1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሊቢያ ድረሱልን የሚሉት ስደተኞች

ዓርብ፣ ሐምሌ 26 2011

በዚህ በሞቃታማ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪቃ ስደተኞች በሰሜን አፍሪቃ በኩል አድርገው ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት እየሞከሩ ነው።ሌሎች ሊቢያ ላይ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ታግተው የይድረሱልን ጥሪ ያሰማሉ።

https://p.dw.com/p/3NAtB
Libyen Flüchtlinge Schlauchboot
ምስል picture alliance/dpa/Str

በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሊቢያ ውስጥ የታገቱት 45 ስደተኞች

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ የአውሮፕያኑ 2019 ዓም ከገባ አንስቶ ማለትም ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ 800 የሚጠጉ ስደተኞች ባህር ሰጥመው ሞተዋል። በቅርቡ የነበሩትን ክስተቶች እንኳን መለስ ብለን ብንቃኝ  ባለፈው ሳምንት  የሜድትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ ከሞከሩ 300 ስደተኞች ውስጥ 147ቱ በህይወት መትረፋቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ገልጿል።  ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል። ቁጥራቸው እና ዜግነታቸው በውል ያልታወቁት ቀሪ ስደተኞችም አስክሬን እንዲሁ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የ 66 ያህሉ መሰብሰቡ ተዘግቦ ነበር። የሞሮኮ ባህር ኃይልም እንዲሁ ወደ ስፔን በጀልባ በጉዞ ላይ የነበሩ 242 ስደተኞችን መታደጉን ገልጿል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ ባለፉት ሰባት ወራት 37000 የሚጠጉ ስደተኞችን በሜዲትራንያን ባህር በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ ገብተዋል። ቁጥሩ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ35 በመቶ ቀንሳል። ምናልባትም ስደተኞቹ ሌሎች የገጠማቸውን እጣ ፈንታ አገናዝበው ከጉዞ ተቆጥበው ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ  በአሁኗ ሰዓት በአሁኗ ደቂቃ እጃቸው በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ስር ያሉ ስደተኞች አሉ። በታገቱበት ቦታ የተወሰኑትን በስልክ አነጋግረናቸዋል።« 45 እንሆናለን። በተዘጋ ቤት ውስጥ ነው ያለነው። 3500 ዶላር ክፈሉ ተብለን ታግተናል። ሰባት ሴቶች 38 ወንዶች ነን። ኢትዮጵያዊ ፣ኤርትራዊ እና ሶማሊያዊ ነን።»  ይላል ከታጋቾቹ አንዱ።

Libysche Migranten ertrunken
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ahmed

ታጋቾቹ እንደሚሉት ናስማህ በተባለው ቦታ ከአመት በላይ የታገቱ ሰዎች አሉ። ስራ አይሰሩም። በተስፋ የሚያስፈታቸው አካል እየጠበቁ ይገኛሉ።  ቢሳካላቸው ሁሉም ወደ አውሮፓ በባህር ለመሰደድ ነበር አላማቸው ። በአንድ ሊቢያዊ ታግተናል ከሚሉት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ያለችበትን ሁኔታ እንዲህ ገልጻልናለች። « ብር አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ የከፈልን ሰዎች አለን። አንድ ዓመት ከአራት ወር ሆኖኛል። ባህር እንዲያሻግረኝ  6100 ዶላር ከፍያለሁ። » ትላለች።

ሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) የህዝብ ግንኙነት መኮንን ታሪክ አርጋዝ  ለ DW እንደገለፁት ሊቢያ ውስጥ በድርጅቱ ስር የተመዘገቡ 50 000 የሚጠጉ ስደተኞችን ዕለት ከዕለት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።  ከዚህም ሌላ « በዚህ ዓመት ብቻ ከ 1300 በላይ ሰዎችን ወደ አውሮፓ እና ሌሎች ደህንነት የሚያገኙበት ቦታ ከተለያዩ የስደተኞች ማቆያ ለማስወጣት ችለናል። የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በህጋዊ መንገድ ስደተኞቹ ሊቢያን የሚለቁበትን መንገድ እንዲተባበረን እየጠየቅንም እንገኛለን።»

ያም ሆኖ ታሪክ አርጋዝ እንደሚሉት በአሁኑ ሰዓት 5000 የሚጠጉ ስደተኞች በሊቢያ የተለያዩ የስደተኛ ማቆያዎች ይገኛሉ። ከነዚህም 3000 የሚሆኑት እጅግ የሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ናቸው። ይህ ቀደም ሲል ያነጋገርናቸውን በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በየቤቱ ታግተው የሚገኙትን ሰዎች ሳይጨምር ነው። ታሪክ አርጋዝ እነዚህን ታግተው የሚገኙ ስደተኞች ለመርዳት UNHCR ስልጣን የለውም ይላሉ።

Italien - Ankunft libyscher Flüchtlinge in Rom
ምስል Reuters/A. Bianchi

« ይህ የሊቢያ ባለስልጣናት ኃላፊነት ነው ምክንያቱም UNHCR ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነው። እንደዚህ አይነት ወንጀልን መዋጋት ወይም ኃይል መጠቀም አይፈቀድልንም። ኃላፊነትም የለብንም።  የአንድ ሀገር ፀጥታ እና የህብረተሰቡ ደህንነት ማስጠበቅ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ሀላፊነት ነው። እኛ ግን  ስደተኞች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እና ሀገር ውስጥ በሚገኙ ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እንዳይጠቁ እና በደል እንዳይደርስባቸው በተደጋጋሚ በ ህገወጥ የሰው ዝውውር ላይ ክትትል እንዲደረግበት እና እንዲቆም ጥሪ አቅርበናል። »

UNHCR በሊቢያ ማቆያዎች ታጭቀው የሚገኙትን ስደተኞች ሁሉ ወደ አውሮፓ መላክ ስለማይችል ስደተኞቹ ፍቃደኛ ከሆኑ ወደ መጡበት የመጀመሪያ ሀገር የሚመለሱበትንም መንገድ  ከአለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅቶች እና ሀገራት ጋር እየሰራ እንደሆነ ይናገራል።  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለ DW እንደገለፁት ሊቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ 38 ኢትዮጵያውያን  ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

Libyen Hunderte Flüchtlinge in Internierungslager ohne Versorgung
ምስል Reuters/H. Amara

ሊቢያ ውስጥ በይፋ በሚታወቁ እና በሰው አዘዋዋሪዎች ታግተው ያሉ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች በምን መልኩ ወደ ሀገር ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ ቃል አቀባዩ አቶ ነቢያት ሲያስረዱ « ፍቃደኝነቱ ያላቸው ሰዎች ካይሮ በሚገኘው ኤምባሲያችን በኩል መልዕክት እየላኩ… ኤምባሲውም በሚያደርገው ክትትል የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት እንዲደርሳቸው እያደረገ ነው ከሊቢያ እየወጡ ያሉት »ብለውናል።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ