1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጅቡቲን ከኤርትራ ሊያስታርቁ ይሆን?

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 1 2010

ከአስመራው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች ስብሰባ በኋላ የሶስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ወደ ጅቡቲ አቅንተዋል። ተንታኞች ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጅቡቲን ከኤርትራ ለማስታረቅ ጥረት ላይ እንደሆኑ ያምናሉ። በድንበር ይገባኛል ውዝግብ ከኤርትራ የተቃቃረችው ጅቡቲ ግን የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግሥት ወደ ቀጣናው ፖለቲካ መመለሱ አልተዋጠላትም

https://p.dw.com/p/34RaP
Asmara - Premierminister Abiy Ahmed mit somalischem Präsidenten Formajo und Präsident Isaias
ምስል Prime Minister's Office/F. Arega

ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጅቡቲን ከኤርትራ ሊያስታርቁ ይሆን?

የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌሕ ከአምቦሊ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የጅቡቲው አቻቸው ማሕሙድ አሊ ይሱፍ እጆቻቸውን ዘርግተው በፈገግታ ተቀብለዋቸዋል። ከአቶ ኦስማን ሳሌሕ ጋር የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ወርቅነሕ ገበየሁ እና የሶማሊያው አቻቸው አሕመድ ኢሴ አዋድ አብረዋቸው ወደ ጅቡቲ አቅንተዋል። 

ሶስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ጅቡቲ ከማቅናታቸው በፊት ግን የየአገሮቻቸው መሪዎች ለሶስትዮሽ ጉባኤ ትናንት ምሽት በአስመራ ከትመው ነበር። ትናንት አመሻሹን በተደረገው የሶስትዮሽ የመሪዎች ስብሰባ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ሞሐመድ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ጥብቅ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣  ባሕላዊ እና የጸጥታ ግንኙነት እንደሚመሰርቱ ገልጸዋል። የቀጣናውን ሰላም እና ጸጥታ ማጠናከር ሶስቱ መሪዎች በፈረሙበት የጋራ መግለጫ ይፋ ከተደረጉ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። ሶስቱ አገሮች ተስማማንባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ተግባራዊነት የሚያስተባብር ከፍተኛ ኮሚቴ ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያን የምታጎራብተው ከሶስቱ አገራት ጋር ተመሳሳይ የሕዝብ አሰፋፈር ያላት እና በቀጣናው ቁልፍ ቦታ ላይ የምትገኘው ጅቡቲ ግን አልተካተተችም። በጸጥታ ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ጥናት ባለሙያው ኦማር መሐመድ እንደሚሉት ግን የሶስቱ አገሮች መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ በይፋ ባይናገሩትም የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በኤርትራ እና ጅቡቲ መካከል ላለው ቅራኔ መፍትሔ መሻት ሳይሆን አይቀርም። 

"የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፎርማጆ ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን ኤርትራ ወደ ቀጠናው ፖለቲካ መመለሷን በደስታ ተቀብለዋል። መፍትሔ የሚሻ ቅሬታ ያላት ጅቡቲ ግን ራሷን አግልላለች። ስለዚህ በኤርትራ እና በጅቡቲ መካከል አሸማጋይ ለመሆን የሚሞክሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጅቡቲን እንዴት ወደ ትብብሩ ማምጣት እንደሚችሉ እየመከሩ ሳይሆን አይቀርም"

ጅቡቲ እና ኤርትራ ከቀይ ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ከባብ አል-መንደብ ሰርጥ አጠገብ በምትገኘው የዱሜይራ ደሴት የይገባኛል ውዝግብ ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ጀምሮ ሰላም ርቋቸዋል። ከአስር አመታት በፊት ነፍጥ ተማዘው ሲጋጩ ጠባቸው የበረደው በካታር አስታራቂነት እና ሁለቱ አገሮች በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ በሰፈረው ጦሯ ነበር። ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነታቸው ከመሻከር የታደገው ገላጋይ ግን አልተገኘም። ዛሬ የኤርትራ አቻቸውን እጃቸውን ዘርግተው የተቀበሏቸው የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ከአንድ አመት በፊት ሁለቱ አገሮች የሚወዛገቡበትን የድንበር አካባቢ ኤርትራ በኃይል ተቆጣጥራለች ሲሉ ከሰው ነበር። ጅቡቲ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ትፈልጋለች ያሉት ይሱፍ ከተገደደች ግን ወደ ጦርነት ለመግባት አገራቸው እንደማታፈገፍግ በወቅቱ ገልጸዋል። 

Dschibuti Präsident Ismail Omar Guelleh
ምስል Picture-allaince/dpa/J. Warnand

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረውን ቅራኔ ሊፈቱ ይችላሉ ያሏቸውን እርምጃዎች መውሰድ ሲጀምሩ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት በቀጣናው ፖለቲካ ያለው ሚና መቀየር ጀምሯል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አስመራ ሲያቀኑ ሁለተኛቸው ሲሆን የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጭምር አስመራ አምርተው ነበር። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ፈቃደኛ ቢሆኑም ጅቡቲ ግን ለዚህ ዝግጁ አይደለችም። 

"ኤርትራ ወደ ቀጣናው ፖለቲካ ተመልሳ መቀላቀሏን ጅቡቲ ገና በይሁንታ አልተቀበለችውም። ጅቡቲ መጀመሪያ በመካከላቸው ያለው ቅራኔ በተለይ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ለመጣሉ ምክንያት ከሆኑ ሁለት ጉዳዮች አንዱ የሆነው የድንበር ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ትፈልጋለች። ወደ ት በወደብ አገልግሎት ጉዳይ ከኤርትራ በኩል ስለሚገጥማት ውድድር ሐሳብ ገብቷት ሊሆን ይችላል። ቁልፉ ጉዳይ ግን መፍትሔ ያልተገኘለት የድንበር ውዝግብ ነው"። 

Karte Eritrea Djibouti DEU
ምስል DW

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዕርቅ ጀርባ ላቅ ያለ ሚና ተጫውታለች የሚባልላት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሶማሊያ እና በጅቡቲ ልታስከብረው የምትሻ ጥቅም አለ። የጸጥታ ተንታኙ ኦማር መሐመድ የአስመራው የሶስትዮሽ ጉባኤ ከቀጠናው የመነጨ እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ግፊት የተደረገ አይደለም ባይ ናቸው። 

"የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ረገድ ኤኮኖሚያዊ መተማመኛ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ፖለቲከኞቹ የመጀመሪያውን ግንኙነት እንዲያደርጉ እገዛ ሊኖራቸው ይችልም ይሆናል። እኔ እንደማስበው ግን ሙሉ በሙሉ ተነሳሽነቱ ከቀጠናው በተለይም ከአዲስ አበባ እና ከአስመራ በኩል የመጣ ነው"

የጸጥታ ጥናት ባለሙያው ኦማር መሐመድ ጅቡቲ ያላትን ቅሬታ የመፍታቱ ጉዳይ ለቀጣናው ሀገራት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ኦማር እንደሚሉት ለአወዛጋቢው የድንበር ጉዳይ መፍትሔ ከመሻት ባሻገር ኤርትራ እና ጅቡቲ የኢትዮጵያን ገበያ የወደብ አገልግሎት በማቅረብ ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት እርስ በርስ ፉክክር ውስጥ የማይገቡበትን መንገድ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።  

እሸቴ በቀለ 

አዜብ ታደሰ