1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሞያሌ ከ84 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2011

በሞያሌ ከተማ ከባለፈው ሳምንት አንስቶ በተካሄደው ግጭት ከ84 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡ ለተፈናቃዮቹ ምግብና ውሃን ጨምሮ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ መጀመሩን የቦረና ዞን መስተዳድር ገልጧል፡፡ በከተማዋ አስከ ትናንት ሲካሄድ የነበረው ግጭትም ዛሬ በተወሰነ ደረጃ ተረጋግቶ መዋሉም ታውቋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3AOsZ
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል

ሳምንቱት በግጭት ስትታመስ የሰነበተችው ሞያሌ / በዛሬ ዕለት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖባት መዋሏን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፤ 
 በተለይም የፌደራሉ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ከገባ ወዲህ ግጭቱ ጋብ ቢልም / የመንግስት መሥራቤቶችን ጨምሮ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግን አሁንም አንደተዘጉ ይገኛሉ፡፡ 
በከተማው የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ እስከአሁን ከሰማኒያ አራት ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የቦረና ዞን መስተዳድር ጽህፈት ቤት ዛሬ ይፍ አድረጓል፡፡ 
 በአሁኑወቅት ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ እርዳታዎችን ማቅረብ መጀመሩን ነው የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ዋቆ ለዲ ደብሊው የገለጹት፡፡ 
አብዛኞቹ ነዋሪዎች የተፈናቀሉት አጎራባች የሞያሌ ቀበሌዎችን ጨምሮ / ያቤሎ ፤ ድሬ፤ ሜጋ፤ ሚዮ፤ ሱርባና ዱብሉቅ ወደ ተባሉ ወረዳዎች መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በአሁኑወቅት በመንግሥት እየቀረበ ካለው ዕርዳታ በተጓዳኝ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ ቢሆንም / በቀጣይ ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋሙ ሥራ ግን ሰፊ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ 
በአሁኑወቅት ተለይቶ የቀረበው የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የሚናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው ይህም በግጭቱ የመቆም ወይም የመቀጠል ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል፡፡ 

የሞያሌ ከተማ በሶማሌ የገሪና በኦሮሞ የቦረና ጎሳዎች መካካል በተነሳ የአስተዳደር ይገባኛል ጥያቄ አስከ ትናንት ምሽት በግጭት ውስጥ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑወቅት በግጭቱ ከፈናቀሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ / 41 ሰዎች ሞተዋል ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩት ቆስለዋል፡፡

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ