1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እላፊ» ፈታኙ የኢትዮጵያዉያን የስደት ጉዞ በጥናት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 14 2013

«ታዬ የዚያን ዕለት ማታ መጥቶ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጉዞ አስጠንቅቆን ሄደ። በተባለው ሰዓት ከብቶችን የጫነ ትልቅ መኪና መጣ። በስድስታች ላይ ሌሎች ስድስት ስደተኞችን ጨምረው፣ ቦታ በባትሪ እየፈለጉ ከብቶቹ መሃል ሰገሰጉን። የፀሐይዋ ስትግል፣ ከብቶቹ ሽታ ስለጨመረ መተፋፈግና ሽታ በረታ። እየረፈደ ሲሄድ በጣም ንዳድ ሆነ። የስደት አሳዛኝ እዉነታ»

https://p.dw.com/p/3sRHd
Äthiopien Buchpremiere Yordanos Almaz Seifu
ምስል privat

መጽሐፉ የስደተኞችን ፖሊሲ ለመቅረጽ እጅግ ጥሩ ግበዓት ይሆናል

«ይሄን መጽሐፍ ሳነብ ፖለቲከኞች እደሎኝ ናቸዉ አልኩ። በተለይ በሃገራችን ምርጫ ተቃርቦአል። የትኛዉ የፖለቲካ ፓርቲ ነዉ ለመሆኑ የስደተኛ ፖሊስን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ያለዉ? ዜጋ በየቦታዉ ሲወድቅ ሲረግፍ፤ ዜጋዉ ሕይወቱ እንዳልሆነ ሲሆንበት፤የሚጠብቀዉ የሚንከባከበዉ አለ ወይ? ለፖለቲከኞች እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሃሳብ፤ የተጠናቀቀ የቤት ሥራ ነዉ፤ ምንድን ነዉ መደረግ ያለበት ብሎ መጠየቅ ማለት በሽታዉን ከነመድሐኒቱ ማስቀመጥ ማለት ነዉ»

 በቀርቡ ለአንባብያን ያበቃዉ እና 510 ገፆችን የያዘዉ በአቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ የቀረበዉ ስለስደተኞች እንግልት የሚያተኩረዉ  «እላፊ» የተሰኘዉ መጽሐፍ ሲገመገም በመድረክ ላይ አንድ ሃያሲ የተናገሩት ነዉ። በቅርቡ በአቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ገበያ ላይ የዋለዉ «እላፊ» የተሰኘዉ የመጽሐፍ ይዘት የኢትዮጵያዉያን ወደ ደቡብ አፍሪቃ የስደት ጉዞን፤ ኑሮን፤ ፍዳ እና አበሳን የሚተርክ ሲሆን በመጽሐፉ ግምገማ ላይ ከተነሱ ሃሳቦች መካከል እንደዚህ ከላይ እንደተጠቀሰዉ፤ እዉነት የምርጫ ዝግጅት እያደረገች ባለችዉ ኢትዮጵያ፤ ፖለቲከኞቻችን የስደተኞች ጉዳይ ፖሊሲን ቀርፀዋልን? የሚያሰኝ ሃሳን ቀስቅሶአል። አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ስደተኞች በተጓዘበት እና በሚኖሩበት ሃገራት በመሄድ ኑሮአቸዉን ችግራቸዉን የስደት ጉዞዋቸዉን በማየት እና በመጠየቅ ለዓመታት ያደረገዉን ጥናት ሰንዶ ለአንባብያን እንዲህ ሲያቀርብ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። አቶ ዮርዳኖስ አሁን ይፋ ባደረገዉ «እላፊ መንገደኛ ቁጥር ሁለት» በተሰኘዉ መጽሐፉ «መጓዝ ነጻ ያወጣል» ሲል ይጠቅሳል ምን ማለቱ ይሆን  ይሆን?

Äthiopien Buchpremiere Yordanos Almaz Seifu
ምስል privat

ደራሲ ዮርዳኖስ «መጓዝ ነጻ ያወጣል ስል ከስደተኞች አንፃር አይደለም። መጓዝ ስል አንድ ሰዉ ከአንድ ቦታ ፤ ከአንድ ባህል፤ ከአንድ የፖለቲካ ማኅበራዊ እና የኤኮኖሚ ማዕቀፍ ወደ ሌላ ሲጓዝ የእስዋን ወይም የእሱን ነባራዊ ሁኔታ የሚያይበት መነፀር አድማሱ ይሰፋል ለማለት ነዉ። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲሄድ በንባብ እና በሚዲያ የሰማቸዉ ነገሮች እና መሪት ላይ ያለዉ ሃቅ ብዙ ጊዜ አንድ አይሆንም። ስለዚህ ኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ባህሉን ብሎም ፕሮፖጋንዳዉን በመጓዝ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የተሻለ ግንዛቤ እና የተሻለ አረዳድ ይኖረዋል፤ ይኖራታል ለማለት ነዉ። መጓዝ ሰፊ አድማስ እንዲኖረን የተሻለ አመለካከት እንዲኖረን ያደርጋል። መጓዝ ቀስ በቀስ ካለንበት ጠባብነት፤ ካለብን ዘረኝነት እና ብሔርተኝነት እየፈታ ነፃ ያወጣናል ለማለት ነዉ። ሌላዉ መጓዝ፤ የሃሳብ መጓዝ ነዉ። ለምሳሌ አንድን ሞያ መማር ጥሩ ነዉ ይባላል። የምህንድስና ሞያ ፤ የታሪክ ሞያ፤ የሕክምና ሞያ ፤ ግን ደሞ የሃሳብ አድማሳችንን በዚህ ሞያ ላይ ብቻ የምናደርግ ከሆነ፤ በዛ ሃሳብ እና በዚያ መነጽር ብቻ ይለጉመናል።  ስለዚህም ከአንደኛዉ የሞያ አድማስ ወደሌላዉ የሞያ አድማስ በሃሳብ መጓዝ ብንችል በባህል በኤኮኖሚ በተለያዩ የሞያ ዘርፎች ተለጉሞ የነበረበትን ማዕቀፍ ጥሶ ለመዉጣት እና የተሻለ ሰዉ ለመሆን እድል ይፈጥራል። ስለዚህ መጓዝ በእግር ብቻ ሳይሆን በማንበብም በምናብም ነዉ። »

እላፊ መንገደኛ ቁጥር ሁለት የተባለዉ በተለይ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰደዱ ኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ የሚተርከዉ ሁለተኛ ክፍል መጽሐፍ ዉስጥ ከተነሱት ጉልህ ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያዉያኑ ጉዞ ለመጀመር ከሃገር ቤት ገንዘብን እንዴት እንዴት እንደሚያገኙ እንዴት እንደሚበደሩ በኋላም የብድር አከፋፈል ዘዴያቸዉን ሁሉ ያስቃኛል።

አቶ ዮርዳኖስ የተለያዩ ነጥቦችን እላፊ በተባለዉ ጥናታዊ መድብላቸዉ ጠቅሰዉታል። «“... ታዬ የዚያን ዕለት ማታ መጥቶ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጉዞ አስጠንቅቆን ሄደ። በተባለው ሰዓት ከብቶችን የጫነ ትልቅ FSR መኪና መጣ። በስድስታች ላይ ሌሎች ስድስት ስደተኞችን ጨምረው፣ ቦታ በባትሪ እየፈለጉ ከብቶቹ መሃል ሰገሰጉን። ታዬ መካሻ ከሚባል ኬኒያ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ደላላ ጋር በስልክ አገናኝቶን እዚያው ቀረ። የፀሐይዋ ሙቀት ሲያይል፣ ከብቶቹ ሽታ ስለጨመረ መተፋፈግና ሽታ በረታ።

እየረፈደ ሲሄድ በጣም ንዳድ ሆነ። ሞያሌ ላይ ከተቀላቀሉን ልጆች አንደኛው ከኋላ ኪሱ ምላጭ አውጥቶ የሸፈነንን ሸራ ቀደደው። ትንሽ ተነፈስን። ልጁ ቀዳዳውን እያሰፋው ሄዶ “መስኮት” ቢጤ ሰራ። የተሸለ አየር ለማግኘት ከብቶቹን ተፋትጎ ወደ ላይ ወጣ። ከመኪናው አናት ላይ ተቀምጦ እያወራን የግራር ዛፍ ቅርንጫፍ ገጭቶ ከመኪናው ላይ ጣለው። መኪናው እንዲያቆም ብንጮህም፣ ሹፌሩ ዝም ብሎን ነዳ። የተሳቢውን ወለል በእግራችን እየደቃን ስንጮህ መኪናውን አቆመ።  ለሊት ዘጠኝ ሰዓት የተነሳ መኪና ቀኑን ሙሉ ሲጓዝ ውሎ እኩለ ለሊት ላይ ቆመ።  መካሻ በስሩ የሚሰራ ኤድዋርድ የሚባል  አሻጋሪ እንደሚጠብቀን ነግሮን ነበር።  [አድዋርድ] ከሌሎች ስደተኞች ጋር ቀላቀለና በስሩ ለሚሰሩ ጀሌዎች አከፋፈለን። ኤሪክ የሚባል አሻጋሪ ወደ አንድ ያረጀ ሕንጻ ወስዶ ፎቅ ውስጥ አስገባና ጠባቂ መደበልን።

ስድስት ቀን ከክፍላችን ሳንወጣ ቆየን። በሰባተኛው ቀን ኤድዋርድ መጣ። ከሌሎች ስደተኞች ጋር ተቀላቀልንና እንደ ኩንታል ተደራርበን የጭነት መኪና ላይ ተጭነን መንገድ ጀመርን። ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ ስንደርስ ከመኪናው ወርደን ረጅም መንገድ በእግር ተጉዘን መጋዘን የሚመስል ቤት ጋር ደረስን። ቤቱ ውስጥ በጣም መጥፎ ጠረን የነበራቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ታጉረዋል። እንዳዶቹ አጋንንት እንደያዘው ሰው ያስፈራሉ። የኤድዋርድ ምንዝሮች እየገፈተሩ ሲያስገቡን ከስደተኞቹ ሸሽተን ጥግ ያዝን። በዚህ ግዜ “ተስፋ ተስፋ ” የሚል ድምፅ ሰማሁ። የጠሩኝ ልጆች ክቡርና ደስታ የሚባሉ የአከባቢያችን ልጆች መሆናቸውን የለየሁት፣ ማንነታቸውን ሲነግሩኝ ነበር። ብዙዎቹ ልጆች በመንገድ እንግልት፣ በውሃ ጥምና በረሃብ ብዛት ተቀያረው ስማቸው ብቻ ነው የቀረው። የእኛም መጨረሻ እንደነርሱ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ጭንቀት ወረረን። የዚያኑ ዕለት ማታ መቶ የምንጠጋ ስደተኞች በደላሎቻችን ተከፋፈልንና ወደ ሞምባሳ መንገድ እንደምንጀምር ተነገረን። ገንዘብ የሌላቸውና ደላላ መያዝ ያልቻሉ እዛው ቀርተው ወደ ናይሮቢ መንገድ ጀመርን። ወደ ናይሮቢ የወሰደን የጭነት መኪና በዝይት ጄሪካኖች የተሞላ ነበር። ሃያ የምንጠጋ ስደተኞችን በጄሪካኖቹ መካከል ጠቀጠቁን። ናይሮቢ ለመግባት ስንቃረብ ፖሊሶች መኪናውን አስቁመው፣ ባትሪ እያበሩ ከያለንበት ፈልፍለው አወጡና አሰሩን።ከሁለት ቀን በኋላ አሻጋሪያችን በፖሊሶቸ አካውንት ገንዘብ አስገብቶ አስፈታን። ናይሮቢ ገብተን ወደ ተዘጋጀልን ሎጅ ስንገባ፣ መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አገኘን። ብዙዎቹ የሆሳዕናና የዱራሜ አከባቢ ልጆች ሲሆኑ ሙቀቱን ለመቋቋም ከፓንት በቀር ምንም አለበሱም። የማየው ነገር ሁሉ እንደ ሕልም ሆነብኝ። እዚያ ከገባሁ እስከ መጨረሻው የምወጣ አልመስልህ አለኝ። ለማምለጥ ስሞክር፣ አሻጋሪውና ጭፍሮቹ ይዘው አስገቡኝ። እንደ ሐገሬ ልጆች ልብሴን አውልቄ በፓንት ቀረሁ። እዚያ ከነበሩት ውስጥ ዓመት ሆነኝ፣ ሰባት ወር ሆነን፣ ስምንት ወር ሆነኝ የሚሉ ብዙ ናቸው።» ልብ አንጠልጣይ ፤ አሰቃቂ እዉነታ!

Äthiopien Buchpremiere Yordanos Almaz Seifu
ምስል privat

ደራሲ ዮርዳኖስ አልማዝ ስደተኞችን በተመለከተ በምርምር እና ጥናት ላይ ተመርኩዞ የተለያዩ መጣጥፎቹን በመፅሐፍ መልክ ጠርዞ ሲያቀርብ ተነባቢነቱን ለማላቅ በብሂሎች፥ በሕዝብ ተረት እና ምሳሌያዊ አነጋገር እንዲሁም በግጥሞች መዋዛቱን  የመጽሐፉ ገምጋሚዎች አድንቀዋል። ለምሳሌ ያህል «ከሰዉ ሃገር መሄድ ያደርጋል ደንቆሮ፣ ዉሻዉን ዘልዬ ነከሰችኝ ዶሮ» የሚለዉ ተጠቃሽ ነዉ።  በተለይ ደራሲዉን ካስቆጩት ነገሮች መካከል በስደት ጉዞም ሆነ በሚኖሩበት ሃገር የኢትዮጵያዉያን ሞት ጉዳይ በቁጥር ብቻ ተነግሮ መታለፉ መሆኑን አሳይቶዋል። ሌላዉ ዉጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ለዘመዶቻቸዉ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብና ግድየለሽ አጠቃቀሙ ነዉ ።

ደራሲ ዮርዳኖስ «ስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በችግር እንቅልፍ አጥተዉ ከበረዶ ታግለዉ ወደ ዘመዶቻቸዉ ወደ ሃገርቤት የላኩትን ብር ኢትዮጵያ ላይ ዉስኪ በበረዶ ሲጠጡበት ማየቱ፤ በደም ገንዘብ ላይ መጫወት እንደማለት ነዉ። » በመጽሐፉ ላይ አንዲት ወጣት አንድ ልብወለድ መጽሐፍን አንብባ በደቡብ አፍሪቃ ያለዉን ዉብ ኑሮ በምናብዋ ስላ ስለመሰደድዋም መጽሐፉ ይተርካል። እላፊን ያነበበ አንድ ሐያሲ፤ መጽሐፉ የስደተኞችን ፖሊሲ ለመቅረጽ እጅግ ጥሩ ግበዓት መሆኑን በመግለፅ ፖለቲከኞቻችን ስለስደተኞች ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፀዋልን ሲል ይጠይቃል።  መጽሐፉን ያነበበ ይጠቀማል ሲሉ ሐያሲያኑ ይናገራሉ!  ሙሉዉን ዝግጅት ለማዳመጥ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።  

አዜብ ታደሰ


እሸቴ በቀለ