1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18 2010

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተከሰተዉ ግጭት አሁንም ለሰዎች ሞት፣ መፈናቀል፣ መቁሳልና ለንብረት መዉደም ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል የተመሰረተዉ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ ለተፈናቀሉት ሰዎች መጠለያ፣ አልባሳት፣ ምግብና የመጠጥ ዉሃ እያቀረበ መሆኑን በተለያዩ ጊዚያቶች አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/2q0ww
Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt
ምስል DW/J. Jeffrey

Oromia to resettle displaced people - MP3-Stereo

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሼን ሐላፊ አቶ አድሱ አረጋ የተፈናቀሉትን ሰዎች በኦሮሚያ ዞኖችና ከተሞች ዉስጥ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለማስፈር መታቀዱን ባለፈዉ ሰኞ በፌስቡክ ገጻቸዉ ዘግበዋል።

የተፈናቀሉት ሰዎች ቋሚ መጠለያ ማግኘት እንዳለባቸዉ ኮሚቴዉ መወሰኑን የኮሚቴዉ አባል የሆኑት ሼክ አህመድ ዛክር ሼክ አህመድ ሳሌ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ሼክ አህመድ: «ቅድሚያ ልሰጣቸዉ የሚገባዉ ለአባዋራዎች መሆኑ ተወስነ። ከዛ ዉስጥም 10ሺሕ አባዋራዎች ተመልምለዋል። ባጠቃላይ ወደ 50ሺሕ ሰዎችን ለማስፈር ዝግጅት እያደረግን፤ ቦታዎቹን እያመቻቸን እንገኛለን።»

ሰዎቹን ለማስፈር የተመረጡት ቦታዎች ከፍንፍኔ-አዳማ መካከል የምገኙ ከተሞች መሆናቸዉ እንድ ሲሉ ሼክ አህመድ ይናገራሉ፣ «አዳማ 1000 አባዋራዎች፣ ሞጆም 1000፣ ቢሾፍቱም 1000፣ ዱካም 1000፣ ገላን 1000፣ ሰባታ፣ ቡራዩ፤ ሱሉልታና ላጋጣፎም ይሄን ቁጥር ያላቸዉ አባራዎችን የማስፈር ስራ ላይ እንገኛለን። ሁለት ሺሕ አባዋራዎችን ደግሞ በፍንፍኔ ላይ ለማስፈር ከሚመለከታቸዉ የከተማዉ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረን ነዉ።»

በጅግጅጋ በንግድ ስራ ላይ ተሳትፎ እንደነበረ የሚናገረዉ ደረጀ ጌታቸዉ አሁን በአዲስ አበባ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በጎታራ ቅርንጫፍ ላለፍቱ ሶስት ወራት ሰፍሮ እንደሚገኝ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራል። በግቢዉም ዉስጥ 2000 አባዋራዎች አሉ ግን የቤቴሴብ አባላት ወደ 6000 ሰዎች እንደሚደርሱም ጠቅሰዋል።

ይህን ኮሚቴዉ ፈልጎ ሳይሆን የተፈናቃዮቹ ምርጫ ነዉ ይላሉ ሼክ አህመድ። ከሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የመጡ ባለሙያዎች የተፈናቃዮችን ፍላጎት ሲጠዩቁ በደሕንነት ሥጋት ምክንያት ወደ ቀድሞ ቦታቸዉ መመልስ እንደማይፈልጉና ከላይ የተጠቀሱት ቦታዎች መስፈር እንደምፈልጉ ተረጋግጦ እንደሆነ ሼክ አህመድ ጨምሮበታል። በተጠቀሱት ቦታዎች ቀደም ብሎ የዉሃ፣ መንገድና የኤሌክትሪክ መስመሮች ቢኖሩም የመኖርያ ግንባታና ቀሪዉን አገልግሎቶች በተመለከተ  እንዲሕ ይላሉ፣ «ለአንድ አባዋራ የሚሰጠዉ መሬት 105 ካሬ ሜትር ነዉ። ከዚህ መሬት ዉስጥ በ40 ካሬ ሜትር ላይ ቤቱ ይገነባል። በዚህ መሬት ላይ ለጊዜዉ የቆርቆሮ ቤት ነዉ የሚሰራላቸዉ። መፀዳጃ ቤት አንድ ይገነባና በቱቦ ከየቤታቸዉ ወደ ጉድጓዱ እንድገባ ይደረጋል።»

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወደ ዱሮ ቦታቸዉ እንዲመለሱ ማስገደድ መብት የለዉም የሚሉት ሼክ አህመድ ክልሉ ያለዉ ሃላፊነት የነሱን ደሕንነት እና በቀድሞ ቦታቸዉ ላይ ያለዉ ሃብታቸዉን የማስጠበቅ መሆኑን ይናገራሉ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ