1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከንግሥቲቱ በኋላ የኮመንዌልዝ ጥያቄና የብሪታንያና የጀርመን ትስስር

ሐሙስ፣ መስከረም 12 2015

ዚምባቤ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀች የመጨረሻዋ አፍሪቃ ሃገር ናት። የእዚያን ጊዜዉ ዌልስ ልዑል ቻርልስ የአዲሲትዋን ዚምባቤ ሉዓላዊነት በይፋ ለሮበርት ሙጋቤ ለማስረከብ በአካል ሃራሪ ተገኝተዉ ነበር። ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ በ70 ዓመት የግዛት ዘመናቸዉ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወደ 40 ለሚጠጉ አካባቢዎች ሉዓላዊነታቸዉን መልሰዋል።

https://p.dw.com/p/4HBqj
Simbabe Besuch Prinz Charles anlässlich Vereidigung Mugabe
ምስል picture alliance/AP Photo

-የብሪታንያ ንጉሳዊ ቤተሰብና የጀርመናዉያን ታሪክ-ከንግስቲቱ ሞት በኃላ በቅኝ ግዛት ሃገሮች የተቀሰቀሰዉ ጥያቄ-ንጉስ ቻርልስ ሳልሣዊ ንግሥናዉን ይወጡት ይሆን?

« ንግሥት ኤልሳቤጥ ጃንሆይ ወደ ጀርመን በመጡ በአስረኛዉ ዓመት ላይ ነዉ የመጡት። ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ በጎርጎረሳዉያን ዓም ወደ ጀርመን የመጡትና ሃገሪቱን የጎበኙት የመጀመርያዉ ርዕሰ ብሔር ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ናቸዉ።»   

የጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የታሪክ ምሁርና በጀርመን ታዋቂ ደራሲ የሆኑት ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደዉን ነበር። ከሰባ ዓመታት በላይ በንግሥና የቆዩት እና ግዙፍ ታሪክን ይዘዉ የነበሩት የታላቅዋ ብሪታንያ የዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈፀመ፤ የአዉሮጳን ግዙፍ ታሪክ ይዘዉ የቆዩት ንግሥት ማህደርም ተዘጋ ተብሎላቸዋል፤ ኤልሳቤጥ።  

Rom Beerdigung des Papstes: Mugabe steht neben Prinz Charles
ምስል AP

ጥያቄዉ አሁን በንግሥቲቱ እግር የተተኩት ልጃቸዉ ንጉስ ቻርልስ ሳልሣዊ የእናታቸዉን የንግሥት ኤልሳቤጥን ያህል ተቀባይነት እና ግርማ ሞገስ ያገኛሉ ወይ የሚለዉ ሆንዋል። በአፍሪቃም ቢሆን የብሪታንያ ንግሥት ዳግማዊ ኤልሳቤጥ ሞትን ተከትሎ በቀደሙት የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሃገሮች፤ የብሪታንያ ንጉሣዊ ውርሶች ላይ ውይይትን ቀስቅሶዋል።  መነጋገርያ ከሆኑት ነጥቦች መካከል በአፍሪቃ ሃገራት አሁንም በብሪታንያ ነገሥታት ስሞች የሚጠሩት ተቋማት፤ ጎዳናዎች እና የቦታዎች ስሞች ይገኙበታል። ይሁንና ተቋማቱም ሆነ የጎዳናዎቹ መጠርያ ስማቸዉን ያገኙት በዳግማዊት ንግሥስት ኤልሳቤጥ አባት እና አያት ዘመን ነበር።  

በናይሮቢ ጂቫንጂ ጋርደን የሚባል መዝናኛ ቦታ ላይ ቆሞ የነበረ የብሪታንያ ንግሥት ቪክቶሪያ ከአንገት በላይ ሐውልት በጎርጎረሳዉያኑ 2015 በጉልበተኞች ተቆርጦ በከተጣለ ወዲህ ቦታዉ በድንጋይ አጥር ተከቦ ባዶዉን ቀርቷል። በርግጥ ጉልበተኞች የተባሉት የቅኝ ግዛት አሳዛኝ ዘመንን ላለማስታወስ የፈፀሙት እንደሆኑ ይታመናልም ተብሏል። የንግሥት ቪክቶርያ ስም አሁንም ድረስ፤ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ ከሚካፈሉት ሐይቅ ጋር የተያያዘ ነዉ፤ቪክቶርያ ሐይቅ።  ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ከሞቱ በኋላ በጋራ ብልፅግና ማለትም በኮመንዌልዝ ሃገራት መካከል የንጉሳዊዉ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለዉጥ ወይም ተሃድሶ ይመጣ ይሆን?   ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ እንደሚሉት ጊዜዉ ሲመጣ ሁሉም መልስ ያገኛል። 

London Begräbnis King Edward VII 9 Könige
ምስል Ann Ronan Picture Library/picture alliance

«እሱ ትክክል ነዉ ጊዜ ሲመጣ ሁሉም መልስ ያገኛል ንግሥቲቱ የ 14 ሃገራት ርዕሰ ብሔር ነበሩ። እንደ ጃማይካ አይነቶቹ ሃገሮች ርዕሰ ብሔርነትን እንደማይቀበሉ ፤ ኮመንዌልዙን ሳይቀበሉ ነገር ግን የራሳቸዉን ርዕሰ ብሔር መሾም እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። እንደ አዉስትራልያ አይነቱም ሃገር ንግሥቲቱን ወይም የአሁኑን ንጉስ ርዕሰ ብሔርነት አንቀበልም ያሉ አሉ። እና እሱ የማይቀር ነዉ ግን የምናየዉ የሆናል። አንዳንዶቹ ግን አሁን ለምሳሌ ኬንያን ያየን እንደሆነ ያሳየችዉ ርምጃ የሚያስደንቅ ነገር ነዉ። የንግሥቲቱ ሞት እንደተሰማ ሃገሪቱ ከሌሎች ሃገር ሁሉ ቀደም ብላ የሦስት ቀን የሐዘን ጊዜ አዉጃለች። የመንግሥት ሐዘን ማለት ነዉ።»

ኬንያ፤ ዩጋንዳ፤ ታንዛንያ፤ ዚምባቤ እና ማላዊ ዉስጥ ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ አሁንም ድረስ የብሪታንያ ንጉሣዊ ቤተሰብ የያዝዋቸዉ ስሞች በሰፊው ሲሰጡ ይታያል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን እነዚህ የአፍሪቃ ሃገራትን ጨምሮ ሌሎች የእንጊሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ሃገራት ቪክቶሪያ፣ አንድሩስ እና ኤድዋርድስ ሲሉ የሰጥዋቸዉን የጎዳናም ሆነ የተቋም ስሞች በአፍሪቃ ጀግኖች ስም ለመተካት እንቅስቃሴን ጀምረዋል። በኬንያ ቻርልስ፤ ኤድዋርድ፤ አንድሬዉ እና ዲያና የሚባሉ ስሞች እጅግ በርካታ ቢሆኑም በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ዓ.ም ቪክቶርያ ጎዳና በመባል የሚታወቀዉ ናይሮቢ ዉስጥ ያለ መንገድ፤ በሃገሪዉ ጀግና ስም በቶም ቢያ ተተክቷል። ቶም ቢያ ጎዳና። 

ሌላዉ የኮመን ዌልዝ አባል ሃገራት በመገበያያ ገንዘባቸዉ ላይ ያስቀመጡትን  የንግሥቲቱ ፎቶ ማለት ምስል በሃገራቸዉ በሚገኝ ታዋቂ ሰዉ ለመቀየርም ጥሪ መቅረቡ ነዉ። ለምሳሌ አዉስትራልያን መጥቀስ ይቻላል። ይሄስ እንዴት ይታይ ይሆን? ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ እንደሚሉት ገንዘብ ላይ የንግሥቲቱ ምስል የተደረገዉ የበላይ ጠባቂ ርዕሰ ብሔር በመሆናቸዉ ነዉ። ንግሥቲቱ የበላይ ጠባቂ በሆኑባቸዉ አስራ አራት ሃገራት ዉስጥ ሕግ የሚወጣዉ በንግሥቲቱ ስም ነዉ። ለዚህም ነዉ የሳቸዉ ምስል በመገበያያ ገንዘብ የተደረገዉ። ንግሥቱቱ ከሞቱም በኋላ ገንዘቡ ላይ የተቀመጠዉ ምስላቸዉ ሊቀየር ይችላል ላይቀየርም ይችላል። ግን ጊዜ ይፈጃል ። ዉይይት ተደርጎበት ሕግ ረቆ ነዉ የሚከናወነዉ።»

ከዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ሞት በኋላ በታላቅዋ ብሪታንያ ንጉሳዊዉ አስተዳደር ተሃድሶ ወይም ለዉጥ ሊመጣ ይችል ይሆን? «ምንም ለዉጥ አይመጣም በብሪታንያ በንጉሳዊ አስተዳደር እና በፖለቲካ መካከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም። ይህ የተወሰ,ዉ ከ 300 ዓመት በፊት ጀምሮ ነዉ። ስለዚህ ምንም አይነት ለዉጥ አይመጣም ። እንጊሊዞች የንጉሳዊዉን አስተዳደር የሚወዱት የሚኮሩበት ነገር ነዉ።»

Queen Eilzabeth II, Staatsbegräbnis
ምስል Marco Bertorello/AFP

50 በመቶ የሚሆነዉ የጀርመን ህዝብ የብሪታንያን ንጉሣዊ ቤተሰብ ደጋፊ አድናቂ እንደሆን ተዘግቧል። የንግሥቲቱ ሞት እንደተሰማ በርካታ ዜጎች ሐዘናቸዉን ለመግለፅ እዚህ ጀርመን በርሊን ወደሚገኘዉ ወደ እንጊሊዝ ኤንባሴተመዋል። የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላቭ ሾልዝ ሐዘናቸዉን የገለፁት የንግሥቲቱን ተግባር በማሞገስ ነዉ።  «የብሪታኒያዋ ንግሥት የዳግማዊ ኤልሳቤጥ ሞት ሁላችንንም አሳዝኖናል። ሐዘኑ በዓለም ዙርያ ህዝብም ዘንድ ታይቷል። ለንደን ውስጥ በቢኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ፊት ለፊት እንዲሁም፤ ጀርመን በርሊን ላይ ብሪታንያ ኤንባሲ ፊት ለፊት ህዝቡ ለሐዘን መግለጫ ያስቀመጠዉ ሻማና እቅፍ አበባ ዳግማዊ ንግሥት ኤልሳቤጥ በብዙ ዜጎች ልብ ውስጥ በመልካም መንፈስ እንደተቀመጡ የሚያረጋግጥ ነዉ። »

መራሄ መንግስት ኦላቭ ሾልዝ ንግሥቲቱ በብሪታንያ እና በጀርመን መካከል የነበረዉ ቅራኔ እንዲፈታ ያደረጉ ፤ የአዉሮጳ መሰረት የሆነዉን ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነትን አንግበዉ የተጓዙ ነበሩ።  ጀርመን የእንግሊዝ ህዝብን ሐዘኑ ተካፋይ ነዉም ሲሉ ተናግረዋል።    

«ብሪታንያ የመቶ ዓመት ህያዉ ምስክር የነበሩትን ንግሥቷን አጥታለች ። ንግሥናቸዉ ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት ዘልቋል። ንግሥቲቱ በአዉሮጳ ከሁሉ የተሻለውን የአውሮጳ ቅርሳችንን ማለትም ዲሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በማሳየት አልፈዋል። ንግስቲቱ ያደረጉት በርካታ ነገሮችን ጨምሮ የቀድሞ ተቀናቃኝ እና ጦርነት ዉስጥ የነበሩት ታላቋ ብሪታኒያ እና ጀርመን መታረቅ ይችላሉ ሲሉ አቋማቸዉን ያሳዩም ነበሩ። ጀርመንን ለበርካታ ጊዜያት መጎብኘታቸዉ እና ጥሩ እና ልዩ ለሆነዉ አቋማቸዉ እና ቅርበታቸዉ አሁንም በብዙ ዜጎች ዘንድ በጥሩ ይታሰባሉ።»

Königin Elizabeth II. Staatsbesuch in Deutschland 1965
ምስል picture-alliance/dpa/J. Philipp

የጀርመኑ መራሔ መንግሥት በመጨረሻ በንግስቲቱ እግር የተተኩትን ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊን የሰመረ የንግሥና ዘመን እንዲሆንላቸዉ ተመኝተዋል። የጀርመናዉያኑና እና የንግሥቲቱ ወዳጅነት በታሪክ ምሁሩ በልዑል ዶ/ር አስፋወሰን አስራተ ዓይን እንዴት ይታይ ይሆን?  የጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የታሪክ ምሁርና በጀርመን ታዋቂ ደራሲ የሆኑት ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ለእነዚህ እና ታላቅዋ ብሪታንያ እና ጀርመን ያላቸዉን ጥንታዊ ግንኙነት እና የደም ትስስር በሰፊዉ አጫዉተዉናል።

ዚምባቤ በጎርጎረሳዉያኑ 1980 ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀች የመጨረሻዋ አፍሪቃ ሃገር ስትሆን በወቅቱ የዌልስ ልዑል የነበሩት ቻርልስ የዛሬዉን ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ የአዲሲትዋን ዚምባቤ ሉዓላዊነት በይፋ ለሮበርት ሙጋቤ ለማስረከብ በአካል ሃራሪ ተገኝተዉ ነበር። የቻርልስ እናት ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ በ70 ዓመት የግዛት ዘመናቸዉ በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወደ 40 ለሚጠጉ አካባቢዎች የሉዓላዊነት ወረቀትን ፈርመዉ ለየሃገራቱ መሪዎች ማስረከባቸዉ የታሪክ ማህደራቸዉ ያሳያል። የታላቅዋ ብሪታንያ ንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት የቀብር ሥነ-ስርዓት ከዓለም የተሰባሰቡ መንግሥታትና የመንግሥታት ተጠሪዎች ንጉሳዉያን ቤተሰቦች በተገኙበት የሽኝት ፀሎት ሥነ-ስርዓትን በማስቀደም ተከናዉኗል።  የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ አስክሬን ባለፈዉ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩት ከባለቤታቸዉ ንጉሥ ፊሊፕ ጎን በዊንድሶር ቤተመንግሥት አርፏል። በቀብር ሥነስርዓቱ ላይ ቅር ቤተ-ዘመዶቻቸዉ ብቻ እንደተገኙ ተዘግቧል።  

Großbritannien | Tod Queen Elizabeth | Staatsbegräbnis
ምስል Gareth Cattermole/Getty Images

ሙሉዉን ዝግጅት ለማዳመጥ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን ይጫኑ ! 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ