1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሞኑ፦ ግጭት በዩኒቨርስቲዎች፤ የአቃቤ ህግ መግለጫ

ዓርብ፣ ኅዳር 5 2012

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ግጭት እና እርሱን ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተከሰቱ ሁከቶች እና አለመረጋጋቶች የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች የሰሞኑ መወያያ ነበሩ። በወልዲያው ግጭት ሁለት ተማሪዎች ማጣታቸው ከተነገረ በኋላ በበርካታ ዩኒቨርስቲዎች መጠነኛ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ተስተውለዋል።

https://p.dw.com/p/3T7yX
Äthiopien Justizminister Berhanu Tsegaye
ምስል DW/E. B. Tekle

ከሰሞኑ፦ ግጭት በዩኒቨርስቲዎች፤ የአቃቤ ህግ መግለጫ

የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ግጭትን ተከትሎ በደምቢ ዶሎ፣ ወለጋ፣ መቱ፣ ጅማ፣ መደወላቡ፣ ድሬዳዋ፣ ወሎ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲዎች መጠነኛ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ተስተውለዋል። ዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ ያለው ሁኔታ ያሰጋቸው ተማሪዎች በእምነት ተቋማት እና በመሰብሰቢያ አዳራሾች ጭምር ለመጠለል ተገድደዋል። 

በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በወልዲያ የተፈጸመውን የተማሪዎች ግድያ አውግዘዋል። በወልዲያው ግጭት ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ሀዘናቸውን የገለጹት ጥላሁን ጽጌ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ መጪውንም ጊዜ በስጋት ተመልክተውታል። “በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ነፍስ ይማር። [ድርጊቱ] ያሳምማል። ዩኒቨርስቲዎቻችን ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ከሆነ ይህ ዓመት ያስፈራል። ከጥላቻ ሰባኪዎች ካዝና ተከፋይ የሆኑ ግጭት ቀስቃሾች እና ጠብ አጫሪዎች ይኖራሉ። ከባድ ጊዜ ነው” ብለዋል ጥላሁን። 

“በወልዲያ የተደረገው አሳፋሪ ነገር ነው” ሲሉ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት በድሉ ሌሊሳ በጸጥታ ማስከበር ረገድ ብዙዎች በተደጋጋሚ የሚያንጸባርቁትን ሀሳብ አጽንኦት ሰጥተዋል። በድሉ “በዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎችን ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው” ሲሉ መንግስት የጸጥታ ማስከበር ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ሚኪያስ ተስፋዬ ሙሉጌታ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የትዊተር አድራሻን በመጠቀም መንግስት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። “እንደምን ዋሉ ጌታዬ! እንደ ሌሎቹ የሀገሬ ዜጎች ሁሉ አስተዳደርዎ ብጥብጥ በሚፈጥሩ ሰዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ እጠይቃለሁ። የትግስት ጽዋው አልሞላም ወይ?” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዚያው በትዊተር ሰሊና የተባሉ ተጠቃሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተውላቸዋል። “ከአክብሮት ጋር! ትዕግስትዎ የሚያልቅበት ቀን እንደ ምጽአት ቀን ናፈቀኝ! አልበዛም ወይ?” ብለዋቸዋል። 

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኦዴፓ) የሚደግፉት ደረጀ ገረፋ ቱሉም “ቁልፉ ያለው መንግስት እጅ ነው” ከሚሉ ወገኖች ጋር ይስማማሉ። ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት አጭር ጽሁፍም ይህንኑ ያንጸባረቀ ነበር። “አሁን ሀገሪቷን ለገጠማት ፈተና እውነተኛ መፍትሄ ማፈላለግ የግድ ነው። መንግስት ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሳይወጡ ቀውሱን የሚመጥን አመራር መስጠቱ የግድ ነው። ዜጎች በዘር እና በሃይማኖት ተለያይተው ሲጋደሉ ከማየት ለጊዜውም ቢሆን የተወሰነ መብቶቻችን ቢገደብ እመርጣለሁ። መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን አውጆ፣ በልሂቃኑ መካከል፣ ከድራማ የራቀ እውነተኛ ውይይት እና ድርድር ማስጀመር አለበት” ሲሉ ጽፈዋል። 

ሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ደግሞ ህዝቡ ሊያደርግ የሚገባውን አመላክተዋል። ዳንኤል ዲሳሳ ፉፋ ባለፈው ማክሰኞ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር መልዕክት “ችግር ውስጥ ወድቀናል” ሲሉ ኢትዮጵያ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።“ሀገር አንዴ ካመለጠችን መልሰን መሰብሰብ ይከብደናል። እያንዳንዱን ነገር በታላቅ ኃላፊነት እንፈጽም” ብለዋል። 

መስዑድ ኤም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚም “እንደ ህዝብ ነው የወደቅነው” ሲሉ መደረግ አለበት ያሉትን መክረዋል። “የሞራል ሚዛናችንን የሚያዛንፉ ድርጊቶችን በጋራ ነቅሰን ማረም ተስኖናል። [ፈረንጆች] soul searching የሚሉት አይነት ከራስ የጀመረ የእውነት ንግግር ማድረግ፤ ቢያንስ እንደ ሰው የሚያስብ ማህብረሰብ ለመፍጠር ይረዳን ይሆናል” ሲሉ ጽፈዋል። መንግስቱ ዲ. አሰፋ  በፌስ ቡክ ገጻቸው “በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት በጊዜ አንድ ነገር ካልተባለ አደጋው ከምንጊዜውም በላይ የከፋ የሚኾንበት እድሉ ሰፊ ነው” ብለዋል። ለዚህም ሶስት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። 

Pressebilder Kalashnikov AK 203
ምስል Kalashnikov Group

“ከምን ጊዜውም በላይ የፖለቲካው ከባቢ አየር መርዛማ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ጥላቻው ስር ሰድዷል። በድሃ አገር ላይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የሚቆጭ ጠባሳ ጥለው የሚሄዱ ጭካኔዎችን ይወልዳሉ። [ለዚህ] ታሪክ ምስክር ነው” ሲሉ ጸሀፊው የመጀመሪያ ምክንያት ነው ያሉትን አጋርተዋል። “ባለፉት ሁለት ዓመታት የመንግሥት ጸጥታ ማስጠበቅ ‘የቸልተኝነት’ ምልክት በማሳየቱ ይኼንን ክፍተት ተጠቅመው የግጭት ንግዳቸውን የሚያጧጡፉ ኃይሎች ብዙ ናቸው” ሲሉ ሁለተኛ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።  “ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ ለምን እንደበረከተ ማሰቡም አይከፋም” ብለዋል።

መንግስቱ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አንድ ደረጃ ከፍ ብለው ኃይማኖትንም ማካተት ጀምረዋል። የዚህ አደገኛነት የማይታየው ሰው ካለ የዋህ ነው” ሲሉ ሶስተኛ ምክንያታቸውን ጠቅሰዋል። መንግስቱ “ጣት መቀሳሰሩን ትተን የሁላችንን ቤት የሚያንኳኳውን ችግር አብረን እንጋፈጠው” ሲሉ አጠቃልለዋል።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር መፍትሄው “በአንድነት መቆም ነው” የሚል እምነት አለው።  ውብሸት “የሚያመልጥ ማንም የለም” በሚል ርዕስ ባለፈው ሰኞ በፌስ ቡክ ገጹ ካስነበበው ጽሁፍ ተከታዩን ቀንጭበናል። “የብዙዎች በር እየተንኳኳ ነው። መከራው በየቤቱ እየገባ ነው። ስንሰማው ሩቅ የሚመስለን በጣም ቅርብ ነው። እኛ ግን አሁንም መለያየትን እየሰበክን ወይም ሲሰበክልን አሜን ብለን እየተቀበልን ነው። ‹ተው!› ማለት አልቻልንም፤ አልፈለግንም። ሲሆን የከረመውን እና እየሆነ ያለውን እያየነው ነው። በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ ለመግለጽ ቀርቶ ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍ እየተፈጸመ ነው። የሆነው እና እየሆነ ያለው ታዲያ ከውጭ በመጣብን ወራሪ ሳይሆን ‘እርስ በርሱ፤ ስጋን በኩበት ጠበሱ’ እንደሚባለው እኛው በእኛው መሆኑ ያሳዝናል፤ ያስቆጫል እንዲሁም የመፍትሔ ውሉን ያጠፋዋል። እመኑኝ ተባብረን በአንድነት ካልቆምን፤ ዛሬ የጎረቤታችን የሚመስለን መከራ ሁሉ ነገ የእያንዳንዳችንን በር ያንኳኳል፤ የሚያመልጥም የለም!” ሲል ጽፏል።

በዜህ ሳምንት በወልዲያም ሆነ ከዚያ በኋላ የነበሩ ክስተቶችን ያመላክታሉ በሚል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወሩ የነበሩ በርካታ ፎቶዎች ከዚህ ቀደም በሌሎች ሀገራት ከነበሩ ሁነቶች የተወሰዱ መሆናቸውም አነጋግሯል። ፎቶዎችን ያጋለጡ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች “በሀሰተኛ ምስሎች በእሳት ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ መቆጠብ” እንደሚገባ ሲመክሩ ተስተውለዋል። እንደዚህ አይነቶቹን የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች በሀገሪቱ በየቦታው ያለውን ችግር ለመሸፋፈን የሚደረግ ሙከራ አድርገው የቆጠሩትም አልጠፉም።

Äthiopien verhaftet 63 wegen Verdachts auf Menschenrechtsverletzungen, Korruption. Der Generalstaatsanwalt Berhanu Tsegaye sagte heute (03.11.2018) lokalen Journalisten, dass die Inhaftierung nach fünf Monaten Ermittlungen erfolgt.
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

በሳምንቱ ውስጥ በማህበራዊ መገናኛዎች ሌላው ያወያየው ጉዳይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ ም በባህር ዳር እና አዲስ አበባ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የጦር ጄነራሎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን የተመለከቱ የምርምራ ውጤቶች ይፋ መደረጋቸው ነበር። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እና የአማራ ክልል አቻቸው አቶ ገረመው ገብረጻድቅ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ሰኔ 15 በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ የተፈጸመው ጥቃት በብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የተመራ እንደነበር ገልጸዋል። ድርጊቱንም “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ሲሉ ገልጸውታል። በመግለጫው እምብዛም አዲስ ነገር እንዳላገኙ የጠቆሙ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ድርጊቱ የተፈጸመ ዕለት በመገናኛ ብዙሃን የተነገረውን የደገመ ነው ሲሉ የምርመራውን ውጤት አጣጥለውታል። 

ሳሙኤል ብሩክ በትዊተር “ብዙ የተባለለት የሰኔ 15ቱ ወንጀል የአቃቤ ህግ መግለጫ እንደተጠበቀው ተቀሽሮ ቀርቧል። ምን አዲስ ነገር አለው? ምንም” ሲሉ ጽፈዋል። ሃይሌ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ “ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሰጠው መግለጫ እና ንጉሱ ጥላሁን ከአምስት ወር በፊት በሰጠው መግለጫ መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ብቻ ነው” ብለዋል። ጌታቸው ተማረ በበኩላቸው “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ያገኙትን ያንኑ ነገር አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በምርመራ ለማግኘት አምስት ወር ወሰደባቸው። ለዚህ እኮ ነው ኢትዮጵያውያን አብይ ነብይ ነው የሚሉት” ሲሉ በዚያው በትዊተር ተሳልቀዋል። 

ሙክታሮቪች ኡስማኖቫ በተሰኘ የፌስ ቡክ ገጻቸው በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን በማካፈል የሚታወቁት የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲው መምህር ሙክታር ኡስማን መግለጫውን ከተቹት መካከል አንዱ ናቸው። “አቃቤ ህግ ያቀረበው መግለጫ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ አምስት ወር ቀርቶ የአምስት ቀን የምርመራ ውጤትም የማይመስል ነው። በመጀመሪያ ቀን በንጉሱና በአብይ ከተሰጡት ምክንያቶች በምንም የማይሻል ጥልቀት የሚጎድለው የምርመራ ውጤት ነው። የጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና ጄኔራል አበራ ገዛኢን ግድያ ከባህርዳሩ ግድያ ጋር ያለውን ተዛምዶ ለማስረዳት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን በዚህ ምርመራ ውጤት የገባበት አላማ፣ አንድም መፈንቅለ መንግስት የሚለውን ለማጠናከር ሁለትም በሴራው ውስጥ አንድ የኦሮሞ ጄኔራል በማስገባት የብሄርን ተዋፅኦ ለሟሟላት ይመስላል። የአዲሳባው ግድያ ብርሃኑ ጁላን እያክለፈለፈ እንዲያመጣው እና በዚህም ምክንያት በመግደል በሰራዊቱ መካከል ግጭት መፍጠር የተባለው ምክንያት ከውጤት የሚራራቅና የማያሳምን መሆኑ መግለጫው ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረን አድርጓል” ብለዋል በፌስ ቡክ ጽሁፋቸው።  

Äthiopien General Berhanu Jula PK
ምስል DW/S. Muchie

በአቃቤ ህግ መግለጫ የተጠቀሰው የጄነራል ብርሃኑ ጁላ ጉዳይ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። ጋሻው አልምዬ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “ሌላውን የተንዛዛ ድራማ እንተወው እና ጀነራል ሠዓረ መኮንን ከተገደለ በኋላ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ሲመጣ እንገድለዋለን ብለው አስበው ጀነራል ብርሃኑ ጁላም ባለመሄዱ ሳይገደል ቀርቷል ያሉት እያሳቀኝ ነው። ወይ መፈንቅለ መንግስት” ሲሉ በመግለጫው የቀረበውን አጣጥለዋል። 

ጸሀፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተክለአረጋይም ይህን የጠቅላይ አቃቤ ህጉን ማብራሪያ “ሊገባኝ አልቻለም ብቻ ሳይሆን ራሴን ለማሳመን ፈልጌ አቃተኝ” ሲል በፌስ ቡክ ጽፏል። ማብራሪያው ላይ ተተንርሶም በርካታ ጥያቄዎችን ደርድሯል። “እንዴት ነው መምጣታቸውን እርግጠኛ ሆነው ለግድያ የሚዘጋጁት? ሌላስ ሰው ለምን አይመጣም ? ቢመጡስ ብቻቸውን ነው ያሚሆነው? አጃቢዎቻቸውስ? እንዴት ከዚያ መሀል ነጥለው ለመምታት ይመቸናል ብለው አሰቡ?” ሲል በመግለጫው የቀረበው ማብራሪያ እንዳልገባው ገልጿል።

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ