1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንግዳችን፤ ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 15 2013

ኢትዮጵያ ከጎርጎረሳዉያኑ 1935 ዓም ጭፍጨፋና አስከፊ ወረራ እስካሁን አልዳነችም። ቁስሏ አሁንም አልሻረላትም። ኢትዮጵያዉያንም  ስለጣልያን ወረሪ ታሪክ ለመወያየት እና ለማዉራት እስከዛሬም እድሉን አላገኙም። በጣልያን ወራሪ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ስለተካሄደዉ የጭካኔ ተግባር ይቅርታ አልተጠየቀችም።  

https://p.dw.com/p/3mwQo
Maaza Mengiste - äthiopische Schriftstellerin
ምስል Imago/Leemage/L. Cendamo

ኢትዮጵያዉያን እስከዛሬ ይቅርታ አልተጠየቁም

በምዕራቡ ዓለምም ሆነ በምኖርበት አሕጉር ዉስጥ ያለዉን የሥነ-ጽሑፍ ዘይቤ ማወቅ በመቻሌ  ለእኔ ሕልሜ ተሳክቶአል ማለት እችላለሁ። ይሁንና አሁንም በኢትዮጵያ ገና ያልወጡ ያልታዩ በጣም  ብዙ ጸሐፍት እንደሚገኙ አምናለሁ ።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ- አሜሪካዊት መዓዛ መንግሥቴ  ናት። 'ዘ ሻዶው ኪንግ' [The Shadow king] በሚል ርዕስ በእንጊሊዘኛ ለአንባቢያን ያቀረበችዉ መጽሐፍ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2019 ዓም ለአንባቢ የታተመው መፅሐፏ የተለያዩ የሥነ-ፅሑፍ ሽልማቶችን አግኝቶአል። “ዘ ቡከር ፕራይዝ”፤'ቡከር ሚክኮኔል ፕራይዝ'በመባል የሚታወቀዉ  በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተፅፈው በብሪታንያ እና አየርላንድ ለህትመት የበቁ የልቦለድ ስራዎችን የሚሸልመዉ ድርጅት የትዉልደ ኢትዮጵያዊትዋን መጽሐፍ ምርጥ ሲል ዘንድሮ ለሽልማት አጭቶት ነበር።  ደራሲ መዓዛ  በመጽሐፉ ላይ የተጠቀመችው አጻጻፍ እና የቋንቋ ብቃት በአንባብያን ብሎም በሃያሲያን  አድናቆትን አስገኝቶለታል።  ትዉልደ ኢትዮጵያዊትዋ ደራሲ የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኘችበት ለሽልማት የታጨችበት “ዘ ሻዶው ኪንግ” ከ85 ዓመታት በፊት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሴት የነጻነት ታጋዮች የነበራቸውን ግዙፍ አስተዋፅኦ ግን ደግሞ በታሪክ ፊት ቸል የተባለ ሚና ስለተሰጣቸዉ ጉዳይ ያነሳል። ደራሲ መዓዛ እንደተናገረችው መጽሐፉን ስትጀምር ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት ጣልያን ጋር ባደረጉት ተጋድሎ ላይ ልታተኩር ብታቅድም በጥናት እና ምርምር ወቅት ያገኘቻቸው መረጃዎች አስደናቂ ሆነው የትኩረት አቅጣጫዋን አስቀይረዋታል።

2020 Booker Prize Awards Ceremony
ምስል David Parry/dpa/picture alliance

« አዎ ፣ በእውነቱ በጣም አስጨናቂ ነበር ።  ከሩቅ ሆኖ መመልከት ደግሞ ነገሩን  ይበልጥ አስጨናቂ ያደርገዋል። ትኩረት የተነሱ፤ በችግር ፤በድህነት የሚኖሩ ሰዎች  እንዳሉ  ማወቁ በራሱ ያስጨንቃል። የእነዚህ ሰዎች ለገዛ ራሳቸዉ እና  ለቤተሰቦቻቸው የሰነቁት ተስፋ እና ህልም መጨለሙን ማወቁና ማየቱ በራሱ ያስጨንቃል። እዚህ ሰዎች እኮ እየሞቱም ነዉ። »      

ኢትዮጵያዊትዋ ደራሲ የመዓዛ መንግሥቴ ሁለተኛ ልብ ወለድ መጽሐፍ የሆነው “ዘ ሻዶው ኪንግ” በሚል ሴቶች የታሪክ አካል ተደርገው አይቆጠሩም፤ በታሪክነትም አንመዘግባቸውም በሚል በተለይ የጣልያን ወራሪ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት  ሴቶችን ያደረጉትን ተጋድሎ ያጎላችበት ነዉ።  ይህ መሐፍዋ ለመጨረሻው ዙር የቡከርስ ሽልማት ውድድር ያለፈው ከ162 ልቦለዶች ጋር ተወዳድሮ እንደሆነ ተዘግቦአል። መጽሐፉን ለመጨረሻው ዙር ያጨው አምስት ሰዎች የነበሩበት የዳኞች ኮሚቴ አባል አንዱ  ትውልደ ኢትዮጵያዊው ብሪታንያዊ ታዋቂዉ ገጣሚ ለምን ሲሳይ ነበር። ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዜናዎችን በመከታተል ላይ መሆንዋን የገለፀችዉ ደራሲ መዓዛ መንግስቴ   ስለኢትዮጵያ መጨነቅዋን እንዲህ ነበር የገለፀችዉ።

«በጣም አስጨናቂ ወር ነዉ። ይህን አስጨናቂ ጊዜ ደግሞ ዓለም እየተከታተለዉ መሆኑ ግልጽ ነዉ። ልክ ከነበረዉ ጦርነት ይሄኛዉ አንዱ ክፍል አይነት ነገር ነዉ የሚመስለዉ። በ 2020 ዓመት የተካሄደ አይነት።»

ደራሲ መዓዛ በጦርነት የሕጻናት ጭንቀት የአዛዉንቶች የሴት የሕሙማን የወጣት ጭንቀት ሁሉ በምናብዋ እንደሚመጣ ትናገራለች። ጣልያን ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የሕጻናቱ ምኞት በጦርነት መቀጨቱ ዛሬም ይሰማታል።

«የሚገርም ነገር ነዉ ። ጦርነት ስለሰዉ ልጆች ማንነት፤ ስለሰዉ ልጆች ሁኔታ ፤ ምን ሊነግረን እንደሚችል ማየቱ በጣም አስገራሚ ነዉ። ስለፍርሃታችን ፤ ስለፍቅራችን ፤ ስለምኞታችን እና ስለ ህልማችን አስበን የጦርነትን ምንነት አይቶ መግለጽ መቻል አስገራሚ ነገር ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 1935 ዓ.ም የጣልያን ጦር ኢትዮጵያን ለመዉረር በሞከረበት ጊዜ የተካሄደዉ ጦርነት በተፈፀመበት ክልል ነዉ፤ ዛሬም ግጭት ተቀስቅሶ ጦርነት የተካሄደዉ። ስለዚህም ዛሬ ባለንበት 2020 የጎርጎረሳዉያን ዓመት በክልሉ የሚሆነዉ ነገር እያየሁ ፤ ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ስለተዋደቀችበት ጊዜ ስለዚሁ ቦታ አስባለሁ።»  

የቡከርስ ሽልማት በእንግሊዘኛ ተናጋሪው ዓለም ከፍተኛ ተቀባይነት ብሎም ክብር የሚሰጠው ሲሆን ላለፉት 50 ዓመታት ምርጥ ለተባሉ ልብወለዶች እውቅናን እና ተነባቢነትን እንዳስገኘ ይነገርለታል።  ከፍተና እዉቅናን ባገኘሽበት መጽሐፍሽ ዋንኛ ገፀ ባሕሪ ሴቶች ናቸዉ፤ ይህን ለማድረግ ለምን መረጥሽ ስትል የዶቼ ቬለዉ የኢንጊሊዘኛ ቋንቋ ክፍል ጋዜጠኛ ያቀረበችላት ጥያቄ ነበር።

Buchcover | The Shadow King von Maaza Mengiste
ምስል WW Norton & Co

«ስለጦርነት ስናወራ እዉነታዉን ማሰብ እፈልጋለሁ። ስለግጭት ስንናገር ፤ ስለ ወታደሮች እናስባለን። ጦርነቱ ዉስጥ የሚሳተፉት ወንድ ወታደሮች ናቸዉ ብለን እናስባለን። ነገር ግን በጦርነቱ ሴቶችም ሆኑ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊ ሴቶች ጉዳት ይደርስባቸዋል። በኢትዮጵያ በጎርጎረሳዉያኑ 1935 ዓ.ም  ወራሪ ጣልያንን ለማባረር እና የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመጠበቅ በማሰብ ሴቶች ወደ ጦር ግንባር መዝመት እንዳለባቸዉ ተገንዝበዉ ዘምተዋል። በመጸሐፊ ይህን ታሪክ ለማሳየት የፈለኩት  ሴቶች በጦርነት ላይ ሴቶች ያላቸዉን ተሳትፎ በበቂ ሁኔታ ስለማንናገር ፤ እዉቅና ስለማንሰጥ ነዉ። »    

ከዚህ ቀደም ታትሞ ለንባብ የበቃው “ቢኒትዝ ዘ ላየንስ ጌዝ (Beneath the Lion’s Gaze) የተባለዉ የደራሲ መዓዛ አንደኛ ልቦለድ የኢንጊሊዘና መጽሐፍ በአንባቢያን ዘን ከፍተኛ ተወዳጅነትን አግኝቶአል። መዓዛ ከቀናት በኋላ በሚገባዉ 2021 ዓመት ጣልያን ዉስጥ ሦስተኛ መጽሐፍዋን ለአንባቢ ለማብቃት ዝግጅት ላይ ናት። የዶቼ ቬለዋ ጋዜጠኛ ደራሲዋ ለምን በጣልያን ይህን መጽሐፍ ይፋ ማድረግ እንደፈለገች ጠይቃታለች።      

«አዎ በጣልያን እጅግ ብዙ ምርምር እና ጥናት አካሂጃለሁ። ይህ ታሪክ የጣልያን ታሪክ ነዉ። ግን ደግሞ ይህን ታሪክ አብዛኞች ጣልያናዉያን አያዉቁትም  አልያም ስለታሪኩ መስማትም ሆነ ማንሳት በጣም ምቾት አይሰጣቸዉም።  ይህን ታሪክ በተመለከተ በጣልያን የሚካሄድ ዉይይት ንግግርን እቀበላለሁ። ታሪኩን በተመለከተ ጣልያናዉያን የጀመሩትን  ዉይይት ላይ ለመካፈል በጣም ጓጉቼአለሁ። በነገራችን ላይ ይህ ይረሳል ተብሎ የታሰበ ታሪክ ነዉ። »  

መጸሐፉን ስጀምረው ዋነኛ ፍላጎቴ የጣልያንን ወረራ በተመለከተ መፃፍ ነበር ስትል የገለፀችዉ ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ የጣልያን ጦር ከአፍ እስከ ገደፉ በመሳሪያ ቢታጠቅም ለነፃነት ሲባል ስለታገሉና ስለተዋደቁ ኢትዮጵያውያን እና ከአምስት ዓመት የመራራ ትግል በኋላ ማሸነፍ ስለቻሉት ኢትዮጵያውያንን ነበር መዘከር የፈለግኩት ስትል መዓዛ ተናግራለች ። ታሪኩን መፃፍ ስጀምርም የተገነዘብኩት ነገር ቢኖርና የበለጠ የሳበኝ ነገር ቢኖር የግል ታሪኮች፣ የቀን ተቀን ኑሮ፣ ግንኙነት ነበርም ብላለች። ጦርነቱ እንደዚያ በተፋፋመበትና በተጋጋመበት ወቅት በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውን የቀን ተቀን ህይወትና፣ የርስ በርስ ግንኙነት የበለጠም ስቦኛል ስትል ገልጻለች። በዚህ ሁሉ ቀውስ መካከል ኑሮ ምን ይመስላል የሚለውን ማሰላሰል ጀመርኩ ስትልም ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ ተናግራለች።  ኢትዮጵያዉያን ከጣልያን የግፍ ጭፍጨፋ አገግመዋል? የአሁኑስ ጦርነት ? በየዶቼ ቬለዋ የኢንጊሊዘኛ ክፍል ጋዜጠኛ ለደራሲ መዓዛ  ያቀረበችላት የመጨረሻ ጥያቄ ነበር።

Maaza Mengiste | Schriftstellerin
ምስል picture-alliance/dpa/Photoshot

«ኢትዮጵያ በጎርጎረሳዉያኑ 1935 ዓም ጭፍጨፋና አስከፊ ወረራ ታሪክ አሁንም አልዳነችም። ቁስሏ አሁንም አልሻረላትም። ኢትዮጵያዉያንም  ስለጣልያን ወረሪ ታሪክ ለመወያየት እና ለማዉራት እስከዛሬም እድሉን አላገኘችም። ስለዚህ አስከፊ ታሪክም እስካሁን ኢትዮጵያ ይቅርታ አልተጠየቀችም። በጣልያን ወራሪ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ስለተካሄደዉ የጭካኔ ተግባር ይቅርታ አልተጠየቀችም።  ኢትዮጵያ ዉስጥ በጎርጎረሳዉያኑ 1935 ጦርነት ነበር። ከዝያም በመቀጠል 1974 አብዮቱ መጣ ። በ1935 የነበሩ ሰዎች በመቀጠል የ 1974 ዓመቱን አብዮት  ኖሩት፤ ከዝያም ይኸዉ ዛሬ 2020 ዓመት ላይ ደርሰናል።  ሕዝብ ይህን ሁሉ ታሪክ ያስታዉሳል። እና እዚህ ላይ የምንገነዘበዉ፤  የተደራረበ ትዉስታ፤ የተደራረበ ሕመም እና ቁስል ግጭትን ነዉ። ይህን ሁሉ ታድያ ገና አላወራነዉም አልተነጋገርንበትም አልፈታነዉም።»   

መፅሐፉን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለመጨረስ አስር ዓመታት እንደወሰደባት የምትናገረዉ ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ  ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመታት  አትኩሮትዋ ምርምሩ ላይ እንደነበር ትናገራለች። ጥናቱን ለማካሄድ ጣልያንኛ ቋንቋ aአተርጓሚ ከመፈለግ ቋንቋዉን ብማር ብላ ተምራለች።  ከዝያም ጣልያን ዉስጥ በተለይም ወደ ጣልያን ዘምተዉ የነበሩት የወታደሮች ልጅ፣ ልጆች አናግራለች፤ መረጃን አሰባስባለች። ከዝያም ታሪኩን በደንብ በአዕምሮዋ እንደገባ ፤ ሴት አያቶችዋ አጎቶችን ወራሪዉን ጦር በመዋጋታቸዉ ታሪኩን የግልዋ ታሪክ እንዳደረገችዉ በኩራት ትናገራለች። መዓዛ መጽሐፉን ስትጽፍ ወደ ጣልያን ብቻ ሳይሆን ወራሪ ጣልያን ኢትዮጵያን የወጋበት አካባቢን ሁሉ ከወላጅ እናትዋ ለአስር ቀናት እየዞረች መጎብኘትዋንም ተናግራለች። ደራሲ መዓዛ መንግሥቴን በማመስገን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን ሙሉን ቅንብር እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ