1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ሙቀት መጨመር ተጽእኖዎችና መከላከያው

ሰኞ፣ ነሐሴ 3 2013

የዓለም ሃገራት መሪዎች የዓለማችን ሙቀት ለመቀነስ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ ርምጃ ካልወሰዱ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ  አይችሉም ሲል የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ምክር ቤት (IPCC) ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አሳሰበ።

https://p.dw.com/p/3ylaN
USA Waldbrände in Kalifornien
ምስል Noah Berger/AP Photo/picture alliance

የዓለም ሙቀት መጨመር ያሳደረዉ ሥጋት

 

የዓለም ሃገራት መሪዎች የዓለማችን ሙቀት ለመቀነስ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ ርምጃ ካልወሰዱ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ  አይችሉም ሲል የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ምክር ቤት (IPCC) ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አሳሰበ። የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ጉዳይ ምክር ቤት በመግለጫዉ፤ በዓለም ላይ የካርቦን ብክለትን በመቀነስ አየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚደረገው ትግል በአፋጣኝ  ተግባራዊ ካልሆነ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ የዓለም ሙቀት መጠን እስከ 1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ማለትም እስከ (2.7 ዲግሪ ፋራናይት) ሊሻገር ይችላል ሲል አስጠንቅቆአል። በዓለም ዙርያ የሚታየዉ የሙቀት መጨመር ምክንያት ዓለም የያዘቻቸዉ የበረዶ ግግሮች እና ንጣፎች መቅለጥ ብሎም የባህር ይዘት ደረጃዎች መለዋወጥ ጉዳዩን፣ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ማድረሱን ድርጅቱ በመግለጫዉ አስታዉቆአል። የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ቁጥጥር ጉዳይ ቢሮ መግለጫ አሳሳቢ ነዉ ያሉት የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ፤ አዉሮጳ ዉስጥ 2030 እስከ 2050 የዓለማችንን የሙቀት መጠን ለመቀነስ የተደረሰዉ ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል። 

Waldbrände auf Sardinien
ምስል Vigili del Fuoco/REUTERS

« በጣም አሳሳቢ ዘገባ ነው። ነገሩን እንደገና በደንብ ማጥናት አለብን ፣ ግን የምናያቸዉ የመጀመሪያ ምልክቶች በጣም አስጨናቂ ናቸዉ። የአየር ንብረት ለውጥ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ እያየን ነዉ። ይህ ተፅእኖ በመጪዎቹ ጊዜያት ይበልጥ ጠንካራ እንደሚሆን አሁን እየተተነበየ ነዉ። ስለዚህ የዓለማችንን የሙቀት መጠን ለመቀነስ  ግቦቹ ላይ መድረሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ግቦች በ 2030 ለአውሮጳ የተቀመጡ ግቦች ሲሆኑ  በአውሮጳ ስምምነት መሰረት በ 2050 የተጣራ ዜሮ ይሙቀት መጠን ይሆናል ተብሎ ስምምነት ላይ ተደርሶአል።»

 የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዝ  “ራይንሼ ፖስት” ለተባለ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ደግሞ በሰው ሰራሽ ጉዳይ የአየር ንብረት ለውጥ መከሰቱ ምንም ጥርጣሬ የሌለዉ እና ብዙ ማስረጃም እንዳለ ተናግረዋል። የጀርመን የልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር በበበኩላቸዉ ታዳሽ ኃይልን በተመለከተ “ግዙፍ” የግል እና በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገራት ዓለም አቀፍ አረንጓዴ ስምምነት እንዲደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በአዉሮጳ ሃገራት የደረሰዉ የጎርፍ አደጋ እና እንዲም በስፔን በቱርክ እና ዩናይትድ ስቴትስ የቀጠለዉ ደን ቃጠሎ ፖለቲከኞች  እንዲሁም  የከባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት እንዲያጤኑት ሳይገፋፋ እንዳልቀረም ተነግሮአል። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም በአዉስትራልያ የቀደን ቃጠሎ በተደጋጋሚ የሚታይ ክስተት መሆኑም ይታወቃል።

Blick vom Fernsehturm Colonius in Köln
ምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopress/dpa/picture alliance

የሙቀት መጨመር ስላስከተላቸው ተጽእኖዎችና ክስተቶቹን መነሻ አድርጎ ስለተካሄደው ጥናት ይዘት የበርሊኑን ዘጋቢያችንን አነጋግረነዋል። 


ይልማ ኃይለ ሚካኤል


ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ