1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰሞኑ፦ የ“ሞንጆሪኖ” ማሳሰቢያ ፣ የቴሌ ቅናሽ

ዓርብ፣ ነሐሴ 18 2010

በሳምንቱ ውስጥ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አበይት መነጋገሪያ ከሆኑት ውስጥ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር በአንድ ውይይት ላይ የሰጡት አስተያየት ይገኝበታል። ኢትዮ ቴሌኮም በሳምንቱ አጋማሽ ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በማህበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ በጎ ምላሽ አስገኝቶለታል።

https://p.dw.com/p/33gYB
Äthiopien 40. Jahrestag TPLF
ምስል DW/T. Weldeyes

ከሰሞኑ፦ የ“ሞንጆሪኖ” ማሳሰቢያ ፣ የቴሌ ቅናሽ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮች እና ነባር ታጋዮች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች በተለየ አትኩሮት መታየት ይዘዋል። ዶ/ር ዐብይ አህመድ  ስልጣን ከያዙ ወዲህ በገዢው ግንባር ውስጥ የተቃዋሚነት ሚና እየተጫወተ ነው የሚባልለት ህወሓት እያንዳንዱ እንቅስቃሴው እንደው በዋዛ የሚታለፍ አልሆኑም። የአመራሮቹ የግል አስተያየቶች ጭምር ሞቅ ያሉ ክርክሮችን ይጭራሉ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ስድተኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ በመቀሌ የተካሄደውን የፓናል ውይይት ተከትሎ የሆነውም ተመሳሳዩ ነው። 

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ የጠቃቀሷቸው ነጥቦች “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ላይ ያነጣጠረ ነው” በሚል ብዙዎች ሲቀባበሉት ተስተውሏል። በርካቶችን ለውይይት የጋበዘው ግን የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖ) ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ነው። አንድ ወጣት ተሳታፊ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንዳለ ህወሓት አቋሙን ግልጽ እንዲያደርግ ለጠየቀው ምክትል ሊቀመንበሯ ተከታዩን መልሰዋል።

Äthiopien 40. Jahrestag TPLF
ምስል DW/T. Weldeyes

“አብዮታዊ ዲሞክራሲ አቅጣጫ ስተን እየሄድን እንደሆነ፣ ሀገሪቱ ወደ ጥፋት እያመራች እንዳለች በዝርዝር የተገመገመ ጉዳይ ነው። የእነዚህ መገለጫዎች ናቸው አሁን በከፋ መልኩ፣ ለመስማትም በሚዘገንን መንገድ በሰው ህይወት ጥፋት እየደረሰ ያለው። በንብረት ጥፋት እየደረሰ ያለው። በአጠቃላይ ህዝባችን በከፍተኛ የሆነ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ከዚህ በመውጣታችን ነው። መፍትሄው ደግሞ ወደ ቦታችን መመለስ ነው።”

የምክትል ሊቀመንበሯ ይህ ንግግር በበርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ትችት ቀስቅሷል። አብዮታዊ ዲሞክራሲን “የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈበት መድኃኒት” ጋር ያነጻጸሩት አቶ አስራት በጋሻው በፌስ ቡክ እንዲህ ብለዋል። “አንድ መድሀኒት የመጠቀሚያ ጊዜ ካበቃ በኃላ በመደርደርደሪያ ላይ መቀመጥ የለበትም፡፡ መወገድ፣ መቀበር፣ መቃጠል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ደግሞ በሀገር በቀል መድኃኒት ተፈውሳለች፡፡ እና በሽተኛው ከተፈወሰ በኋላ መድኃኒቱ ምን ያደርጋል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አባል ግርማ ሰይፉ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን በፌስ ቡክ ገጻቸው ያጋሩት የወ/ሮ ፈትለወርቅን ቅጽል ስም ተጠቅመው ነው። “ሞንጆሪኖ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቀልብሷል፣ መፍትሔው ወደሱ መመለስ ነው ብላናለች። ዶ/ር ዐብይ አህመድን የደገፍነው ለምን እንደሆነ አልገባትም ማለት ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሰመር አክሳሪ መሆኑን አውቀው፣ ሳይነግሩን በተግባር ስላሳዮን ነው። ሞንጆሪኖ! ባይ ባይ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብለናል” ሲሉ ጽፈዋል። 

በዚያው በፌስ ቡክ ጫላ ዳንዴሳ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተቀለበሰው ዛሬ ነው እንዴ?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ይንደደራሉ  “ገና ድሮ አይደለም እንዴ በራሱ በኢህአዴግ ‘አዋጪ አይደለም!’ ተብሎ ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲ የተንከባለልነው? ባጭሩ ሕወሓት እንደፈለገች በየክልሉ የምትፈነጭበት ጊዜ አልፏል። እሱን ጊዜ ደግሞ መልሶ ማምጣት አይቻልም! ሴትየዋ ያ ግልፅ ቢሆንላት መልካም ነው። ከዚህ በኋላ ሕወሓት ያላት አንድ ጤነኛ አማራጭ እንደ እህት ድርጅቶቿ ወጣት የሆነና ከዘመኑ የሕዝቡ እሳቤ ጋር የተግባባ አመራር ወደፊት በማምጣት የትግራይ ሕዝብን ከሌላው ሕዝብ ጋር የማቀራረብና የሕዝቡንም ኑሮ በማሻሻል ረገድ ጠንክራ ለመስራት መዘጋጀት ነው።” ብለዋል።  

ወርቁ በዳዳ “ወደነበርንበት እንመለስ” የሚለውን እንዴት እንደተረዱት በፌስ ቡክ ሲጽፉ “አጋዚ፣ ማእከላዊ፣ ቂሊንጦ፣ ጭቆና፣ አፈና እና የሕወሓት የበላይነት” የሚሉትን ቃላት ተጠቅመዋል። ሞሃመድ ቲ. ዴኮ የተሰኙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም የወ/ሮ ፈትለወርቅ ወደ ነበርንበት እንመለስ መፍትሄን አልተቀበሉትም። “ወ/ሮ ፈትለወርቅ በምን መልኩ ወደ ነበርንበት ሊመልሱን እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም፡፡ እኛ ግን ወደ ነበርንበት ሁኔታ እንኳን ለመመለስ ስናስታዉሰውም ይነዝረናል፡፡ ስንት ሰዉ አካሉን ያጣበት፣ ስንት ሰዉ የተሰቃየበት፣ ሀገር መከራ ዉስጥ የገባችበትን ሁኔታ ማስታወስ ይነዝራል፡፡ ለሰራነው ግፍ ይቅርታ አርጉልን ብለዉ ይጠይቁናል ብለን ስንጠብቅ ጭራሽ ‘ወደነበርንበት መልሱን?’ ይህን ያመጣዉ የዶ/ር አብይ የእንደመር ‘ልመና ነው፡፡’ ገዳዮች ለሕግ ይቅረቡልን” ሲሉ ኮምጨጭ ያለ አስተያየታቸውን አካፍለዋል። 

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ካሳ አንበሳው  በሚል ስም ፌስ ቡክ የሚጠቀሙ ግለሰብም እስርን መክረዋል። ረዘም ካለው ጽሁፋቸው ተከታዩን ቀንጭበናል። “አምባገነኖች በባህሪ አንድ ናቸው። መጀመሪያ የራሳቸውን አለም ይፈጥራሉ፤ ከሌላው ህዝብ የተለየ ትንሽ አለም። የሚመላለሱት በዛች ትንሽ አለም ነው። ህዝቡን አያውቁትም። እውነት እኛ ጋር ነች ብለው ያምናሉ። ሰማይን እንደ ምሰሶ ደግፈው እንዳቆሙ ይሰማቸዋል። ስልጣን ከለቀቁ ሰማይ እንደሚደፋ፣ ምድር እንደምትጠቀለል ያምናሉ፤ ሊያሳምኑም ይሞክራሉ። ህወሓት እያደረገ ያለው ከአምባገነን የማይጠበቅ አይደለም።

ዛሬ ሞንጆሪኖ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተመልሶ ቦታውን ካልያዘ ሀገሪቷ ያበቃላታል አለች። ይህም ለሞንጆሪኖ እና ለሌሎች እውነት ነው። መቀሌ መሽጓል የሚባለውን ቡድን ‘ጸረ-ለውጥ’ ብለህ የምታስበው አንተ ነህ. እሱን ብትጠይቀው ‘ኢትዮጵያን ለማዳን ነው’ ብሎ ነው የሚመልስልህ። የህወሓት ነውረኞች ‘እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ያበቃላታል’ የሚለውን ትርክት ለኦባማ ጭምር ሳይነግሩት የቀረ አይመስለኝም። ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ባደረገው ንግግር ‘አንዳንዴ መሪዎች ይህቺን ሀገር አያይዤ ያቆምኩት እኔ ነኝ’ ሲሉ ትሰማችኋላችሁ። ያ እውነት ከሆነ እንግዲያው መሪዎቹ ሀገራቸውን መገንባት አልቻሉም ማለት ነው’ ብሎ ነበር።  እንደኔ እንደኔ ሰዎቹ ታስረው የማስላሰያ ጊዜ ቢያገኙ ጥሩ ነው።”

በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን የምንቋጨው ዳንኤል ረጋሳ “የህወሓት ህልም እና የሞንጆሪኖ ቅዠት” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባስነበቡት አስተያየት ይሆናል። “ማንፈቅዶላችሁ ይሆን ከእንግዲህ በኋለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የምትሉትን ጨለምተኛ አስተሳሰብ መልሳችሁ ለማምጣት የምትመኙት? ለውጡ በህዝብ ግፊት እና ጫና መምጣቱን ዘንግታችሁት ወይስ አሁንም ከቅዠት ዓለም አልወጣችሁም ?” ሲሉ ጸሀፊው ይጠይቃሉ። “ወደ እድገት ማማ ለመውጣት በትግል ላይ ያለች ሀገርን ‘በውድቀት ቁልቁለት ላይ ተቀምጣለች’ ማለት መልዕክቱ ሌላ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እራሳቸው ሹመት የሰጧቸው ግለሰቦችን ከእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ማጽዳት ካልቻሉ በማንኛውም ሰአት ለውጡን ከማደናቀፍ ወደኋላ አይሉም። እና ድጋሚ ሊታሰብበት ይገባል ባይ ነኝ” ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃልለዋል።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች ሰጪ የሆነው መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም በማህበራዊ መገናኛዎች ብዙውን ጊዜ ነቀፌታ፣ ወቀሳ እና እሮሮ ሲያስተናግድ ነው የቆየው። መስሪያ ቤቱን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ በቅርቡ የተሾሙት ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ባለፈው ረቡዕ የሰጡት መግለጫ ግን ሙገሳ አትርፏል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎችን የማስመዝገብ ግዴታ መቅረቱን እና ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን ማሳወቃቸው ነበር የአድናቆቱ መነሻ።

Äthiopien Freheiwot Tamiru Ethio Telekom
ምስል DW/G. Tedla

“የታሪፍ ማሻሻያው ቅናሽ ነው። በሞባይል ድምጽ ላይ የ40 ፐርሰንት ቅናሽ፣ በሞባይል ኢንተርኔት የ43 ፐርሰንት እንዲሁም የሞባይል አጭር መልዕክት የ43 ፐርሰንት ቅናሽ አድርገናል ማለት ነው። እንዲሁም በሌሎች አገልግሎቶቻችን በብሮድባንድ፣ ኢንተርኔት፣ በብሮድባንድ ቪ. ፒ. ኤን ሌሎችም አገልግሎቶች ላይ እንደዚሁ የታሪፍ ማሻሻያ አድርገናል” ብለዋል ወይዘሪት ፍሬህይወት በመግለጫቸው። 

የኢትዮ ቴሌኮም ውሳኔ በደስታ ከተቀበሉት  አንዱ የሆኑት ነቢል ኸሊፋ በትዊተር ገጻቸው “ይህ በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።  በእምነት ኤ. መኩሪያ በበኩላቸዉ “ኢትዮ ቴሌኮምን በተመለከተ በአስርት ዓመታት ውስጥ የተሰማ ጥሩ ዜና” ሲሉ በትዊተር የገለጹት ሲሆን ዶ/ር ሰሎሞን ደርሶ በበኩላቸው “ለአዲሱ ዓመት ከኢትዮ ቴሌኮም የተሰጠ ስጦታ” ብለውታል።

አለማየሁ በቀለ በዚያው በትዊተር ኢትዮ ቴሌኮም ከቅናሹ አትራፊ እንጂ ከሳሪ እንደማይሆን ግምታቸውን አስቀምጠዋል። “ይህ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ገቢያቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያድኑበት ነው። ነገር ግን የእኔ ጥያቄ ሰዎቹ ያተረፉትን ይቆጥባሉ ወይስ ይበልጥ ኢንተርኔት ይጠቀማሉ? የሚል ነው። የኋለኛው ከሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚያጣው ይልቅ የሚያገኘው ይበልጣል” ሲሉ ተቋሙ ራሱ ከማሻሻያው እንደሚጠቀም አመላክተዋል።

“በሞኖፖል ከተቆጣጠሩት አገልግሎት እንዲህ አይነት ቅናሽ በእውነቱ ግሩም ነው” ያሉት ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ አዲሲቷ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የወሰዱትን እርምጃ አድንቀዋል። በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለነጻ ገበያ ክፍት ማድረግ ውድድርን እንደሚያበረታታም ጠቁመዋል። 

አለባቸው ሞልቶት በትዊተር ገጻቸው የኢትዮጵያ ቴሌኮምዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ይባል የነበረው ድርጅት በፈረንሳይ ድርጅት አማካሪነት ኢትዮ  ቴሌኮም ተብሎ ከተቀየረ በኋላ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ታሪፍ ተጭኖባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የተቋሙ ደንበኞች በተለይ በ3ጂ የኢንተርኔት አገልግሎት ታሪፍ ይማረሩ እንደነበርም ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮምን “ራስ ወዳድ እና እብሪተኛ ” ሲሉ የጠሩት አቶ አለባቸው “አሁን ከዚያ ነጻ ወጥተናል” ብለዋል። 

አቤል የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ “እንዴ ቴሌ ብር በቃኝ አለ? መቀነስ ይበጃል አለ? ተአምር ነው” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተዋል። ብሩክ አማኑኤል  “ቅናሽ ማለት ዝቅተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ማለት አይደለም። ይልቁንም የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት፣ ሰፊ ሽፋን እና በአገልግሎቱ የረኩ ተጨማሪ ደንበኞች ማለት ነው” ሲሉ ኢትዮ ቴሌኮም ልብ ማለት ያለበትን ጉዳይ አንስተዋል። 

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ የሆነውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎችን የማስመዝገብ ግዴታ በመነሳቱ ከተደሰቱት መካከል ብርሃን ታዬ አንዷ ናት። እርሷ እና መሰሎቿ የማስመዝገብ ግዴታው እንዲነሳ ሲወተውቱ መቆየታቸውን ያስታወሰችው ብርሃን እርምጃውን “ታላቅ” ብላዋለች። “ሰላዩ መንግስት ራሱን እያረቀ ነው” ስትል አክላለች። ቀፎ የማስመዝገብ “ሂደቱ ከመጀመሪያውኑ አንስቶ በችግር የተሞላ ነበር” ያለችው ትዝታ ማስመዝገቡ ይቅር በመባሉ ደስታዋን በትዊተር ገልጻለች። እርምጃው “ያሳካው ነገር ቢኖርየሚጎላሉ ተጨማሪ የቴሌ ተጠቃሚዎችን መፍጠር ነበር” ስትል ኮንናለች።  በዚህ ሳምንት የቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት መሰረት ፈጠነ የተባለች ወጣትን  ታሪክን በቪዲዮ አቀናብሮ አሰራጭቶ ነበር። ቪዲዮው፤ መሰረት ከቤት ሰራተኝነት እስከ ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ከጫማ ጠራጊነት እስከ ጫማ ሰሪነት የተጓዘችበትን ውጣ ውረድ በአጭሩ ያስቃኛል። የአንድ ልጅ እናት የሆነቸው እና በህይወቷ ብዙ ያየችው መሰረት ጫማ፣ ስካርፍ፣ ቀበቶ እና አልጋ ልብስ በክር እየሰራች ለሽያጭ ብታቀርብም እምብዛም ገበያ አለማግኘቷን ታስረዳለች። ይህንን የመሰረት ታሪክ ከ“አዲስ ስታንደርድ” መጽሔት የትዊተር ገጽ የተመለከተው አንድ የድረ ገጹ ተጠቃሚ አንድ ሀሳብ ብልጭ ይልለታል። 

ብርካን ፋንታ በሚል ስያሜ ትዊተርን የሚጠቀመው ይሄው ግለሰብ ለመሰረት በነጻ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ሊሰራላት ያስብና የ“አዲስ ስታደርድ” መጽሔት አዘጋጆች አድራሻዋን እንዲሰጡት ይጠይቃል። ቪዲዮውን ደግሞ ሲመለከተው መሰረት በቀን አንድ ጫማ የመስራት አቅም ቢኖራትም ብዙ ትዕዛዝ እንደማታገኝ የተናገረችውን ያስተውልና ከእርሱ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ሊያግዟት የሚችሉበት አንድ ሀሳብ ውል ይልበታል። 

ብርካን “ትዕዛዝ የለም እንጂ ያለችውን ለመቅረፍ መቶ ስው እንዲገዛት ብዬ ለተወሰኑ ሰዎች በውስጥ መስመር መልዕክት ስልክ ፈጣን ምላሽ ሰጡ” ይላል ከዶይቼ ቬለለተጠየቀው በጽሁፍ በሰጠው ምላሽ። “እንዲህ ከሆነማ አመቱን ሙሉ ስራ እንዳትፈታ እናድርግ አልኩ። ለዓመት 365 ትዕዛዝ ቢኖራት አሪፍ ነው ብዬ እንደ ቀልድ ትዊት ሳደርግ ለራሴም እስክደነግጥ በስዓታት ውስጥ መቶ ትዕዛዝ ሞላ” ሲል ከሌሎች የትዊተር ተጠቃሚዎች ያገኘውን ምላሽ ያስረዳል። 
ጫማ እንዲሰራላቸው የሚጠይቁ ሰዎች ትዕዛዝ መስጠቱ አሁንም ቀጥሏል። ከትዕዛዞቹ ሌላ የመሰረትን ስራዎች የሚያስተዋውቅ ድረ ገጽ፣ ኒውዮርክ የሚገኝ መደብር በቋሚነት አብሯት ሊሰራ የሚችልበት ዕድል ለማመቻቸት እና የአንድ ደቂቃ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ፕሮዳክሽን ለመስራት ቃል የገቡ የትዊተር ተጠቃሚዎችም ተስተውለዋል።  

(ዶይቼ ቬለ ከዚህ ቀደም ስለ ወጣት መሰረት ፈጠነ ያዘጋጀውን መሰናዶ ለማድመጥ የሚከተለውን መስፈንጠሪያ ይጫኑ)

 ሊስትሮዋ የልጅ እናት

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ