1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከችግር ያልተላቀቁት የአበርገሌ ወረዳ አካባቢዎች

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2015

ከሁለት ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ የነበሩ የአበርገሌ ወረዳ አካባቢዎች አሁንም አብዛኛዎቹ ነፃ ባለመውጣታቸው የግብርና ሥራዎችን ማገዝ እንዳልተቻለ የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች አመለከቱ። በ2014/15 የእርሻ ወቅት በአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ አልታረሰም።

https://p.dw.com/p/4TS8Y
Äthiopien | Teile der Amhara-Region nun unter Kontrolle der Regierung
ምስል Waghemra Communication office

«ብዙዎች ለወባ በሽታ ተዳርገዋል»

ከሁለት ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ የነበሩ የአበርገሌ ወረዳ አካባቢዎች አሁንም አብዛኛዎቹ ነፃ ባለመውጣታቸው የግብርና ሥራዎችን ማገዝ እንዳልተቻለ የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች አመለከቱ። በተለይ የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች በወባ እየተሰቃዩ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ነፃ የወጡ ቀበሌዎችም ቢሆን የእርሻ በሬዎቻቸው ታርደው የተበሉ በመሆኑ የአካባቢው አርሶ አደር አህያዎችን ጠምዶ እያረሰ ነው ተብሏል። በ2014/15 የእርሻ ወቅት በአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ አልታረሰም።

ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። በተለይ አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ከሁለት ዓመት በላይ በህወሓትና በአካባቢው ታጣቂዎች ስር ቆይተዋል። 70 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ቀያቸውን ለቅቀው ተፈናቅለው የነበሩ ናቸው።

ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ተፈናቀዮቹ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም በተለይ የአብዛኛዎቹ መኖሪያ ቀበሌዎች እስካሁን ነፃ ስላልሆኑ በርካታው ህዝብ ችግር ላይ እንደሆነ ነው የአበርገሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ መኳንንት የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት በወረዳው ከሚገኙ 17 ቀበሌዎች ውስጥ 12ቱ ነፃ አልወጡም። በተለይ በጦርነቱ ወቅት የእርሻ በሬዎቹ ታርደው በመበላታቸው እና በመዘረፋቸው፣ ነፃ በሆኑ ቀበሌዎች ያለው አርሶ አደር በአህያ ለማረስ እየተገደደ እንደሆነ ነው አቶ አበበ የሚናገሩት። ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አሁን ነፃ ወዳልወጡት አካባቢዎች መንቀሳቀስ ባለመቻሉ እዛ ያለው ህዝብ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንደማይታወቅም አብራርተዋል።

የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓለሙ ክፍሌ በበኩላቸው ወረዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት ያልተደረገበት በመሆኑ በአጠቃላይ የወረዳው ህዝብ ለወባ ህመም ተጋልጧል ብለዋል። ከሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮም አምስት ሰዎች በወባ መሞታቸውንም ገልጠዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወልዴ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በፃግብጂና በአበርገሌ ወረዳዎች ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳ እንዳልታረሰ ጠቁመው፣ አርሶ አደሩን ለማገዝ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ የወባ በሽታ ስርጭትን በተመለከተ ተጠይቀው፣ የአልጋ አጎበር ነፃ በወጡ ቀበሌዎች መሰራጨቱን ተናግረዋል። ነፃ ወዳልወጡ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ግን የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ወደዚያ መድረስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል። ወረዳው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት ባለመካሄዱ ከፍተኛ ስጋት እንዳለም አመልክተዋል። ከአበርገሌ በተጨማሪ ዝቋላና ሳህላ የተባሉ ወረዳዎችም ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው ወረዳዎች እንደሆኑም አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም የወባ መርሃግብር አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለወረዳው በቂ የአልጋ አጎበር እንደተላከ ጠቁመው፣ የኬሚካል ርጭትን በተመለከተ ጥያቄው ለፌደራል መንግሥት ጤና ሚኒስቴር መላኩን ገልጸዋል። ምላሽ  እንደተገኘም ስርጭቱ ይካሄዳል ብለዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ