1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከምርጥ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር የተካተተው ወጣት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 5 2013

የ23 ዓመቱ ትንሳኤ አለማየሁ የመቀሌ ዩንቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነው።ወጣቱ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ሽልማት ተቋም በዚህ ዓመት ከመረጣቸው እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ከሆኑ ምርጥ 10 የአፍሪካ የህዋ ምርምር ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ነው።

https://p.dw.com/p/3yqyN
Tensae Alemayehu
ምስል Privat

ከምርጥ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር የተካተተው ወጣት


የ23 ዓመቱ ትንሳኤ አለማየሁ የመቀሌ ዩንቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነው።ወጣቱ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ሽልማት ተቋም  በዚህ ዓመት ከመረጣቸው እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ከሆኑ  ምርጥ 10 የአፍሪካ የህዋ ምርምር ባለሙያዎች  ውስጥ አንዱ ነው።ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ለህዋ ሳይንስ ምርምርና ለምህንድስና ሙያ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው ትንሳኤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማህበረሰብ አባል በመሆን ከመደበኛ ትምህርቱ በተጓዳኝ በንባብ  ያገኘውን የህዋ ሳይንስ ዕውቀት ለሌሎች ለማካፈል ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
 «መሰረታዊ የሆኑ ብዙ ነገሮች ይቀሩናል ብለን ስለምናስብ  አብዛኛዎቹ ስራዎቻችን በግንዛቤ ማስጨበጫ  ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።  በዚህም ምክንያት በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በዩንቨርስቲ ተማሪዎች፣  በአጠቃላይ ኗሪው ላይ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት እንሰራ ነበር።  ከዛ በተጨማሪ  ትንሽ  ይትምህርት  ስሜት ብቻ  ፈጥሮ ሰውን እንዳያርቀው  ለዘብ ለማድረግ በጨዋታ መልክ የተለያዩ የምልከታ «ኘሮግራሞችን» እናዘጋጅ ነበረ።  ጠጋ ብሎ  ጨረቃን ከነ ጉድጓድ ከነ ተራሮቿ ማየት ለብዙ ሰው የሚያስደንቅ ስለነበረ፤ የማርስን   ቅላት ማየት፣  የጁቢተር ገንፎ የሚመስለውን መልክ ከዚያ ደግሞ የሳተርንን ቀለበት ማየት በጣም ለብዙ ሰው የሚያስደንቅ ነገር ስለሆነ፤ ይህንን  በአጠቃላይ  ለህብረተሰቡ የማሳየት ስራዎችን በብዛት እንሰራ ነበር። »

Tensae Alemayehu
ምስል Privat

ከዚህ በተጨማሪ ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪቃ ደረጃ በየዓመቱ የሚዘጋጀውን ሶስተኛውን የአፍሪቃ   የህዋ ሳይንስ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲዘጋጅ አድርጓል።ይህንን የወጣቱን ተስፋ ሰጪ ስራዎች የተመለከቱ ታዲያ «አፍሪቃ ኢን ስፔስ» የተባለው ተቋም በቅርቡ ላካሄደው የ2021 የአፍሪቃ ወጣት ምርጥ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ምርጫ  ዕጩ አርገው አቀረቡት።
በዚህ ውድድር ከበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት የተወከሉ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ትንሳኤ እና ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት  የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ ወጣት ቤተልሄም ግርማ  ከአፍሪቃ 10 ምርጥ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ ወጣቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።ይህ እዉቅና ከዚህ ቀደም ለተሰሩ ስራዎች ዋጋ ከመስጠቱ ባሻገር በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ፊት ለሚሰራቸው  ስራዎች በር ከፋች በመሆኑ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረለት ይናገራል።
«ሁለት ነገር ነው በዋናነት  እንደ ግለሰብ የማስበው። አንደኛ  እስካሁን የነበሩ ስራዎች  እንዲሁ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዳልቀረ እና ለዓለም ሁሉ  እንዲህ ዓይነት ነገር ተሰርቷል የሚለውን ነገር እንዲደርስ ለተደረገ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ።  በተጨማሪ ደግሞ አንድ ሰው ሊሰራ ሲል ብዙ ጊዜ  በመጀመርያ የሚጠየቀው በዚህ ዘርፍ ምን ሰርተሀል ? ምን አይነት ልምድ አለህ ? የሚለው ነውና እንደዚህ አይነት ዕውቅና  እቅዶቻችን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ በር የሚከፍት ነው ብዬ አስባለሁ።  እቅዶቻችን ተግባራዊ ለማድረግ  በጣም ብዙ በሮችን ይከፍትልናል ብዬ አስባለሁ በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ  ደረጃም ማለት ነው።»ሲል ገልጿል።

Tensae Alemayehu
ምስል Privat

በቱርክ አንካራ የአቬሽን ቴክኖሎጅ ስልጠናን  የተከታተለው ትንሳኤ ፤ የመቀሌ እና   የቤልጄሙ ቶማስ ሞር ዩንቨርሲቲዎች  በጋራ ባያዘጋጁት  «ሙን ሹት ኢትዮጵያ» የተባለ ልዩ የትምህርት መርሃ ግብር ተከታትሎም የድርብ ክብር ዲግሪ አግኝቷል።ለዘርፉ ተመራማሪዎች በሚሰጠው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ መርሃ ግብር በዘንድሮው ዓመት  አሸናፊ ከሆኑ ከአምስት የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ውስጥ ከአፍሪቃ የመጀመሪያው ነው። ታሪክና ጥንታዊ መፃህፍትን ማንበብ እንደሚያዘወትር የሚገልፀው ትንሳኤ፤ ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት የአቡነ ጎርጎሪዮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የግዕዝ ቋንቋ መማሩ ደግሞ ተጨማሪ ጥንታዊ መፃህፍትን ለማገላበጥ ዕድል ሰጥቶታል። ከእነዚህ መፃህፍት ያነበበው ጥንታዊ  ታሪክ ታዲያ፤ የህዋ ሳይንስ ምርምር የአደጉ ሀገራት ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ጥንታዊ መሰረት እንዳለው እንዲገነዘብ አድርጎታል። ይህ ግንዛቤ በትምህርት ቤት ከሚያገኘው ዘመናዊ የሳይንስ ትምህርት ጋር ተዳብሎ ወደ ህዋ ሳይንስ ምርምር  የበለጠ እንዲሳብ አድርጎታል። 
 «በዚህ ነገር ላይ ብሠራ ደስ ይለኛል ያልኩበት ምክንያት፤ ታሪክ እወድ ነበር ። ብዙ አደለም የተወሰነ አነባለሁኝ።  የቅርቡ እንዳለ ሆኖ በጣም  በጣም  የዱሮ የሚባሉትን  ሁሉ አነባለሁ። እና ሦድስተኛ  ክፍል እያለሁ  አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ስገባ፤ ያኔ ግዕዝ መማር ጀመርን። ትምህርት ቤቱ ውስጥ በካሪክለም ስለሚሰጥ። በዚያ  ምክንያት የማነባቸው መጽሐፍት ዝርዝር  የአማርኛ መፃህፍት በተጨማሪ የግእዝ የብራና መጽሐፍትን  የማንበብ አቅምን ፈጠረ ልኝ። ስለዚህ በዛ ምክንያት ቀጠልኩ ማለት ነው።» ካለ በኋላ፤ ካነበባቸው ጥንታዊ መፅሀፍት ውስጥ  በተለይ አንዱ  የበለጠ  ለዘመናዊው የህዋ ሳይንስ ቀረቤታ እንደነበረው ያስታውሳል።  
«ለምሳሌ  በዋነኝነት ስትጠቀምበት የነበረው አክሲማሮስ የሚባል አንድ መጽሐፍ ነበር። በመሠረቱ መጽሐፉ ስለ ስነ-ፍጥረት ነበር ሚያወራው። ነገር ግን እዛ ላይ ስለ ስነ-ፍጥረት ሲያወራ ህዋው እንዴት እንደተፈጠረ የሚያብራራበት ተመሳሳይነት ነበረው በአገላለፅ። እና  ትንሽ ትንሽ ደግሞ እኔ ከሳይንስ ከማውቀው ነገር ጋር ለማገናኝት ስሞክር መመሳሰሎች አሉ በአገላለጽ ደረጃ። ምናልባት  ሳይንስ ላይ እንደተማርነው «ኤለክትሮን »፣«ፕሩቶን»የሚል ቃላት ላይኖሩ  ይችላሉ፤ ነገር ግን እዚያ ላይ የሚጠቀመው አገላለጽ ና የቃላቶቹ አኳኋን ሳይ  ይህ ነገር ለካስ እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነበር።  እያልኩ  የማነጻጸር ነገር በራሴ አደርግ ነበር።» በማለት አብራርቷል።

Tensae Alemayehu
ምስል Privat

ትንሳኤ እንደሚለው በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስን በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ የሚረዱ በርካታ ልጆች አሉ።ያም ሆኖ  ከሳይንሱ በስተጀርባ ያለውን አመክንዮ በተግባር በተደገፈ ትምህርት እንዲረዱ ማድረግ ላይ ብዙ አልተሰራበትም ባይ ነው።ያ በመሆኑ በአካቢያችን ከሚገኙ ቁሳቁሶች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በመስራት እንዲማሩ ቢደረግ ውጤታማ ተመራማሪዎችን ማፍራት እንደሚቻል ይገልፃል።የህዋ ሳይንስ ዕውቀቱን ለሌሎች ለማካፈል ስልጠናዎችን ይሰጥ በነበረበት ወቅትም ይህንኑ መንገድ ይከተል እንደነበር ይናገራል።
 «የህዋ ሳይንስ ከዕለት ተዕለት ህይወታችን ጋር የተሳሰረ እንጅ የቅንጦትና ያደጉ ሀገራት ብቻ አይደለም።»የሚለው፤ትንሳኤ  የህዋ ሳይንስም እንደማንኛውም ዕዉቀት  ሀብት በመሆኑ ኢትዮጵያም  ልትጠቀምበት እንደሚገባ ይገልፃል።
«ላደጉ ሀገራት እንጂ ለእንደኛ አይነት ታዳጊ ሀገራት አይሆንም ማለት አንችልም።« ቴክኖሎጂካሊ» ሁላችንም እንሻሻላለን ወደፊት እመርታ እናሳያለን። የቴክኖሎጂን መሰረታዊ ትሩፋቶች አንጠቀምም ማለት አይችልም። ለምሳሌ በከተማ የሚኖር ሰው በቀን አንዴ  «ኤቲኤም» ሳይጠቀም  አይውልም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ «ኤቲኤም»  ሚሰራው በ«ፋይበር ኔትወርክ» ነው።ነገር ግን «ባካፑ»  ሳተላይት ኔትወርክ ነው። የምንጠቀማቸው የአልትራ ሳዉንድ  የልብ በሽታ «ፔስ ሜከር»  በሳተላይት ቴክኖሎጂ ምክንያት የመጣ ትሩፋት ነው።ግብርናን እናዘምናለን ካልን ያለ ህዋ ሳይንስ የሚሆን ነገር አደለም። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለኛ አይሆንም ካልን በተዘዋዋሪ መንገድ ጥገኛ እንሆናለን።የሰው ኃይልም ትልቅ «ሪሶርስ» ነው ዕውቀትም ትልቅ «ሪሶርስ» ነው ታላንትም ትልቅ« ሪሶርስ»  ነው።  እነዚህ ነገሮች በሙሉ ነ ጥቅም የሚያስገኙልን ናቸው። እንዲሁ በማይመስል ምክንያት እነዚህን ሁሉ ገሸሽ ማድረጉ ኣግባባ ነው  ብዬ አላስብም። » በማለት የህዋ ሳይንስን አስፈላጊነት በአፅንኦት ገልጿል።
ወጣቱ ከጎርጎሪያኑ  2012 ጀምሮ የኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ አባል ሲሆን፤በመቀሌ ዩንቨርሲቲ ቆይታውም  ከ2018 ዓ/ም ጀምሮ  በኢትዮጵያ  የጠፈር ሳይንስ ማህበረሰብ የመቀሌ ቅርንጫፍ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ ሰርቷል።

Tensae Alemayehu
ምስል Privat

በአሁኑ ወቅትም በሳተላይት ምስሎች ላይ ተመርኩዞ የሰብል ምርቶች እና የጤና ቁጥጥር አገልግሎቶችን በሚሰጠው «ስፔስ ቴክኖሎጂ ፎር ኧርዝ አፕሊኬሽንስ (STEA) »በተባለ መርሃ ግብር ከሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል።
በተባበሩት መንግስታት የህዋ ሳይንስ ድጋፍ በሚደረግለት «ስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዘሪ ካውንስል»በተባለውና  ወጣቶችን የማስተሳሰር ስራ በሚሰራው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ከጎርጎሪያኑ 2013 ዓ/ም ጀምሮ  የኢትዮጵያ  አስተባባሪ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።በአፍሪቃ ደረጃ ሰሞኑን ካገኘው ዕውቅና በኋላ ደግም በድርጅቱ የአፍሪካ አስተባባሪ ሆኖ መመረጡንም አጫውቶናል። ለዚህ ስኬቱ የወላጆቹ እንዲሁም  የሰራባቸውና የተማረባቸው  ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና ችሯቸዋል። ወጣቱ ስለወደፊት ዕቅዱ ሲናገር ለመመረቅ የወራት ዕድሜ ሲቀረው በሀገሪቱ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ የተቋረጠውን ትምህርቱን በመቀጠል የመጀመሪያ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ በትምህርቱ በመግፋት ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪቃ በህዋ ሳይንስ ምርምር ኢንደስትሪ ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የማበርከት ህልም አለው። ለትንሳኤ የወደ ፊት ህልሙ እንዲሳካ እየተመኘን የዛሬውን የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በዚህ ቋጨን። ሰላም።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ አንጋብዛለን።

 

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ