1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተገን ጠያቂዎች ችግሮች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2010

ከቋንቋ ችግር በተጨማሪ ግለሰቦች ለጥያቄአቸው የሚያቀርቧቸው ደጋፊ መረጃዎች አለመሟላት ፣አለመስተካከል እና መዛባት ጉዳያቸውን ሊያጓትት ጥያቄአቸውም ተቀባይነት እንዳያገኝ  ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ሌላ ስደተኞች በጀርመን ያላቸውን መብት ባለማወቅም ወደ ሌላ አገር መስደድን የመሳሰሉ አላስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል። 

https://p.dw.com/p/321e9
Deutschland Ankunft von Flüchtlingen
ምስል picture-alliance/dpa/F. Kästle

ኢትዮጵያውያን ተገን ጠያቂዎች በጀርመን

ጀርመን ተገን የጠየቁ እና የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያለገኘ ኢትዮጵውያን ስደተኞች ለተለያዩ ችግሮች እንደሚዳረጉ ይናገራሉ። የቋንቋ ችግር ፣ የሀገሪቱን የተገን ጠያቂዎች አቀባበል ህግ አለማወቅ የሚረዳቸው እና የሚመክራቸው ማጣት ብቸኝነት መቦዘን እና የመሳሰሉት ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች ህይወት በጀርመን ከባድ እንዲሆን አድርገውባቸዋል። በዚህ የተነሳም በተለይ ጥገኝነት ያልተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን ለተለያዩ ስነ ልቦናዊ ቀውሶች ይዳረጋሉ። ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሌላ አገር የሚሰደዱ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው ያለፈም አሉ። በደቡብ ጀርመንዋ በሙኒክ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለስደተኞች የምክር አገልግሎት የሚሰጠው አብዲ አባጀበል እንደሚለው ጀርመን የተገን ጥያቄ ማመልከቻ ከሚያስገቡ ኢትዮጵያውያን እጅግ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ተቀባይነት የሚያገኙት። እዚህ የኢትዮጵያውያን የተገን ጥያቄ እንደ ኤርትራውያን አለያም እንደ ሶሪያውያን በጥቅል ሳይሆን በተናጠል ነው የሚታየው። በዚህ ሂደትም ከቋንቋ ችግር በተጨማሪ ግለሰቦች ለጥያቄአቸው የሚያቀርቧቸው ደጋፊ መረጃዎች አለመሟላት ፣አለመስተካከል እና መዛባት ጉዳያቸውን ሊያጓትት ጥያቄአቸውም ተቀባይነት እንዳያገኝ  ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ሌላ ስደተኞች በጀርመን ያላቸውን መብት ባለማወቅም ወደ ሌላ አገር መስደድን የመሳሰሉ አላስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል። 

 ለዚህ ፕሮግራም ሲባል ስሙ የተቀየረው እስማኤል ከትውልድ አካባቢው ከባሌ  ተሰዶ ጀርመን ነው የሚገኘው። ከሀገሩ የወጣው በአካባቢው ይደረግበት የነበረውን ክትትል በመሸሽ መሆኑን ይናገራል። እርሱ እንደሚለው መሪታቸውን በኢንቬስትመንት ምክንያት የተነጠቁ የአካባቢው ሰዎች ድርጊቱን ሲቃወሙ ፀረ-ልማት ፀረ-ህገመንግሥት ኦነግ ፣ተብለው በሽብር ወንጀል ተከሰው በታሰሩበት ወቅት ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ይረዳቸው እና ለውጭ መገናኛ ብዙሀንም መረጃዎችን ያስተላልፍ ነበር። አንዳንድ ሰነዶቹ ፖሊስ እጅ ሲገቡ የትውልድ አካባቢውን ለቆ ወጣ ከሀገር ለመሰደድም ወሰነ። ከኢትዮጵያ ሱዳን ከዚያም ሊቢያ በኋላም በሜዴትራንያን ባህር አድርጎ ኢጣልያ ገባ የስደቱ መጨረሻ አሁን የሚገኝባት ጀርመን ናት። እንዲህ በአንድ ዐረፍተ ነገር የተጠቃለለው የስደት ጉዞ አደገኛ ነበር። በጉዞ ወቅት በበረሃ እና በባህር ጉዞ ብዙ መከራ እና ስቃይ ደርሶበታል። ቻድ እና ሊቢያ ድንበር ላይ ፣እርሱ እና መሰሎቹ በደላሎች ተሸጠዋል። ገንዘብ ተጠይቀው ማምጣት ያልቻሉ ሲገደሉ፣ በጉዞ ላይ በሙቀት እና በአየር እጦት እንዲሁም በውሀ ጥም ህጻናት እና አዋቂዎች ሲሞቱ፣ሴቶች ሲደፈሩ አይቷል። እርሱም ተደብድቧል። የባህር ጉዞውም እንዲሁ ቀላል አልነበረም። ግን እንደ እድል ሆኖ ከዚህ ሁሉ መከራ እና ስቃይ ተርፎ በኢጣልያ እና በስዊትዘርላንድ በኩል አድርጎ ጀርመን ገባ ከገባ ሦስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተዋል። ምንም እንኳን ሰዓድ ሀገር ቤት ቢቆይ እንዳይታሰር እና ለሌሎች አደጋዎችም እንዳይጋለጥ  በመስጋት ጀርመን ቢመጣም ያሰበው እና የተመኘው ግን አልተሳካም።
ኢስማኤል የተገን ጥያቄው ተቀባይነት ባለመግኘቱ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉን ተናግሯል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። እርሱ እንደሚለው ይህ ችግር የሚደጋገመው በደቡብ ጀርመን ነው። 
 
እንደ ኢስማኤል ሁሉ በአደገኛ የበረሃ እና የባህር ጉዞ ጀርመን ከገባች ሁለት ዓመት ግድም የሆናት ለዚህ ፕሮግራም ሲባል ስሟ የተቀየረው ቡርቱካንም ተመሳሳይ እጣ ነው የገጠማት። ኢስማኤል ኡጣልያ ሲገባ የአውሮጳ ህብረት ህግ እንደሚጠይቀው አሻራ እንዲሰጥ አልተጠየቀም። መንደሪና እና በአጠቃላይ 95 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያን እና ሶማሊያውያን ስደተኞች ግን ኢጣልያ ተገደው አሻራ ሰጥተዋል። ከኢጣልያ በኦስትሪያ አድርጋ ፍቅረኛዋ የሚገኝበት ጀርመን ብትገባም የተገን ጥያቄዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውድቅ ተደርጎባት ወደ ኢጣልያ ተመለሺ የሚል ደብዳቤ ደርሷታል። አብረዋት የመጡትም በሙሉ በፍርሃት ጀርመንን ጥለው ሲወጡ እርስዋ ግን የባቡር አደጋ ደርሶባት ጀርመን መቆየቷን ገልጻለች። መንደሪን እንደምትለው እርስዋ ባለችበት አካባቢ በርካታ ተስፋ የቆረጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ።
ብርቱካን  በአደጋው ምክንያት ለሁለት ወራት ሆስፒታል ቆይታ ብትወጣም አደጋው ከጤና እክሎች በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችንም አስከትሎባታል። 
እስማኤል እና ብርቱኳን፣አብዲ በምክርም በትርጉምም ከሚረዳቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ናቸው ። ርሱ ለሚሰጣቸው ድጋፍ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። እንደ ርሱ ሊረዷቸው እየቻሉ ምንም እገዛ አላደረጉልንም የሚሏቸውን ኢትዮጵያውያንን ይወቅሳሉ።
ብርቱኳን የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ በሚመለከተው መሥሪያ ቤት በድጋሚ ለቃለመጠይቅ ተጠርታ ውጤቱን እየተጠባበቀች ነው። ከአደጋው በኋላም የአንድ ልጅ እናት ሆናለች። እርስዋም በመጣችበት መንገድ ጀርመን ከርስዋ ቀድሞ የገባው የፍቅረኛዋም የተገን ማመልከቻ ተቀባይነት አላገኘም። ቢያንስ ግን አሁን ከብቸኝነት ተላቃለች። ኢስማኤል ደግሞ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ የተገን መብቱን ለማስከበር እየጣረ ነው። ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ በፖለቲካ ምክንያት የተሰደዱ ኢትዮጵያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም ለርሱ ወደ ሀገር መግቢያው ጊዜው ገና መሆኑን ነው የሚናገረው።

Migration aus Afrika in der Nähe der Stadt Gohneima, Lybien
ምስል picture-alliance/dpa/AP/Küstenwache Lybien
Grenzen in Europa
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ