1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከበኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ወገኖች ሥጋት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 7 2012

ከሁለት ሳምንት በፊት በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በታጣቂዎች ደረሰ በተባለ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ እንደ ማይፈልጉ ተናገሩ።  በማንኩሽ  ከተማ  በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዩቹ ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ መንግስት ሌላ ቦታ እንዲያሰፍራቸውም ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/3gvV5
Assosa Town Äthiopien
ምስል DW/N. Dessalegn

በቂ እርዳታ እያገኘን አይደለም ብለዋል

ከሁለት ሳምንት በፊት በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በታጣቂዎች ደረሰ በተባለ ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ እንደ ማይፈልጉ ተናገሩ።  በማንኩሽ  ከተማ  በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዩቹ ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ መንግስት ሌላ ቦታ እንዲያሰፍራቸውም ጠይቀዋል።

 ከ136 በላይ የሚሆኑ ከጃዲያ ተፋናቅለው በማኩሽ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሌሎች ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች የሚሰጣቸው ድጋፍ አነስተኛ እንደሆነም አስታውቀዋል።  የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከሶስት ቀበሌዎች ለተፈናቀሉ 367 ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ዕርዳታ የመጀመሪያ ዙር ማዳረሱን አመልክቷል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ተፈናቃዩቹ አካባቢው እስኪረጋጋ ድረስ በመጠለያ እንዲቆዩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ  በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩት ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢዎች  የሚገኙ ዜጎች  ለችግር መጋለጣቸውን  ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰይድ መኮንን ከሁለት ሳምንት በበፊት ከጉባ ወረዳ ማንኩሽ ከተማ በ25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኝ ጃዲያ ቀበሌ በታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት ተፈናቅለው በማንኩሽ ከተማ በተዘጋጀው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንሚገኙ ገልጸዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢውያ መኖር ከጀመሩ ሁለት ከሳምንት በላይ የሆናቸው ሲሆን እስካሁን የተደረገላቸው ድጋፍ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡  አቶ እሸቱ ሀይሉም በተመሳሳይ  ከጃዲያ ተፈናቅለው በጉባ ወረዳ ማንኩሽ ከተማ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ የተፈናቀሉበት አካባቢው የጸጥታ ችግር አሳሳቢ በመሆኑ ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመመለስ እንደማይፈልጉም ተናግረዋል፡፡ የሚሰጡ እርዳታዎችም አነስተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን የምግብ ዋስትና በሚባል ተቋም በኩል አንድ ጊዜ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል፡፡ የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ተሲሳ በበኩላቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ የማድረስ ተግባር እያከናወኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ያረንጃና ጃዲያ በተባሉ ቀበሌዎች በደረሰው ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ  ባለፉት ሁለት ሳምንታት  በተፈጠሩ ግጭቶች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሰዋል፡፡ ከሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም አንስቶ በተለያዩ ቀናት በአካባቢው  ሁለት ጊዜ በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃትም የመንግስት ወታደሮችን ጨምሮ በጉባ ወረዳ  ከ20 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ በስልክ እንዳስታወቁት  በወረዳው የተለያዩ ስፋራዎች ሸማቂዎቹ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን ጃዲያ ከተባለና ሌሎችም ስፋራዎች ነዋሪው ከቤት ንብረቱ በዚሁ ምክንያት መፈናቀሉን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው እሁድ በጉባ ወረዳ ያረንጃ በተባለ ስፋራም ለስራ በመንቀሳቀስ ላይ በነበሩ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ላይ ያደፈጡ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን አብራርተዋል። ለስራ ሲንቀሳቀሱበት የነበረው መኪና ተገልብጦ አምስት  ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የአሽከርካሪው ህይወትም ማለፉን አክለዋል፡፡ ጥቃት አድርሰዋል ከተባሉ ሸማቂዎች መካከል  የተያዘ ሰው አለመኖሩንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ የሀገር መከላከያና የክልል ጸጥታ ሀይሎች ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ 

በጉባ ወረዳ ባለፈው ሐምሌ 20ቀን 22012 ዓ.ም ጃዲያ በተባለ ቀበሌ  ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 13 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ 121 ግለሰቦችንና ሲጠቀሙበት የነበሩትን የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
አዜብ ታደሰ