1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነ ጃዋር መሐመድ አስር "ተደራራቢ ክሶች" ተመሰረተባቸው

ቅዳሜ፣ መስከረም 9 2013

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24 ሰዎች "በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት አስር ተደራራቢ ክሶች" እንደተመሠረተባቸው አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3iib1
Äthiopien Addis Abeba Oppositionsführer Jawar Mohammed
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 24 ሰዎች ላይ "አስር ተደራራቢ ክሶች" መመሥረቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ። ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ማግሥት የታሰሩት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ  እንዲሁም አቶ ሐምዛ አድናን ክስ ከተመሠረተባቸው መካከል እንደሚገኙበት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ እና የቴሌቭዥን ጣቢያው ጋዜጠኛ አቶ ደጀኔ ጉተማ፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የነበሩት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ፣ መቀመጫቸውን በአውስትራሊያ ያደረጉት አቶ ጸጋዬ ረጋሳ በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ "በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ  እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ" ክስ እንደተመሠረተባቸው አስታውቋል።

በመግለጫው መሠረት እነ አቶ ጃዋር "የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ" የመተላለፍ ክሶች ጭምር ተመስርቶባቸዋል።

ባለፈው ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. "በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215 አስር ተደራራቢ ክሶች" መመሥረቱን የገለጸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ "ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል" ብሏል።