1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦነግ ሠራዊት በተባሉና በመከላክያ ሠራዊት መካከል ገጭት መከሰቱ

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2011

የኢትዮጵያ መከላክያ ሰራዊት 16 ከባድ ተሸከርካር ላይ ከነሙሉ ትጥቃቸዉ በመሳፈር የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር /ኦነግ/ ስራዊት ተቆጣጥረዉታል ወደ ተባሉባቸዉ ቦታዎች እየተጓዙ እንደሚገኙ በቀለም ወላጋ ዞን በግዳም ከተማ የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ምትኩ ታከለ ለ«DW» ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/37Lh1
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

ከባለፈዉ ቅዳሜ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን በቤግ ከተማና በቀለም ወላጋ ዞን በግዳም ከተማ መካከል በጋራ አካይና ላጋ ሃዳ ጃርሳ በሚባል ቦታ ላይ የኦነግ ስራዊት ናቸዉ በተባሉትና የአገሪቱ መከላክያ ሰራዊት መካከል ግጭት እንደነበረ አቶ ምትኩ ገልፀዋል። ግጭቱ በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ስላለዉ ጉዳይ እንደገለጹት «በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት አደርሰዋል። ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ሱቆች ተሰባብረዋል። ነዋሪዎቹም ነፍሳቸዉን ለማዳን ቀየያቸዉን ጥለዉ እየተሰደዱ ይገኛሉ። በቅርብ የወለዱ እናቶች ህፃናትና የቤተሰብ አባላት ወደ ጫካ እየሸሹ ይገኛሉ። ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ስጋት ዉስጥ ነዉ።» ብለዋል።

የተጎዱ ሰዎች አሉን በሚል ለቀረበላቸዉ ጥያቄም አቶ ምትኩ እስካሁን ወደ ቦታ በመሄድ እንዳላጣሩ ተናግረዉ ግን ሦስት የመከላክያ ሰራዊት ህይወት ማለፉን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በጊዳም ወረደ በቀለም ከተማ ዉስጥ አንድ የአይምሮ ህመመተኛ በመከላክያ ሰራዊት በጥይት ተመቶ መሞቱን መስማታቸዉ የወረዳዉ ፀጥታ ሃላፊ አቶ ምትኩ አክለዋል። ችግሩ እተከሰተ ያለዉ የኦነግ ሰራዊት ናቸዉ የተባሉ ሳይሆኑ የአጋር መከላከያ ሰራዊት ናቸዉም ብለዋል። አቶ ምትኩ- «አሁን ትልቅ ችግር እያደረሰ ያለዉ የኦነግ ሰራዊት ሳይሆን የመንግስት ሰራዊቶች ናቸዉ። በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባለዉን የኦነግ ሰራዊት መሆኑን በቀጥታ የምናዉቀዉ አይደለም። ከሚወራዉ ወሬ ዉጭ ሄደን አላጣራንም፣ አላየንም። »

ግጭቱን አስመልክቶም የክልሉ ፕሬስዳንት አቶ ለማ መገርሳ በትላንትናዉ እለት ባደረጉት ንግግራቸዉ ሁኔታዉ በጣም እንዳሳዘናቸዉ ገልፀዋል።
«ወጣቶች ሦስት፣ አራት፣ አስር የጦር መሳርያ በመታጠቅ ወደ ጫካ ሲሮጡ፣ እዉነት ለመናገር፣ ሊድኑ አይችሉም። ዘመናዊ መሳርያ ከታጠቀዉ ከመንግስት ሰራዊት ጋር ለመወጋት እንዴት ወደ ጫካ እንዲህ ሁኔታ ሰዎች ይሄዳሉ? ይህ ስህተት ነዉ። እዉነቱን ለመናገር፣ ይህ ትግልም ከሆነ፣ ትክክለኛ የትግል ስልትም አይደለም።» ነበር ያሉት። 

«ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች መብት ይከበር፤ በድንበር አከባቢ ለሚፈፀሙ ግጭቶች ከጎናችን የቆመዉ የኦነግ ወታደር ነዉ» የሚል መፈክር የያዙ ወጣቶች ላለፉት ሁለትና ሦስት ቀናት በአከባቢዉ ተቃውሞ ሲያካሂዱ እንደነበረ አቶ ምትኩ ገልፀዋል። ሰላማዊ ሰልፉም በሰላም መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተሳተፈ አንድ የቤጊ ነዋሪ በበኩሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የኦነግ ሰራዊት ያሉበትን ጠቁመዉ በየቤቱ እየሄዱ ሰዉን «እያሸበሩ» ነዉ ብሎአል። በቤጊ ከተማ ዉስጥ የስምንት ሰዉ ህይወት እንዳለፈና ከ80 በላይ ሰዎች መታሰራቸዉን ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀዉ የዓይን እማን ለ«DW» ተናግረዋል። ግጭቱም በቀለም፣ በጋራ አካይ፣ ላጋ ሃዳ ጃርሳ፣ በሆሮና በዋባራ መቀጠሉን ነዋሪዉ አክሎ ገልጾአል።

በምዕራብ ወለጋ ዞንና በቀለም ወላጋ ዞን ዉስጥ ያለዉን የፀጥታ አለመረጋጋት ጉዳይ ላይ ከፌዴራል ባለስልጣናት፣ ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትና ከኦነግ አመራሮች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ