1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦነግ ሸኔ ሰዎችን ገደለ፤እስረኞች አስለቀቀ

ዓርብ፣ ጥር 19 2015

የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደነበር የተናገሩት አንድ የከተማይቱ ነዋሪ “ታጣቂዎቹ ንጋት ላይ ከተማውን በመልቀቅ ተመልሰው ሄደዋል፡፡ ጠዋት ላይ አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ ሦስት አስክሬኖች ወድቀው ይታዩ ነበር ፡፡ የጠቃጠሉ የመንግሥት ተቋማትና ተሽከርካሪዎቹንም አይቼያለሁ “ ብለዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4Mn7y
INFOGRAFIK Äthiopien: Konfliktreiche Grenzregion EN

ኦነግ ሸኔ ጌድኦን ሲያጠቃ የመጀመሪያዉ ነዉ


የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ-ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር አባላት ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች ትናንት ለዛሬ አጥቢያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ በከፈቱት ጥቃት አምስት ሰዎች ገደሉ።የአካባቢዉ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ከሟቾቹ አንዱ የፖሊስ ባልደረባ ነዉ።የገደብ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ደግሞ ታጣቂዎቹ በመንግስት ተቋማት ዉስጥ የነበሩ መኪኖችን አቃጥለዋል፤ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዉ የነበሩ እስረኞችን አስፈትተዋልም።
በከተማው ሁለት አቅጣጫዎች የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደነበር የተናገሩት አንድ የከተማይቱ ነዋሪ  “ታጣቂዎቹ ንጋት ላይ ከተማውን በመልቀቅ ተመልሰው ሄደዋል፡፡ ጠዋት ላይ አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ ሦስት አስክሬኖች ወድቀው ይታዩ ነበር ፡፡ የጠቃጠሉ የመንግሥት ተቋማትና ተሽከርካሪዎቹንም አይቼያለሁ “ ብለዋል ፡፡
በጥቃቱ ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የዞኑ የመንግሥት ኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ አብረሃም መኩሪያ ጥቃቱን ያደረሰው ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተሻግሮ የገባ  “ ሸኔ “ የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው ብለዋል ፡፡
በጥቃቱ አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን  ያረጋገጡት አቶ አብረሃም “ ታጣቂ ቡድኑ በመንግሥትና በነጋዴዎች ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ፡፡ አሁን ላይ የደቡብ ክልል ልዩ ሀይልና የፌዴራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በመድረሱ ከተማው እየተረጋጋ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
መንግሥት ሸኔ በሚል በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት  ሠራዊት በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን  በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡
ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት ዞኑን ከሚጎራበተው የደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በመግባት ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱ የደቡብ ክልል መንግሥት  ሲገልጹ መቆየቱ የሚታወስ ቢሆንም በጌዴኦ ዞን ውስጥ ግን ጥቃት ሲፈጸም የአሁን የመጀመሪያው ነው ፡፡

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ