርኔት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ዜናው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ ሲኾን፦ «ዕውቁ የኢትዮጵያ አትሌት ምሩጽ ይፍጠር አርፏል» ይላል። ዜናውን ከኢንተርኔት በዝርዝር ለማንበብ ግን አይቻልም። «በቅድሚያም ዜና ረፍት» ሲል የሚንደረደረው የስፖርት ዜና ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ድረ-ገጽ እንደተሰረዘ የሚያመለክተው «የተፈለገው መረጃ አልተገኘም» የሚል መልእክትም ይነበባል። 

አጥናፍ ብርሐኔ በትዊተር ገጹ «የመንግሥት መገናኛ አውታሮች በረዥም ርቀት ታዋቂው አትሌት ምሩጽ ይፍጠር አርፏል በማለት ሰዉን አሳስተዋል» ሲል ጽፏል።
እሸቱ ሆማ ቄኖ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዜና እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን አርማዎች ስር የቀረቡ ማስተባበያዎችን ምስል በመቅረጽ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፉ፦ «ከመረጃ ምንጫችን ስህተት በሚል ገልፀውታል» ሲል አስነብቧል።  እሸቱ ከጽሑፍ ጋር ያያዘው የኢብኮ ማስተባበያ፦ «ማርሽ ቀያሪው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ተብሎ የተላለፈው ዜና ከመረጃ ምንጫችን ስህተት መሆኑን እየገለጽን በይፋ ይቅርታ እንጠይቃለን» በሚል ይነበባል።

ካሳሁን ይልማ ደግሞ በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን አስፍሯል። «ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ጀግና  ምሩጽ ይፍጠር በሕይወት አለ። ቶሮንቶ ሐኪም ቤት ነው የሚገኘው። በእርግጥ በጠና ታሟል። ጸልዩለት! እግዚአብሔር ይመስገን» ሲል ጽፏል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Lei

አብይ ተክለማርያም የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ሒደት እና ውጤት እንዲሁም ቀደም ሲል ይሰጡ የነበሩ የፖለቲካ ትንታኔዎች መጣረስን በተመለከተ አጭር መልእክት ትዊተር ላይ አስፍሯል። የአብይ አጠር ያለው ስላቃዊ ጽሑፉ፦ «የፖለቲካ ትንታኔ ነፍስሽን በሠላም ያሳርፈው» የሚል ነው። 

ዘላለም ክብረት በትዊተር ገጹ የሪፐብሊካኖች ፓርቲ መለያ የኾነውን ቀይ ቀለም ከኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በማነጻጸር አጠር ያለ መልእክት አስተላልፏል። የምርጫ መዘርዝር ውጤቱን ለማሳየት የቀረበው የዩናይትድ ስቴትስ ካርታን በስፋት አልብሶ የሚታየው ቀይ ቀለም ሪፐብሊካኖች በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስፋት ማሸነፋቸውን ያመለክታል።  «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀይ ዞን» ከሚል ጽሑፍ ጋር በቀይ ቀለም የተዋጠ የኢትዮጵያ ካርታም ከጎኑ ሰፍሯል። ዘላለም፦ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከኢትዮጵያ ካርታ ጋር ያያዘው አጭር ጽሑፍ «ቀይ በቀይ የሆነ ጊዜ» ይላል። ጽሑፉ በሳቅ በሚያነባ ምስል ነው የተቋጨው።  

በረዥም ርቀት የሩጫ ውድድር በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ስም በተደጋጋሚ ያስጠራው አንጋፋው አትሌት ምሩጽ ይፍጠርን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዥታን የፈጠረ አስተያየት ሲንሸራሸር ቆይቷል። የብዥታው ምንጭ የመንግሥት መገናኛ አውታሮች ዘገባ እንደኾነ ብዙዎች ጽፈዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ