1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ክብር ከሌለው የፖለቲካ አዙሪት የምትላቀቀዉ መቼ ነዉ?

እሑድ፣ ሰኔ 26 2014

ፖለቲካችን በጎሳ የተቃኘ ፖለቲካ በመሆኑ የቀነጨረ ነዉ። ቤተ መንግሥት የሚገኘዉ መንግሥት ራሱ፤ ነገ በዚህ አደጋ ላይ አለመዉደቁ የሚያስተማምን ነገር የለም። መንግሥት የራሱን ሹማምንት ከወንጀለኞቹ ጋር አለመሳተፋቸዉን መፈተሽ ይኖርበታል። መንግሥት ነገሩን ክብደት ሰጥቶ የኃዘን ጊዜ ባለማወጁ ነገ ይቅርታ ይጠይቅበታል ብለን እናምናለን።

https://p.dw.com/p/4DZJ1
Symbolbild I Kerzen Licht
ምስል privat

«በብሔር ተኮሩ ግድያ እንድንፈራና እና እንድንባንን እየተደረግን ነዉ»

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለምን በሰብዓዊነት ላይ ትኩረቱን አላደረገም? ሲል ነዉ የዛሬዉ ዉይይታችን የሚያጠይቀው፡፡ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በአማራ ንጹሃን ላይ አነጣጥሮ የተፈጸመው ግድያ ሰፊ ቁጣን የቀሰቀሰና ድንጋጠሬንም የፈጠረ ነዉ፡፡ ግድያውን መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ፈፅሞታል ሲል መንግስት ከሷል፡፡ በእርግጥ ከጥቃቱ ያመለጡና አስተያየታቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ጋሩ  የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንኑን ነው ያረጋገጡት፡፡ ይሁንና ነፍጥ አንግቦ መንግስትን የሚዋጋው ኦነግ ሸኔ የተባለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር፤ ግድያው የተፈፀመው  በመንግስት ታጣቂዎች  ነው ሲል፤ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል አድንዲያጠራ ጠይቋል። 

ያም ሆነ ይህ  በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረው የቅርብ ጊዜው የምዕራብ ወለጋው ጥቃት በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ላለው የፖለቲካ ምስቅልቅል አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።  በሌላ በኩል ፤ ጭፍጨፋዉ  በመቶዎች  የሚቆጠሩ  ሰዎች  ቢገደሉም  መንግሥት  ለድርጊቱ  በቂ  ምላሽ  አልሰጠም፤ ብሔራዊ የኃዘን ጊዜም አላወጀም፤ ከጥቃቱ  የተረፉትን  ለማፅናናት ባለስልጣናት ወደ ቦታዉ አልሄዱም። ሲሉ ብዙዎች ቅሬታቸዉን እየገለፁ ነው፡፡የሀገሪቱ ትልቁ የህግ አውጭ ተቋም  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቢሆን፤ጉዳዩ አሳስቦናል ያሉ የህዝብ እንደራሴዎች መንግስት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥና ምክክር እንዲካሄድ ቢወተዉቱም ምክር ቤቱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በማለት በጉዳዩ ያዘኑ እና የተቆጡም ጥቂቶች አይደሉም።  በሌላ በኩል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግድያዉን በማዉገዝ መንግሥትን ተጠያቂ ቢያደርጉም፤ ከጥቃቱ ለተረፉ ሟች ቤተሰቦች ያደረጉት ምንም ሰብዓዊ ድጋፍ አልታየም ተብለው ይተቻሉ፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብዓዊነትን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጉት ነዉ ሲሉ የሚተቹም አሉ።  በፖለቲካው ተሳትፎ ያላቸው ሙህራንም ቢሆኑ  ደሃዉን  በተለይም አርሶ  አደሩን  የፖለቲካ መጠቀሚያ ከማድረግ በዘለል፤ ለጎሳ  ግጭት፣ ለድህነትና ለጅምላ ጭፍጨፋ ዳርገውታል ብለው የሚተቹም አሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩረቱን ሰብዓዊነት ላይ ያላደረገዉ ለምንድን ነዉ? ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ክብር ከሌለው የፖለቲካ አዙሪት እንዴት ትወጣ ይሆን? የዛሬው የውይይታችን ትኩረት ይሆናል፡፡

በነዚህ ነጥቦች ላይ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉንና የችግሩን መነሻ ተንትነው መፍትሔ አመላካች ውይይት እንዲያደርጉ የጋበዝናቸዉ እንግዶቻችን፤ አቶ አበበ አካሉ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ዋና ፀሐፊ ። በፈቃዱ ኃይሉ፤ የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል መስራች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች። አቶ ቸርነት ወርዶፋ፤ የሕግ ጉዳይ ምሁርና እና ጠበቃ፤ እንዲሁም  አቶ ያሬድ ኃይለማርያም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸዉ። ተወያዮች ሃሳባችሁን ለማካፈል ስለቀረቡ በዶቼ ቬሌ ስም እና በማመስገን ሙሉዉን ዉይይት እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ