1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

እቁብዎን በእጅ ስልክዎ

ረቡዕ፣ መጋቢት 8 2013

ዮሐና ኤርሚያስ እና አሌክሳንደር ይስሐቅ የመሰረቱት ኩባንያ ኢትዮጵያውያን እቁብ የሚጥሉበትን በእጅ ስልክ ላይ የሚጫን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። መተግበሪያው ይፋ በሆነባቸው አጭር ቀናት 200 ገደማ እቁቦች መቋቋማቸውን የሚናገሩት የኩባንያው መስራቾች በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የተጠቃሚዎች ቁጥር 30 ሺሕ እንዲደርስ አቅደዋል።

https://p.dw.com/p/3qmDC
Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
ምስል eQUB financial technologies

ከኤኮኖሚው ዓለም፦እቁብዎን በእጅ ስልክዎ

እቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ የተባለ ጀማሪ ኩባንያ ተለምዷዊውን ተዘዋዋሪ የቁጠባ እና ብድር ማቅረቢያ ሥርዓት በእጅ ስልኮች ለመከወን የሚያስችል መተግበሪያ ሰርቶ ይፋ አድርጓል። ኩባንያው የተመሰረተው በዮሐና ኤርሚያስ እና አሌክሳንደር ይስሐቅ ሲሆን መተግበሪያው ሥራ ላይ ከዋለ አስር ቀናት ገደማ አልፎታል። እስከ ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ከ1400 በላይ ተጠቃሚዎች ተመዝግበው ከ200 በላይ እቁቦች መመስረታቸውን የኩባንያው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ዮሐና ኤርሚያስ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ዮሐና ኤርሚያስ "እቁብ መተግበሪያ የእቁብ ሰብሳቢዎች እና የእቁብ ተሳታፊዎች የሚገናኙበት ፕላትፎርም ነው። እንጂ እቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ራሱ እቁብ ፈጥሮ የሚያንቀሳቅሰው የለም። እኛ እቁብ ሰብሳቢዎች እና ተሰብሳቢዎች ተገናኝተው ብራቸውን የሚጥሉበት፤ ማን ከፍሏል? ማን አልከፈለም የሚታይበት፤ እጣ የሚወጣበት፤ ሰዎች የሚገባበዙበት ፕላትፎርም ነው የፈጠርንው" ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ መተግበሪያ እቁብተኛ ለመሆን መጀመሪያ መተግበሪያውን ከጉግል አፕ ስቶር ወደ ስልክ በማውረድ መጫን ያስፈልጋል። ለመመዝገብ ስልክ ቁጥር፣ የኢ-ሜይል አድራሻ፣ የትውልድ ቀን፣ የመኖሪያ አድራሻ እና በመንግሥት የተሰጠ መታወቂያ ማቅረብ ያስፈልጋል። ተቋሙ ያዘጋጀውን ውል መሙላትም ሌላው ግዴታ ነው።  ከዚያ በኋላ እቁብ ማቋቋም ወይም ቀደም ብለው የተቋቋሙ እቁቦችን መቀላቀል ይቻላል።

Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
የእቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ተባባሪ መስራች እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ዮሐና ኤርሚያስ ምስል eQUB financial technologies

የእቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ተባባሪ መሥራች እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ዮሐና ኤርሚያስ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ይኸው ተዘዋዋሪ የቁጠባ እና ብድር ማቅረቢያ ሥርዓት ያሉበት እንከኖች በመፈተሽ ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። "ባሕላዊው እቁብ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር የሚበዛበት ነው። በአገር ውስጥ ባንኮቻችን በሚገኙ በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች አባላት በቀላሉ ወደ እቁቦቻቸው ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ [መተግበሪያው] ያስችላል" ሲሉ ሌላኛው የኩባንያው ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሌክሳንደር ይስሐቅ ተናግረዋል።

በባንኮች የሚከፈቱት "ልዩ የእቁብ የባንክ አካውንቶች" አቶ አሌክሳንደር እንደሚሉት "የሰብሳቢው፣ የዳኛ እና የጸሐፊን ሚና የሚያቀሉ የአባላቶቻቸው ክፍያ በሰዓቱ ተከፍሏል ወይ? አልተከፈለም የሚለውን የቁጥጥር ሥርዓት" ያቀፉ ናቸው።

በተለምዷዊው እቁብ እጣ አወጣጥ "ሰብሳቢዎች ለመረጡት ሰው የመስጠት ሒደት እንዳለ ተረድተናል" የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ቴክኖሎጂን በመጠቀም "ገለልተኛ የሆነ የሎተሪ አወጣጥ ሥርዓት በመተግበሪያው ላይ አዘጋጅተናል" ብለዋል። ይኸንን የእጣ አወጣጥ ሥርዓት "ሰብሳቢዎችን ከጥያቄ የሚያድን እቁብተኞችንም ሐሳብ እንዳይገባቸው የሚያደርግ" ሲሉም ይገልጹታል። እጣ የወጣላቸው እቁብተኞች ገንዘቡን መውሰድ ካልፈለጉ በጨረታ ዕድሉን ለሌላ እቁብተኛ የሚያስተላልፉበት ሥርዓትም ተዘርግቶለታል።  

አቶ አሌክሳንደር እንደሚሉት ተቋማቸው በመተግበሪያው አማካኝነት በሚቋቋሙ እቁቦች የሚጣል የገንዘብ መጠን ላይ አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ገደብ አልተደረገም። "እቁብ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መሆን መቻል ይኖርበታል። አምስት ሳንቲም መጣል የሚችል ሰው ከሌሎች አምስት ሳንቲም መጣል ከሚችሉ ሰዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን አንድ ብር ማግኘት እንደሚችል እኛ ተረድተን፤ ያቺ አንድ ብር ዋጋ እንዳላት እና ማንንም ማህበረሰብ ይኸኛው ከዚህኛው ብለን ሳንለይ ለሁሉም ተገልጋይ የሚያደርግ ነው። ወደ ላይ ከፍ ባለ ቁጥር ደግሞ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ይኖራሉ። በባንኮችም በኩል የተሻለ ወለድ ሊሰጣቸውም ይችላል። ስለዚህ ለጊዜው ያስቀመጥንው አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ገደብ የለም" ብለዋል።

ይኸን መተግበሪያ በመጠቀም ለጊዜው እቁብ መጣል የሚችሉት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ብቻ ናቸው።  ቪዛን ከመሳሰሉ የክፍያ ሥርዓቶች ጋር ተቋማቸው እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ዮሐና በቅርብ ጊዜ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ግልጋሎቱ እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
የእቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሌክሳንደር ይስሐቅምስል eQUB financial technologies

በፈረንሳይ ኒዎማ ቢዝነስ ትምህርት ቤት በመምህርነት የሚያገለግሉት እና ከዚህ ቀደም በእቁብ ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ፋይዳ ላይ ጥናት የሰሩት ዶክተር ብስራት አገኘሁ "እቁብ በመተግበሪያ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም፤ ገርሞኛል" ሲሉ እቁብ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ይዞት ብቅ ባለው የሥራ ሐሳብ መደነቃቸውን ይገልፃሉ።

ዶክተር ብስራት የእቁቦችን አሰራር የሚያግዝ መተግበሪያ መሥራት እና ተቋሙን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል በመቀየር ሰዎች ሳይገናኙ እንዲከወን ማድረግ የተለያዩ ናቸው የሚል ዕምነት አላቸው። "እቁቦች እየሰሩበት ያሉበት አሰራር ወደ ዲጂታል እንዲያመጡት፤ የሥራ አመራሩን የሚያግዝ መተግበሪያ መስራት እና ተቋሙን ራሱን ወደ ዲጂታል ቀይሮ ሰዎች ሳይገናኙ በዲጂታል ዓለም ብቻ የእቁብን ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ሁለት የተለያዩ ነገሮች መስለው ይታዩኛል" ይላሉ።

"እቁብ ከገንዘብ በላይ ነው። ማሕበራዊ ጎኑ ያደላል። ሰዎች ለምን እቁብ ይገባሉ? ብለህ ስታስብ የግድ ቅልጥፍና ፈልገው ላይሆን ይችላል። እቁብን እቁብ የሚያደርገው ኢ-መደበኛ ጠባዩ ነው፤ የማሕበራዊ ግንኙነቱ ነው" የሚሉት ዶክተር ብስራት "እቁብን እንደ ተቋም ወደ ዲጂታል ለመውሰድ መሞከር ትንሽ የሚያስቸግር ይመስለኛል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።  

አቶ አሌክሳንደር መተግበሪያውን አማርኛን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግልጋሎት መሥጠት እንዲችል ኩባንያቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ኩባንያው "በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት" እስከ 30 ሺህ እቁብተኞች በመተግበሪያው እንዲጠቀሙ የማድረግ እቅድ አለው። አቶ አሌክሳንደር በእንግሊዘኛ የተዘጋጀው እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤ ባላቸው ዜጎች ላይ ያተኮረው ግልጋሎት በሒደት እንደሚያድግ አስረድተዋል።

"መጀመሪያ የለቀቅንውን መተግበሪያ በመመልከት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀት ያለው ማሕበረሰብ ላይ ያተኮረ ሊመስል ይችላል። የእኛ አመለካከት ገጠር ያለው ሰው የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ነው የምንፈልገው። አላማችንም ይኸ ነው" የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሒደት "ቀላል የሆነውን አጠቃቀም" የቴክኖሎጂ እውቀታቸው የዳበረ ላልሆነ የማሕበረሰብ ክፍሎች የማድረስ ውጥን እንዳላቸው ገልጸዋል።  

Äthiopien Addis Abeba eQUB financial technologies
ምስል eQUB financial technologies

ተለምዷዊው እቁብ በእምነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ኢትዮጵያውያንን ሲያገለግል ቆይቷል። እቁቦች ሲቋቋሙ በሰፈር በአገር ልጅነት አሊያም አባላቱ በሚጋሯቸው ተቋማት እና የጋራ እሴቶች ላይ ተመስርተው ነው። "እነዚህ መተግበሪያዎች የሚያግዙት ተቋማቱን በሚሰሩት ሥራ መዝገብ ለመያዝ ወይም `የመክፈያ ቀንህ ደርሷል` የሚል መልዕክት በመላክ ሰዎች እንዲከታተሉ፤ መረጃ እንዲመዘገብ በማድረግ የተሻለ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይኸ ምንም ጥያቄ የለውም" ሲሉ ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽዖ የሚያብራሩት ዶክተር ብስራት "ተያዥ" በማቅረብ እጣ የወጣላቸው ሰዎች ገንዘብ የሚቀበሉበትን ትውውቅ እና ማሕበራዊ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ አሰራር "ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ስታደርግ ታጣቸዋለህ" ይላሉ።

"በደንብ የተደራጁ ነጋዴዎች ከመጡበት አካባቢ ሊሆን ይችላል፤ በጓደኝነታቸው፣ በዝምድናቸው አዳዲስ ለሚመጡ እንደ አሰልጣኝ ሆነው ያገለግላሉ። ገንዘቡን መስጠት ብቻ አይደለም። የተለያየ አቅጣጫ ያስቀምጡላቸዋል፤ ይደግፏቸዋል፤ መንገድ ያሳዩዋቸዋል። ይኸንን ነገር ወደ ዲጂታል ስታመጣው ማሳካት ትችላለህ ወይ?" ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር ብስራት እቁብ በሚጣልባቸው ቦታዎች አባላቱ "ተሰብስበው ከሚጨዋወቱት ማሕበራዊ ጉዳይ ባለፈ" የሚፈጥሩት ግብይት ቸል መባል እንደማይኖርበት ተናግረዋል።

በማሕበራዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረተውን እና የእቁብ ዋንኛ መገለጫ የሆነውን መተማመን በምን ትተኩታላችሁ ተብለው የተጠየቁት የእቁብ መሥራቾች ለጊዜው በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ብቻ ተወስኖ እንዲቆይ መወሰናቸውን አስረድተዋል። የኩባንያው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ዮሐና ኤርሚያስ እንደሚሉት በሒደት አሰራሩን በማጠናከር የማይተዋወቁ ሰዎች ጭምር በጋራ እቁብ የሚጥሉበት ሥርዓት ተቋማቸው ያበጃል። አቶ አሌክሳንደር በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት ሊፈጠር የሚችል የሥራ መስተጓጎልን ለማስቀረት አማራጭ መፍትሔዎች ማዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ