1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢፕሊፕሲን በመድኃኒት መቆጣጠር ይቻላል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2011

በዘልማድ የሚጥል በሽታ የሚባለው ኢፕሊፕሲ የተሰኘውን ከነርቭ ሥርዓት ጋር የተገናኘ ህመም ብዙዎች እንደልክፍት እየተመለከቱት ወደ ህክምናው እንደማይሄዱ ይነገራል። የህክምና ባለሙያዎች ግን ይህን የጤና ችግር መንስኤውን በመመርመር በህክምና ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይቻላል ይላሉ። ህክምናው እንዴት ያለ ይሆን? የእኛ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ ነው።

https://p.dw.com/p/3N1OS
3D Darstellung von Gehirnzellen - Nervenzellen
ምስል Imago/imagebroker/O. Maksymenko

«ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ሆስፒታሎች ህክምናው ይሰጣል»

ከሳምንት በፊት ለኢፕሊፕሲ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶችን የዘረዘሩት ዶክተር ተሻገር ደመቀ፤ ችግሩ ከሥርዓተ ነርቭ እና ከአንጎል ጋር እንደሚገናኝ፤ ተፅዕኖው ደግሞ ለመላ አካል እንደሚተርፍ አስረድተው ነበር።  የጤና ችግሩ ከእርኩስ መንፈስ ጋር እንደማይገናኝ አፅንኦት በመስጠትም በህክምና መቆጣጠር ይቻላል ነበር ያሉት።  ከዚህ በሽታ ሊገላግል የሚችል ብቸኛ የህክምና ዘዴ አለ ይሆን? ያልናቸው በጀርመን ባድ ሽታፍል ሽታይን ከተማ በሚገኘው ሽን ክሊኒክ የነርቭ ማዕከል ከፍተኛ የነርቭ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ተሻገር ደመቀ፤ እንዲህ ይላሉ።

«እንደዛ እንኳን ሊባል አይቻልም፤ ለምን? በሚጥል በሽታ ውስጥ የተለያዩ (ሲምፕተሞች )ምልክቶች አሉ። አንዳንዱ የሆነውን የሰውነታችንን ክፍል ወይም ደግሞ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍሎች ሊያጠቃልል ይችላል። እነዚህ እነዚህ ነገሮች በህክምናው ላይ መታየት አለባቸው። ሌላው ደግሞ መንስኤው ምንድነው? ለምሳሌ በአንጎል ውስጥ አንድ ዕጢ ካደገ ያንን በኦፕሬሽን ማውጣት አስፈላጊ ነው። ወይም ደግሞ አንጎላችን ውስጥ ደም ሊኖር ይችላል ያንን ደም ማስወገድ አስፈላጊ ነው። እና በምክንያቱ የተነሳ ነው እንግዲህ የሚያስፈልገው ምርመራም ህክምናም የሚደረገው።»

እንዲያም ሆኖ ግን ምርመራውን ተከትሎ በአብዛኛው በመድኃኒት ሊቆጣጠሩት የሚችል የጤና ችግር መሆኑን ነው የነርቭ ከፍተኛ ሃኪሙ የነገሩን። ይህን የሀኪሙን ምክር የሚያረጋግጥ እንግዳም አለን ለዛሬ። ኢዛና ሀዲስ ወልደ ገብርኤል ይባላል። በቅርቡ ነው ከማንቼስተር ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪውን ሠርቶ በከተማ ልማት እና የአካባቢ አስተዳደር የተመረቀ። ከተጠቀሰው የጤና ችግር ጋር በተገናኘ የግል የሕይወት ተሞክሮውን ሌሎችም እንዲጠቀሙበት በማሰብ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማካፈሉን ተመልክቼ ስለነበር ፈቃደኝነቱን ስጠይቀው በደስታ ነው የተቀበለኝ። ዶክተር ኢዛና ልለው ነበር፤ እሱ ግን የለም እኔ እንዲህ መጠራትን አልፈልግም በሃሳቤ እና በሥራዬ ብቻ ነው ሰዎች እንዲያውቁኝ የምፈልገው አለኝ። አክብሮቴን ገልጬ የጤና ችግሩ ምንነት በውል ባለመታወቁ ብዙዎች ተገቢውን ህክምና ባለማግኘታቸው ከጓዳ ውለዋል እና እስኪ ያንተን የስኬት ምንጭ ግለፅልን አልኩት።

«የእኔን ሥራ ነው እየሠራሽልኝ ያለሽው እና ደስታው የእኔ ነው፤ ምንድነው መሰለሽ ኢፕሊፕሲ በብዛት እኛ ሀገር የሚስተዋለው የሚጥለው ዓይነት ነው። እኔ ፐርሰናሊ ያጋጠመኝ መፍዘዝ የሚባለው ነው። ሳትወድቂ ለጥቂት ሰከንዶች ቀልብሽን ትስቻለሽ።»

Bayer AG Logo
ምስል picture-alliance/Geisler/C. Hardt

ኢዛና የጤና ችግሩን ለመግለጽ የሞከረበት መንገድም ከነርቭ  ከፍተኛ ሃኪሙ  መግለጫ  ጋር ይቀራረባል። ኢዛና በልጅነቱ ነው ይህ የጤና ችግር ያጋጠመው።  በልጅነቱ የገጠመው የጤና ችግር የትምህርት ጉዞውን ፈፅሞ ባያደናቅፍበትም የማይረሳው ሕይወት ተሞክሮ ግን አትርፎለታል።

ኢዛና በወቅቱ የጤና ችግሩ ወዲያው ቢታወቅለትም መድኃኒት ለመውሰድ ግን አልቻለም ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቀው የሚጥለው አይነት ብቻ በመሆኑ ለሚያፈዘው ገና መድኃኒቱ አልገባም ነበር። ኢዛና እንደሚለው በሽታው ውሎ አድሮ መጣል ሲጀምረው ደግሞ እሱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡንም የሚነካ ሌላ ነገር ተከተለ፤

« እናቴም አስቸጋሪ ጊዜ ነበራት ምክንያቱም ሰው እንደሕክምና ችግር ስለማያየው አንዳንድ ቦታዎች እንድትወስደኝ እምነቷም የማይፈቅደው ነገር ላይ ጠንቋይ ቤት ሊሆን ይችላል ሌላ ሌላ ቦታ ሊሆን ይችላል። ባጠቃላይ እነሱ ለእኔ ያላቸው አመለካከት በሰይጣን በልክፍት መለከፉ ምናምን ነገር ይሰማት ነበር። ያኔ ነው ብዙም ሰው ማግኘት ሁሉ የሚያስጠላኝ ደረጃ የደረሰው።»

መድኃኒቱን የሚወስድ ሰው አልክሆል መጠጥ መጠጣት እንደማይፈቀድ፤ ካፌይን ወይም የሚያነቃቁ የሚባሉ ቅመሞች ያሉበት ሌሎች መጠጦችም ሆኑ እፆችን መጠቀምም እንደማይመከር ነው የሚናገረው ኢዛና። እሱም ከእነዚህ ነገሮች ራሱን ቆጥቦ መኖሩን ገልጾልናል። መድኃኒቱን በጥንቃቄ በመውሰዱም አሁን የጤና ችግሩን መቶ በመቶ ለመቆጣጠር መቻሉንም አጫውቶናል።  

Wellcome Image Awards Brain-on-a-chip
ምስል Collin Edington and Iris Lee/Koch Institute at MIT

ተገቢውን ህክምና በመከታተል በትምህርቱ ገፍቶ ዛሬ ሦስተኛ ዲግሪውን መቀበል የቻለው ኢዛና ሰዎች በዚህ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው እና እቅዳቸው ሊስተጓጎል አይገባም ባይ ነው።

ህክምናውን ለመከታተል በቤተሰቦቹ ድጋፍ እና በራሱም ጥንካሬ ለዚህ የበቃው ኢዛና ሀዲስ ወልደገብርኤል፤ የእሱ ስኬት ብቻ የሚያረካው አይነት ሰው አይደለም። ሌሎች የዚህ የጤና ችግር ተጠቂዎችም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በቂ መረጃ አግኝተው ወደ ህክምናው እንዲሄዱ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አጫውቶኛል። እሱ አጥብቆ በጠየቀኝ መሠረት እኔም ወደ ኢትዮጵያ በመደወል ከፍተኛ የስነልቡና ሃኪም የሆኑት ዶክተር መስፍን አርአያን አሁን በሀገር ውስጥ ስላለው የኢፕሊፕሲ የህክምና ይዞታ ጠይቄያለሁ። ዶክተር መስፍን እንደነገሩኝ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሃኪም የኢፐልፕሲ ታማሚዎችን መርዳት ይችላል። ዋናው ነገር የህመሙ መንስኤ ቀድሞ በነርቭ ልዩ ሃኪሞች መጣራት ይኖርበታል። እርግጥ ነው በሀገር ቤት ያለው የመድኃኒት አይነት አራት ግፋ ቢል አምስት አይነት መሆኑን፤ ያም ሆኖ ግን 90 በመቶውን ታማሚ በሚገባ ሕመሙን እንዲቆጣጠር የሚረዳ ህክምና ማግኘት እንደሚቻልም አስረድተውኛል። በክፍለ ሃገራት ሳይቀር የጠቅላላ ህክምና ዶክተሮች ይህን ችግር ለመርዳት ስልጠና መውሰዳቸውንም ዶክተር መስፍን አርአያ አረጋግጠውልኛል። የብዙዎች ችግር የህመሙን ምንነት አለመረዳት በመሆኑ ይህን መረጃ የሰማችሁ ሁሉ ለምታውቋቸው በማስረዳት በህክምናው ተጠቅመው ህመሙን መቆጣጠር ችለው በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። የራሱን ተሞክሮ በማካፈል የተባበረንን ኢዛና ሀዲስ ወልደገብርኤልን፤ እንዲሁም ሙያዊ መረጃዎችን የሰጡንን ተባባሪ የህክምና ባለሙያዎቹን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ