1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዉያኑ ስደተኞች በጅቡቲ 

ሐሙስ፣ ሐምሌ 26 2010

በጅቡቲ በኩል ወደ የመንና  ሳዉዲ አረቢያ ለመሻገር ጉዞ የሚጠባባቁ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በኮሌራ በሽታ እየሞቱ ነዉ ሲል ፍራንስ 24 የተባለዉ የዜና አዉታር ዘገበ። እንደ ዜና ምንጩ ባለፉት 5 ሳምንታት ብቻ ከ 40 በላይ ስደተኞች በበሽታዉ ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

https://p.dw.com/p/32WC3
Migranten aus Westafrika Symbolbild Menschenhandel
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

Ethiopian migrants risk torture and cholera on way to Yemen - MP3-Stereo


 ጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ችግሩ መከሰቱን ተናግረዉ ፤ ነገር ግን የሟቹቹ ቁጥር ከተጠቀሰዉ አሃዝ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልፀዋል። 
 ፍራንስ 24 የተባለዉ የፈረንሳይ ዜና አዉታር ሰሞኑን እንደዘገበዉ ወደ የመንና ሳዉዲ አረቢያ ለመሻገር በጅቡቲ ጉዞ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች  በበሽታ ፣በረሀብና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ስቅይት ሕይወታቸዉ አደጋ ተጋርጦበታል።  ካለፉት 5 ሳምንታት ወዲህ ደግሞ የበርካታ ስደተኞች መዳረሻ በሆነችዉ «ኦቦክ» በተባለች የጅቡቲ የባህር በር አቅራቢያ ስፍራ፤ በኮሌራ  በሽታ ሳቢያ ኢትዮጵያዉያኑ ስደተኞች ሕይወታቸዉ እየተቀጠፈ መሆኑን ገልጿል።
ላለፉት አራት አመታት በስደት ጅቡቲ እንደሚኖሩ የገለፁልን አቶ ኑርዬ አበበ የተባሉ ኢትዮጵያዊም የተባለውን ይጋሩታል። በበሽታዉ ሳቢያ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች መሞታቸዉን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Alsoofi

«ኮሌራ በሽታ ተከስቶ ነበረ። ብዙ ወገኖቻችን ሞተዋል።አሁንም ቢሆን በሽታዉ አለ።እና ብዙ ኢትዮጵያዉያንን እየቀጠፈ ነዉ ያለዉ። በወሬ ሰምቼ ሳይሆን በአይኔ ያየሁት ነገር አለ።»

ካሉ በኋላ በሽታዉ ከንፁህ መጠጥ ዉሃ እጥረት ጋር ተያይዞ መከሰቱን ከባለሙያ መስማታቸዉን ገልፀዋል። 
ላለፉት 6 አመታት በጅቡቲ በስደት የሚኖሩ ስማቸዉን መጥቀስ ያልፈለጉ ሌላው ኢትዮጵያዊ በበኩላቸዉ «ተጆራ» በተባለ አካባቢ በዚሁ በሽታ ሰዎች መሞታቸዉን ገልፀዋል።
ያምሆኖ ግን የአካባቢዉ የእርዳታ ድርጅቶችና ነዋሪዎች ከሚያደርጉት መጠነኛ ድጋፍ እንዲሁም በሽታዉ እንዳይዛመት የታመሙትን ለይቶ ከማስቀመጥ ባለፈ የበሽተኞቹን ህይወት ለመታደግ  የሚደረግ ጥረት ብዙም እንዳልሆነ አቶ ኑርዬ ይናገራሉ።

በሽታዉን አለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አጣዳፊ ትዉከትና ተቅማጥ እያለ እንደሚጠራዉ ዘገባዉ አመልክቶ፤ ነገር ግን በአካባቢዉ የኮሌራ በሽታ መከሰቱን «ሚድል ኢስት ኤይ» የተባለዉን የዜና ወኪል ጠቅሶ ዘግቧል። በበሽታዉ 3 የአካባቢዉ ነዋሪዎችና  ከ30 እሰከ 50 የሚጠጉ ስደተኞች መሞታቸዉንም አመልክቷል። ከሟቾቹ መካከል  80 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች መሆናቸዉ ነው የተገለጸው። አቶ ኑርዬ ግን የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ባይ ናቸዉ።

« እነዚህ የታወቁት ናቸዉ።መኪና መንገድ በማይገባበት ለምሳሌ በህገወጥ ስደት ስለመጡ በረሃ ለበረሃ ነዉ የሚሄዱት ።ይሄ ሰዉ ያወቀዉ ሊሆን ይችላል። በዚህ ምክንያት ሰዉ የማያዉቃቸዉ ብዙ አሉ።ስለዚህ ከዚህ በላይ ቁጥሩ ሊያሻቅብ ይችላል።»ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ስደተኞች ያለ በቂ  መረጃ ወደ ጅቡቲ እየመጡ መሆኑን የጠቆመት ኢትዮጵያዉያኑ ፤ ወቅቱ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በመሆኑ ቢያንስ ይህ የሙቀት ወቅት እሲኪያልፍና በሽታዉ ረገብ እስኪል ኢትዮጵያዉያን ተሰዳጆች ወደ ጅቡቲ ከሚያደርጉት ጉዞ ቢታቀቡ መልካም መሆኑን  አሳስበዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የጅቡቲን ዓለም ዓቀፍ የጤና ድርጅትና  ዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተወካዮች በስልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካምሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

Libyen (Symbolbild) afrikanische Migranten auf Rettungsboot
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Palacios

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ