1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እስላም የጀርመን አካል ነዉ» አንጌላ ሜርክል

ሐሙስ፣ መጋቢት 20 2010

በአዲስ በተዋቀረዉ የጀርመን ጥምር መንግሥት የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ሆነዉ የተመረጡት ታዋቂ የጀርመን ፖለቲከኛ « እስላም የጀርመን አካል አይደለም»  በሚል በመናገራቸዉ በጀርመን ፖለቲከኞች ብሎም በፓርቲያቸዉ ከፍተና ቁጣን ቀስቅሶአል።  

https://p.dw.com/p/2vDiY
Eifeler Sufi-Zentrum Osmanische Herberge
ምስል DW/M. Odabasi

«በጀርመን ሃገር ከ2000 በላይ መስጂድ አለ»

«እስልምና የጀርመን አንዱ አካል ነዉ። በታሪክ ዉስጥ ጀርመን የክርስትያን፤ የአይሁድ ሃገር ናት ልትባል ትችላለች። ነገር ግን ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን ፍላጎት ከሙስሊም ሃገራት የጉልበት ሰራተኞች መጥተዉ ይህች ሃገር ከአፈር ከረሜላ እንድትሆን አብረዉ ከጀርመናዉያኑ ጋር የገነቡ ሙስሎሞች ናቸዉ» ሲሉ አንድ የዶቼ ቬለ ተከታታይ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

በቅርቡ የተቋቋመዉ አዲሱ የጀርመን ጥምር መንግሥት የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ሆነዉ የተሾሙት ሆርስት ሎሬንዝ ዜሆፈር እስልምና የጀርመን አካል ነዉ መባሉ ሃሰት ነዉ ሲሉ መናገራቸዉ በጀርመን ነዋሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ብዙ ዉዝግብን ቀስቅሶአል። «ጀርመን የተመሰረተችው(የተቀረጸችው)በክርስትና እምነት ነዉ ሲሉ የተናገሩት በጀርመን የክርስትያን ሶሻል ኅብረት (CSU) ፓርቲ ሊቀመንበር እና በጀርመን አዲስ ተሿሚዉ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ዜሆፈር ቢልድ ለተሰኘዉ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እስልምና የጀርመን አካል ባይሆንም በሃገሪቱ ዉስጥ የሚኖሩ ሙስሊሞች የጀርመን አካል ናቸዉ ሲሉ፤ አንዴ ደገፍ ደግሞ ዘለፍ አይነት አስተያየት መስጠታቸዉ፤ ስማቸዉ የአንድ ሰሞን ዉይይት እንዲሆን ከመሻት ባሻገር የሃገራቸዉ ገፅታ  ማጥልሸታቸዉ አልታወቃቸዉም፤ ይህንንም ለማገናዘብ እንብዛም  አቅሙ የላቸዉም ተብለዉ መነጋገርያ ርዕስ ሆነዋል። 

Horst Seehofer - Innenminister - Islam und Deutschland
ምስል picture alliance/dpa/S. Hoppe

ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ በቅርቡ የተዋቀረዉ አዲሱ የጀርመን ካቢኔ የሃገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ የተሾሙት የቀድሞዉ የባየርን ማለትም የባቫርያ ፊደራል ግዛት ፕሬዚዳንት የነበሩት ሆርስት ሎሬንዝ ዜሆፈር በመጀመርያዉ የካቢኔ ስብሰባ እስላም የጀርመን አካል አይደለም፤ ሆኖም ግን እዚህ የሚኖሩ ሙስሊሞች የኛ አካል ናቸዉ ብለዉ በመናገራቸዉ ንግግራቸዉ ከፋፋይ በሚል ቁጣን ቀስቅሶአል። ይህ ንግግራቸዉ በማኅበረሰብ ዉስጥ ትልቅ ጩኸትን አምጥቶአል ያሉት በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ  ሰዉየዉ ይህን የተናገሩት በፖለቲካዉ መድረክ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ስማቸዉ  እንዲነሳ ብቻ ፈልገዉ ነዉ፤ ሲሉ ተናግረዋል። 

«ጩኸትን ያመጣበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የጀርመን ፕሬዚዳንት የነበሩት ክርስትያን ዎልፍ እስላም የጀርመን አካል ነዉ ብለዋል። አሁን ለአራተኛ ጊዜ ጀርመንን እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት መራሒተ መንግስት እስላም የጀርመን አካል ነዉ ብለዋል። ዜሆፈር የፖለቲካ ካርድ ለመሰብሰብ ወይም እንዲህ ብሎአል ለማለት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር የለም። መጀመርያ ዜሆፈር ማን ናቸዉ? የባቫርያ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነዉ የቆዩ ናቸዉ። ባቫርያ ዉስጥ ከ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመስጂድ ጋር ተዋዉለዉ ሕጻናቶችን በጀርመንኛ ቋንቋ ሳይሆን እንደ ሞዴል ተደርጎ ከቱርክ ሃገር በሚላክ ኢማም ሃይማኖት እንዲማሩ እያደረጉ ነዉ። ይህን የፈቀደ የባቫርያ አስተዳዳሪ የነበረዉ ዜሆፈር አሁን ግን በፊደራሉ መንግሥት ተሾመዉ ወደ በርሊን ከመጡ በኋላ እስላም የጀርመን አካል አይደለም ነዉ። ይህ አነጋገራቸዉ የፖለቲካ ተዓማኒነታቸዉን የሚቀልስ ነዉ።       

በጀርመን ሃገር ሃይማኖት መሠረታዊ የሰዉ ልጅ መብት ነዉ ተብሎ በሕገ መንግስቱ ተፅፎአል።  እንደየመናገር የመኖር ነፃነት ሁሉ ይህ እንዴት ይታያል?

«ሃይማኖት በጀርመን ሃገር መሠረታዊ የሰዉ ልጅ መብት ነዉ። ይህ የሰዉ ልጅ መሰረታዊ የሰዉ ልጅ መብትም በመሆኑ ነዉ ዛሬ እንኳ የእስላም በዓል ከስራ ቀርቶ የማክበር ፈቃድ መስጠት ቀርቶ፤ እያንዳንዱ መስርያ ቤት ዉስጥ፤ አራት ጊዜ አምስት ጊዜ ሶላት ስለሚሰገድ እያንዳንዱ መስርያቤት የመስገጃ ክፍል የተለየ እንዲያዘጋጅ ሁሉ ተደርጎአል። ይህ የሆነበት ምክንያት በአንቀጽ 4 የጀርመን ሕገ መንግሥት መሰረት ሃይማኖት የሰዉ ልጅ መሰረታዊ የሰዉ ልጅ መብት በመሆኑ ነዉ።ለዚህም ነዉ በጀርመን ዉስጥ እስላምና ክርስትያን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሃይማኖቶች ፤ ቡዲዝም ይሁዳዉያን የመሳሰሉ ሁሉ ይገኛሉ። ግን ጀርመን ዉስጥ ዛሬ ከክርስትና ሃይማኖት ለጥቆ የሚገኘዉ የእስልምና ሃይማኖት ነዉ። በጀርመን ከ 4 ሚሊዮን በላይ ሙስሊሞች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት እስልምና በተጨባጭ አንዱ የጀርመን አካል ነዉ። በጀርመን ሃገር ነዋሪ የሆኑትና ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን በመርዳታቸዉ የሚታወቁት ወ/ሮ ዘሕራ ዚንትል በበኩላቸዉ የሰዉየዉ ንግግር አረበሸኝም ሲሉ ነዉ ነዉ የገለፁት።

Tag der offenen Moschee Sehitlik Moschee
ምስል DW

«እኔ በበኩሌ ምንም አልረበሸኝም ምክንያቱም ይህ ነገር አዲስ አይደለም። ብዙ ጊዜ ፖለቲከኞች የምርጫ ሰዓት ሲደርስና ከተመረጡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ታዋቂነትን ለማግኘት አንገብጋቢ የሆኑ ርዕሶችን ይዘዉ ማራገባቸዉ ያለ ነገር ነዉ። እንጂ እስልምና ለጀርመን አዲስ አይደለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የሚኖሩበት ነዉ። የዉችዉ ዜጋ ብቻ ሳይሆን እራሱ የጀርመን ተወላጆች ፤ እንዲሁም የዉጭ ዜጋ ሆነዉ እዚህ አገር ተወልዶ ያደጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ሰዉየዉ ሙስሊም የጀርመን አካል አይደለም ይበለዉ እንጂ ጭንቅላታቸዉ የተናገሩትን ነገር የሚቀበለዉ አይመስለኝም። ባለፉት ዓመታት ስደተኞች ወደ ጀርመን ሲገቡ ነዋሪዎች ያደረጉትን አቀባበል ያሳዩት መስተንግዶ እንዴት አድርገዉ እንደተቀበልዋቸዉ ስላየሁኝ በአብዛኛዉ ፖለቲከናዉ የታነገሩትን እስከወድያናዉ አይቀበሉትም። አብዛኞቹ ጀርመናዉያን ተቀራርበን ተዋህደን አንድነትን ፈጥረን እንድንኖር የሚፈልጉ ናቸዉ።»   

ወ/ሮ ዘሕራ በጀርመን ሃገር የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸዉን በፈለጉበት መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ? « አዎ ይህ ፍቅር ማለት ነዉ። አንዱ ክርስትናን ያፈቅራል። አንዱ ክርስትያን አንዱ ሙስሊም አንዱ ሂንዱ ነዉ አንዱ ቡዳ ነዉ። ይህ ሰዉ ሆኖ ሃይማኖቱ ግን ዉስጣዊ ፍቅር ነዉ። እኔ ሃይማኖቴን ብኖር ማንንም የምረብሸዉ የለም፤ ማንንም የምነካዉ የለም። ጎረቤቴ ክርስትያን ናት፤ሌላዋ ሌላ ሃይማኖት ይኖራታል ፤ ሁላችንም ግን በሰዉነታችን እንሰራለን እንከባበራለን እንፋቀራለን። ሃይማኖታችን ግን የግል ነዉ። ለዚህም ነዉ በሕገ መንግስቱ ማንኛዉም ሰዉ የራሱን ሃይማኖት የመኖር መብት እንዳለዉ የተገለፀዉ። መቼም ዱንያ ላይ ሁሉም ሰዉ ይወደኛል ብሎ ማለት አይቻልም፤ የሚወድም አለ የሚጠላም አለ። ስለዚህ እያንዳንዱ የራሱን ሃይማኖት እየኖረ እና እየተገበረ ተከባብሮ  መኖር የሚችልበት ሃገር ነዉ።»      

እስልምና በጀርመን ከ 16 83 ዓ,ም ጀምሮ ያለ ነዉ ያሉን በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የሙስሊም ማኅበራት ተጠሪ አቶ ብርሃን አባስ የፖለቲከኛዉ ንግግር ተቀባይነት እንደሌለዉ ተናግረዋል።

Duisburg Moschee DITIB
ምስል Imago/Reichwein

«እስልምናን በጀርመን ዉስጥ ከ 1683 ዓ,ም እስልምና መግባቱ ይታወቃል።የመጀመርያዉ መስጂድ በጎርጎረሳዉያኑ 1732 የመጀመርያዉ መስጂድ በርሊን አጠገብ በሚገኘዉ የፖስትዳም ከተማ ዉስጥ ነዉ የተገነባዉ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ሙስሊሞች በጀርመን ሃገር ይኖራሉ። በአሁኑ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ጀርመን ዉስጥ ይኖራሉ። በጀርመን ሃገር ከ 2000 በላይ መስጂዶች ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ነገር እያለ እስልምና የጀርመን አካል አይደለም ማለቱ ይህ ሰዉ ፤ በመጀመርያ ደረጃ ድጋፍ ፍለጋ ይሆናል። አልያም ደግሞ አካል ነዉ ለማለት መቀበል አልፈለገም ወይም እዉቀት ብዙ የለዉም። ይህን ነገር በማለቱ ብቻ ከሙስሊሙ ወገን ብቻ ሳይሆን ከራሱ የፓርቲ አባል በኩል ከፍተና ተቃዉሞ ገጥሞታል። ዜሆፈር ይህን አወዛጋቢ ጉዳይ ካነሳ በኋላ የጀርመን ነዋሪዎች በአብዛኛዉ እስልምና የጀርመን አካል ነዉ ሲሉ መልስ ስለሰጡት አስደስቶኛል።»

ጀርመን ለሙስሊሞች የምትመች ሃገር ናት? ለሚለዉ ጥያቄ በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የሙስሊም ማኅበራት ተጠሪ አቶ ብርሃን አባስ እንደሚሉት እኔ በኖርኩበት ዓመታት ለእስልምና ጥሩ አቀባበል ኖሮ እስልምናን ተግባራዊ የምናደርግበት ሃገር ነዉ።»   

ዲቲብ የተሰኘዉና በኮለኝ ከተማ የሚገኘዉ መስጂድ በጀርመን ሃገር ትልቁ መስጂድ ነዉ ያሉን ስማቸዉ ባይጠቀስ የመረጡት በጀርመን ነዋሪዉ ኢትዮጵያዊ በበኩላቸዉ በኮለኝ ከተማ እና አካባቢዋ ላይ ብቻ ከ 50 በላይ መስጂዶች እንዳሉ ተናግረዋል።  ጀርመናዊዉ ፖለቲከኛ ያሰሙት ንግግር ግን እንዳሳዘናቸዉ ነዉ የገለፁት።

እኔ በእዉነቱ ለመናገር ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሙስሊም ባለበት ሃገር ወይም የስድስት ሚሊዮኖች እምነት በሆነበት በዚህ አገር እስልምና አካል አይደለም መባልን ስሰማ በጣም አዝኛለሁ። ምክንያቱም እኛን ከቁጥር ዉስጥ ያላስገባ እንደማለት ይመስለኛል። እስካሁን ድረስ የገጠመን ነገር የለም። በማኅበርም እንደራጃለን በመስጊዳችንም እንሰግዳለን፤ ማንም ሰዉ የፈለገዉን ሃይማኖት ሊያራምድበት የሚችል ሃገር ነዉ። የእምነት ነፃነት ያለበት ሃገር ነዉ። እስላምን ከጀርመን ክፍል ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነዉ። እስልምና ነገም ሆነ ዛሬ የጀርመን ብሎም የአዉሮጳ አካል መሆኑ አይቀርም።

Deutschland Angela Merkel macht Selfie auf Fest in Stralsund
ምስል Getty Images/S. Gallup

ትክክለኛ ላልሆነ ነገር በአፀፋዉ መመለስ ያለብን ትክክለኛ አለመሆኑን ማሳየት አለብን እንጂ ነገሩን ይዘን ይባስ ማጉላት የለብንም ሲሉ የሚያስጠነቅቁት በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበራት ተጠሪ አቶ ብርኃን አባስ የትዕግሥት ፍሪ ጣፋጭ መሆንዋን በምሳሌ አስረድተዋል።  

« ጀርመን ከሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በኋላ ስደተኞችን ከቱርክ ሃገር ከእስላም ሃገር አምጥተዉ ጀርመን በሁለተናዉ ዓለም ጦርነት የወደቀችዉን አፈር ገንብተዉ ለዛሬ ኤኮኖሚ ማንሰራራት መሰረት የጣሉት እነዚህ ሙስሊሞች አንዱ የኅብረተሰቡ አካል ናቸዉ። እነዚህ ማኅበረሰቦች ከሦስት ትዉልድ በላይ አፍርቶአል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጀርመን የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ሕግ አክባሪ ናት፤ በዚህም መሰረት ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት ወደ ጀርመን መጥተዉ የስደተኝነት መብትን አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም በስራ ተጋብዘዉ የመጡት ቤተሰቦቻቸዉን አምጥተዋል። ከሁሉ በላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ከሶርያ በጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ስደተኞችን እጃቸዉን ዘርግተዉ ተቀብለዋል። በዚህም ምክንያት መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ፖለቲከኛዉ ፍሪን እንዲይዙ ማድረግ አለባቸዉ። ሙሉ መሰናዶዉን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን በመቻን ይከታተሉ።

DITIB Zentralmoschee Köln-Ehrenfeld
ምስል DW/M. Odabasi

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ