1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስር በከሚሴ፣ሆነ ተብሎ ፈረሰ የተባለው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከ/ም/ቤት አጥር ጉዳይ

ዓርብ፣ ጥር 13 2014

የከሚሴ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ሰዎች ያለምክንያት እየታሰሩ እንደሆነ ተናገሩ፣የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በበኩሉ ያለምክንያት የሚታሰር ሰው የለም ብሏል፣ በባሕር ዳር ከተማ በጥምቀት ዋዜማ ሆነ ተብሎ ፈረሰ የተባለው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አጥር ጉዳይ ተጋኗል ሲል የከተማው ፖሊስ አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/45tgi
Äthiopien Stadt Sanbatee
ምስል Eshete Bekele/DW

እስር በከሚሴ፣ሆነ ተብሎ ፈረሰ የተባለው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከ/ም/ቤት አጥር ጉዳይ

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ያለምክንያት እየታሰሩ እንደሆነ የከሚሴ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ብሔረሰብ አስተዳደሩ በበኩሉ ያለምክንያት የሚታሰር ሰው የለም ብሏል፣ በሌላ በኩል በባሕር ዳር ከተማ በጥምቀት ዋዜማ ፈረሰ የተባለው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አጥር በአንዳንድ አካላት ከሚገባው በላይ በተጋነነ መልኩ እየተራገበ ነው ሲል የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰዎች ያለምክንያት እየታሰሩ ነው ሲሉ የከሚሴ ከተማና አካባቢው አንዳንድ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ለደህንነታቸው ስማቸው እንዳይገለፅና ድምፃቸውም እንዳይቀረፅ ያስጠነቀቁት አስተያየት ሰጪዎች ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ሰዎች በፖሊስ እየተያዙ እየታሰሩ ነው ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዲ እንደሪስ ያለምክንያት የታሰረ ሰው የለም፣ በቅርቡ ከነበረው የህወሓት ወረራ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ግን አረጋግጠዋል፡፡
የማጣራት ሥራው የተለየ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረ አይደለም ያሉት አቶ አብዲ እስሩ “የሐይማኖት አባቶችን ያነጣጠረ ነው” የሚለውን ስምታ አይቀበሉም። ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆኑት አቶ አብዲ ህብረተሰቡ ከአሉባልታ ወሬ ይቆጠብ ሲሉም መክረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በባሕር ዳር ከተማ የጥምቀት ዋዜማ ሰዎች ሆን ብለው የአማራ ክልልን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አጥር አፍርሰዋል ሲሉ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፀሐፊ ሐጂ ኡስማን ኡመር በግል የፌስ ቡክ ገፃቸው ፅፈዋል፡፡ ግለሰቡን ስለጉዳዩ እንዲያብራሩልኝ በስልክ ጠዬቄያቸው ነበር፣ ሆኖም በስልክ መረጃውን እንደማይሰጡኝ አስረድተውኛል፣ በአካል ለመሄድ ብፈልግም ለዛሬ እንደማይመቻቸው ነው የነገሩኝ፡፡
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር ዋጋው ታረቀኝ ድርጊቱን የተፈጠረው በከተራ ወቅት ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ በጽ/ቤቱ በኩል ሲያልፍ ከነበረው መጨናነቅ አኳያ በስሚንቶ ያልተያዙ ብሎኬቶች ወድቀዋል፣ ያ ደግሞ ሆን ተብሎ የተፈፀመ እንዳልሆነ ፖሊስ አረጋግጧል ብለዋል፡፡
በሲሚንቶ ያልተያያዙ ብሎኬቶች አሁንም ስላሉ በቀላሉ የመውደቅ እድል እንደላቸው አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ባለመሆኑ አንዳንድ አካላት ድርጊቱን ከሚገባው በላይ ከማጋነንና ከማራገብ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።ህብረተሰቡ ክፍተቱን ለሚፈልጉ አካላት መሳሪያ አንዳሆንም ኮማንደሩ አስጠንቅቀዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕረዚደንት ሐጂ ሰኢድ መሐመደን በተደጋጋሚ በስልክ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ስልካቸው ስለማይነሳ ሊሳካልኝ አልቻለም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሰ