1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር 

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2013

በቱርክ በግራጫ ፓስፖርት እገዛ ቁጥራቸው ሦስት ሺህ የሚጠጋ ሰዎች ጀርመንና ጎረቤት ሃገራት ሄደው ተሰውረው ይኖራሉ።መጀመሪያ ከጀርመን የግብዣ ደብዳቤ ይመጣል። ለማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ለተዘጋጀ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት እንዲካፈሉ አለያም ለባህል ልውውጥ በሚል ሰዎቹ ይጋበዛሉ። ዐውደ ጥናቱምም ሆነ የባህል ልውውጥ ፈጽሞ አይካሄዱም።

https://p.dw.com/p/3sxan
Menschenschmuggel Thailand Bangladesch Archiv 11.06.2014
ምስል Reuters/Bangladesh Coast Guard

ከቱርክ ወደ ጀርመን የሚካሄድ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቱርክ ወደ ጀርመን በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ የቱርክ ዜጎችን ጉዳይ የቱርክም የጀርመን ባለሥልጣናትም ምርመራ እያካሄዱበት መሆኑን ተናግረዋል። በቱርክ ባለሥልጣናት እገዛ ጀርመን በሕገ ወጥ መንገድ መግባታቸው ከተገለጸው ከነዚሁ ሰዎች አንዳንዶቹ የመሰወራቸው ምስጢር ማነጋገሩ ቀጥሏል። 
በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ከሀገር ወደ ሃገር ማሻገር፣በወንጀሉ የተሰማሩ፣በብዙ ቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ የሚያጋብሱበት ንግድ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።ሕገ ወጥ አሻጋሪዎች ሰዎችን ለከፋ አደጋ አጋልጠው በየብስ በባህርና በአየር ከአንዱ ሃገር ወደሌላው ሲያዘዋውሩ ሕይወታቸው የሚያልፍ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸውም ጥቂት አይደሉም።በዚህ መንገድ ወደ ተለያየ ሃገር የመግባት እድሉ ከገጠማቸውም፣ ለተለያዩ የስነ ልቦና ችግሮች የሚዳረጉ ብዙዎች ናቸው። እነዚህን  ችግሮች የሚያስከትለውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት የአውሮጳ መንግሥታት በተናጠልም ሆነ በጋራ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸው አልቀረም።ችግሩ ከሌሎች ከባድና የተደራጁ ወንጀሎች ጋር የተያያዘ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ በፍጥነት እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ያስገነዝባል። የአውሮጳ ኅብረት ችግሩን ለመከላከል  ከጎርጎሮሳዊው 2015 እስከ 2020 ባወጣው የድርጊት መርሃ ግብር ካካተቻቸው መካከል  የተጠናከረ የፖሊስና የፍትህ አካላት ሥራ ፣ከአባል ሃገራት ጋር መረጃ መለዋወጥ እንዲሁም የኅብረቱ አባል ካልሆኑትም ጋር ተባብሮ መስራት ይገኙበታል።እነዚህ  ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ ቢሆንም አሁንም ይህ ወንጀል በተለያየ የዓለም ክፍል መፈጸሙ ቀጥሏል።እዚህ ጀርመንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሕገ ወጥ መንገድ ከቱርክ ወደ ጀርመን የሚገቡ ሰዎች ጉዳይ  እያነጋገረ ነው።ሰዎቹ ጀርመን የገቡት በቱርክ ባለሥልጣናት እገዛ ነው መባሉ ደግሞ ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርመራዎች መሠረት በርካታ የቱርክ ዜጎች በባለሥልጣናቱ እርዳታ ጀርመን ገብተዋል።ይህ የሚሳካላቸውም የቱርክ ባለሥልጣናት በሚሰጧቸው የተለየ ፓስፖርት አማካይነት ነው።እዚህ ከገቡ በኋላ ደግሞ ይሸሸጋሉ።የቱርክ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደራጁ የሰዎች አሻጋሪዎች ይፈጸማል የተባለውን ይህን ወንጀል በማጣራት ላይ መሆኑን አስታውቋል።የጀርመን የፍትህ ስርዓትም ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ገልጿል። ግራጫ ቀለም ያለው ድብቁ የቱርክ ፓስፖርት ለሕገ ወጦች ድንበር እያስከፈተላቸው ነው።በመሠረቱ ይህኛው ፓስፖርት የሚሰጠው ለይፋ የሥራ ጉዳይ ከቱርክ ወደሌላ ሃገር ለሚሄዱ ዜጎች ነው።ይሁንና ይህን ፓስፖርት በመጠቀም ቢያንስ 43 ሰዎች ባለፈው ህዳር በህገ ወጥ መንገድ ጀርመን መግባታቸው ተዘግቧል።ጉዳዩን የደረሰችበት ሃበርቱርክ ለተባለው የቱርክ ጋዜጣ የምትሰራው ጋዜጠኛ ሴቪሌይ ይልማን እንዳለችው የተፈጸመው በተደራጀ መንገድ የተካሄደ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ማሸጋገር ነው።ከትውልድ ስፍራዋ ከማላትያ ስለ ህገ ወጡ የሰዎች ማዘዋወር መረጃ ካገኘኘች በኋላ ነበር ምርመራውን የቀጠለችው።
« የተርብ ጎጆ ጥሼ የገባሁ ነው የሚመስለው።በምርመራው እንደታወቀው በማላታያ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በየሲልኮይ ማዘጋጃ ቤት የሆነው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በ43 ሰዎች ብቻ የተገደበ እንዳልነበረ በምርመራው ታውቋል።»
ከየሲልኮይ በስተምስራቅ ከምትገኘው ከቢንጎልም ወጣት ወንዶችና ሴቶች የሚያመዝኑባቸው ሌሎች ቱርኮችም በግራጫው ፓስፖርት ወደ ጀርመን ተጉዘዋል እንደ ጋዜጠኛ ይልማን።በዚህ አጋጣሚም የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪዎች በዚህ ሕገ ወጥ ዝውውር በተጠረጠሩ በርካታ የቱርክ ማዘጋጃ ቤቶች ላይ ዓይናቸውን መጣላቸው ተሰምቷል። በጋዜጠኛ ይልማን ግምት በቱርክ በግራጫ ፓስፖርት እገዛ ቁጥራቸው ሦስት ሺህ የሚጠጋ ሰዎች ጀርመንና ጎረቤት ሃገራት ሄደው ተሰውረው ይኖራሉ።ሂደቱም ሁሌም ተመሳሳይ ነው።መጀመሪያ ከጀርመን የግብዣ ደብዳቤ ይመጣል።ለምሳሌ ለማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ለተዘጋጀ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት እንዲካፈሉ አለያም ለባህል ልውውጥ በሚል ሰዎቹ ይጋበዛሉ።የሚገርመው ነገር የተባለው ዐውደ ጥናትም ሆነ የባህል ልውውጥ ፈጽሞ አይካሄዱም።እንደተባለው የግብዣዎቹ  ደብዳቤዎች የሚጻፉት በሰሜን ጀርመንዋ ከተማ ሃኖቨር እንደሚገኙ በተነገረው ኤርሲን ኬ በሚል ስም በሚጠሩ የቱርክ ዝርያ ባላቸው ጀርመናዊ ነው።እዚያ የአካባቢው አቃቤ ህግ ቶማስ ክሊንገ ፣ኤሪሰን ኬን የጀርመንን የመኖሪያ ፈቃድ ሕግ በመጣስ ክስ መስርተውባቸዋል።እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ዓይነት መንገድ ሰውዬው በላኩላቸው የግብዣ ደብዳቤ ጀርመን የሚገቡት እነዚህ ሰዎች ወዲያውኑ ይሰወራሉ።
«ተከሳሹ  ከአካባቢ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለተዘጋጀ ዐውደ ጥናት በይፋ ሰዎቹን ጋብዘዋል።ይሁንና እኛ እንደተረዳነው ግብዣው እውነት አይደለም።ቡድኑ ጀርመን ከገባ በኋላም ደግሞ ወዲያውኑ ተሰውራል።»
ክሊንገ እንደሚሉት ከመካከላቸው አምስቱ ጀርመን ተገን እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።የቀሩት አሁንም እንደተሸሸጉ ነው።ጋዜጠኛ ሴቪሌይ ከመካከላቸው አንዱን ማነጋገር ችላ ነበር። ግራጫ ቀለም ያለውን ፓስፖርት ይዞ ወደ ጀርመን የሚወስደው አውቶብስ ላይ ለመሳፈር ስድስት ሺህ ዩሮ መክፈሉን ነግሯታል። 
«በግንባታ ስራ ውስጥ በቀን ሠራተኝነት እንደሚተዳደር ተናግሯል። ጥሩ ገቢ እንዳለው ደስተኛና ባለው የሚረካም መሆኑን  ምክንያቱም ማንም ጀርመን ውስጥ ፓስፖርቱን እንዲያሳይ ስለማይጠየቅ ። ብሏል።»
ይኽው የአርባ ዓመቱ ቱርካዊ እንደተናገረው ግራጫው ፓስፖርት አውቶብስ ውስጥ እያሉ ተሰብስቦ ተወስዷል።ፊሊ አግባባ በምህጻሩ CHP የሚባለው ትልቁ የቱርክ ተቃዋሚ ፓርቲና የቱርክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው። እኚህ ፖለቲከኛ በቴሌቪዥን ሲናገሩ ቱርክ ውስጥ ተፈጽሟል በተባለው ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ የማሸጋገር ወንጀል የቱርክ ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት አምናለሁ ብለዋል።ይህንንም በጉዳዩ ላይ በተካሄደ ጥናት መረጋገጡን ነው የተናገሩት።
«እኛ ባካሄድነው ጥናት መሠረት የገዥው የAKP ፓርቲ አባል የሆኑት የቱርክዋ የቢንጎል ከተማ ከንቲባ ከጎርጎሮሳዊው 2014 እስከ 2019 ሰዎችን ከቱርክ ወደ ሌላ ሃገር የማሻገሩን ሥራ አደራጅተዋል። አዎ ጉዳዩ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው።
በቱርክዋ በኤላዝጊ ከተማ አቅራቢያ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ከንቲባ ለአንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት ማዘጋጃ ቤታቸው በፈቃደኝነት ለሚያደርገው ትብብር ምስጋና አንድ ያገለገለ ከባድ መኪና በስጦታ ተበርክቶላቸዋል።በቱርክ ከግራጫማው ፓስፖርት ጋር የተያያዙ ቅሌቶች ወደ ፖለቲካ ጉዳይነት ከፍ እያሉ ነው።የቱርክ ተቃዋሚዎች መንግሥት ጉዳዩን የሚያጣሩ ሰዎችን በገዥው ፓርቲ በAKP ወደሚመሩ ማዘጋጃ ቤቶች ሳይሆን ተቃዋሚዎች ወደሚመሯቸው የቱርክ ማዘጋጃ ቤቶች ይልካል ሲሉ ቅሩታቸውን ገልጸዋል።የገዥው ፓርቲ የAKP ቃል አቀባይ ኦማር ሴሊክ ግን ይህን ይቃወማሉ።
«የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁሉንም ነገር በሁሉም ቦታ ያጣራል።አጣርቶም ውጤቱን ለፍትህ አካላት ያስረክባል።እኛ ግልጽ ለሆነ ምርመራ ነው የምንቆመው። »
ከዚህ ቅሌት በኋላ የቱርክ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጊዜው ግራጫ ቀለም ያለውን ፓስፖርት መስጠት አቁሟል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚደረገው ጥረትም በአውሮጳ ኅብረት በኩል መቀጠሉን ነው ድርጅቱ የሚናገረው ።የእስካሁኖቹ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስገኘታቸውን ነው ኅብረቱ የሚገልጸው።ለዚህም የአውሮጳ ኅብረት ፖሊስ ድርጅት ዩሮፖል እና የኅብረቱ ድንበር ተቆጣጣሪ ፍሮንቴክስ ጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል።ኅብረቱ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የኅብረቱ አባል ያልሆኑ ሃገራትን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ለሚያደርጉትን ጥረት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍም ይሰጣል። ከድጋፎቹ ውስጥ ስለ ሕገ ወጥ ስደት አስከፊነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ፤እንዲሁም ለሕግ አስከባሪዎች የሚሰጡ ስልጠናዎች ይጠቀሳሉ።ይሁንና ኮሮና ዓለማችንን ካደረሰ በኋላ ሃገራት የአየር የየብስና የባህር ጉዞዎች ገደብ ቢጥሉም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አለመቆሙን ነው የአውሮጳ ኅብረት ፖሊስ ድርጅት ዩሮፖል ያስታወቀው።ለዚህም ምክንያት የተባለው የኮሮና ተኅዋሲን ሥርጭት ለመግታት መንግሥታት የጣሉት የእንቅስቃሴ እገዳ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ችግር ማስከተሉን መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። 

Deutschland Stephan Mayer
ምስል DW/N. Kreizer
Türkei Gönül Özel CHP Partei Diyarbakir
ምስል Felat Bozarslan/DW

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ