1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሊቢያ የባህር ጠረፍ የሚነሱ ስደተኞች

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 29 2007

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ተነስተው በጀልባ ወደ አውሮፓ በመሰደድ ላይ ናቸው ሰዎችን ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው የሚያሻግሩ ደላሎች ስደተኞቹን በአነስተኛ የሞተርና ጀልባዎች እንደነገሩ በተሰሩ ታንኳዎች አሳፍረው ከላኩዋቸው በኋላ የባህር ዘቦች እንዲታደጓቸው የእርዳታ ጥሪ ያስተላልፋሉ ።

https://p.dw.com/p/1FL9b
Migranten in Libyen
ምስል DW/N. Porsia

አንድ የኢጣልያ ባህር ኃይል መርከብ ትናንት ለሊት በኢጣልያዋ ሲሲሊ ወደ ምትገኘው የፖዛሎ ወደብ የደረሰው በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ከሰጠመ ጀልባ የታደጋቸውን 870 ስደተኞችን አሳፍሮ ነበር ።ከመካከላቸው ባህር ኃይሉ የስደተኞቹን ነፍስ ለማዳን በተሰማራበት ወቅት ወደ ዚህች ዓለም የመጣችው ህፃን ትገኝበታለች ። እናት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ የወለደቻትን ሴት ልጅዋን ፍራንሴስካ ማሪና ብላታለች።እናት የዋም ሆነ ህፃን ልጅዋ የኢጣልያ ባህር ኃይል ባይደርስላቸው ኖሮ አይተርፉም ነበር ።

ከተወሰኑ ቀናት ወዲህ ሮም የሚገኘው የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ማዕከላዊ እዝ በስልክ ተደጋጋሚ የድረሱልን ጥሪ ይቀበላል ። ስደተኞቹ ወደ ማዕከላዊው እዝ የሚደውሉት ደላሎቹ በሰጡዋቸው የሳተላይት ስልኮች ነው ። ከሊቢያ የሚነሱትም በሚሰጣቸው ስልክ ላይ የባህር ዘቡ እዝ ማዕከል ስልክ ቁጥር ይዘው ነው ።ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎች በየአንድ ሰዓት ልዩነት ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ይነሳሉ ።የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM ባልደረባ ፍላቭዮ ዲ ጅያኮሞ እንደሚሉት ከስደተኞቹ የስልክ ጥሪ የሚደርሳቸው የባህር ድንበር ጠባቂዎቹ ሁሉንም ሊታደጉ ግን አይችሉም ።

« አሳዛኙ ነገር በተመሳሳይ ሰዓት ለሚደወሉት ለነዚህ በርካታ የድረሱልን ጥሪዎች በሙሉ ፈጥኖ መድረስ መቻሉ ከባድ ነው ። በዚህ ሳምንት እንደ እድል ሆኖ ትልቅ የሚባል የመስጠም አደጋ አልደረሰም ። ያም ሆኖ ቢያንስ የ10 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። ሆኖም ሚያዚያ ውስጥ የደረሰው ዓይነት በርካታ ሰዎች የሰጠሙበት ከባድ አደጋ ሊደርስ ይችላል የሚለው ስጋት ግን አሁንም አልጠፋም ። ስለዚህ እንደ ማሬ ኖስትሩም ያለ የባህር ላይ የነፍስ አድን ተልዕኮ በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ አለብን ። የአሁኑ ስምሬት ግን በአውሮፓ ህብረት የሚመራ እንዲሆን ነው የምጠይቀው ።»

Bootsflüchlinge vor Italien
ምስል picture-alliance/ dpa

ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በሜዴቲራንያን ባህር ላይ ለተደጋጋመው የስደተኞች እልቂት መፍትሄ ለመሻት ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባኤ ፍሮንቴክስ በተባለው የአውሮፓ ድንበር ጠባቂ ስር የተሰማራውን ትሪቶን የተባለውን የነፍስ አድን ተልዕኮ አቅም ለማሳደግ ውሳኔ አሳልፈው ነበር ።ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያሳሰቡት IOM ን የመሳሳሉ ድርጅቶች እንደ ትሪንቶን በአውሮፓ የባህር ክልል ብቻ ያልተወሰነ ይልቁንም በሊቢያ የባህር ጠረፍ በአስቸኳይ የሚሰማራ የሰብዓዊ ተልዕኮ ሥራ እንዲጀምር ጠይቀዋል ።ፍላቭዮ ጅያኮሞ

«ስደተኞቹ ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚሳፈሩባቸው ጀልባዎች ያረጁ ከበሰበሱ እንጨቶች የተሰሩ ናቸው ይህ ሁሌም ያሳስበናል ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀልባዎቹ አይሰጥሙም ነበር ።የየቅርብ ጊዜዎቹ ጀልባዎች ግን ከሊቢያ የባህር ጠረፍ 48 ኪሎ ሜትር እንደተጓዙ ነው ችግር ውስጥ ወድቀው እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ። »

Symbolbild Flüchtlinge Mittelmeer Ankunft Italien Gebet
ምስል Reuters/A. Parrinello

ደላሎቹ ስደተኞቹን በጀልባ አሳፍረው ወደ አውሮፓ እንዲያቀኑ ሲያደርጉ የአውሮፓ የባህር ጠረፍ ለመድረሳቸው ምንም ዋስትና የላቸውም ። እነዚህ የፕላስቲክ ጀልባዎች ውሐ ከገባባቸው በ10 ደቂቃ ውስጥ ይሰጥማሉ ። እናም በሊቢያ የባህር ጠረፍ ላይ በርከት ያሉ መርከቦች ለጥበቃ መሰማራት እንዳለባቸው ነው ጅያኮሞ የሚያሳስቡት ። በዚህ ሳምንት ሁለት የጀርመን ጦር የመርከቦች የኢጣልያን የባህር ጠረፍ ጠባቂ እያገዙ ነው ። እነዚህ ለባህር አደጋ የነፍስ አድን ስራ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ያሏቸው መርከቦች ክሬታ በተባለው ስፍራ ነው የተሰማሩት ።ከዚህ በተጨማሪም የግል የንግድ መርከቦችም በነፍስ አድኑ ተግባር ጠቃሚ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ።

ቲልማን ክላይንዩንግ

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ