1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፈንቅለ መንግስት ወይስ ሌላ ፤ለምን?

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2011

ኢትዮጵያ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሟ፣ ከባለአራት ኮኮቡ ጄኔራል ከሰዓረ መኮንን እስከ ተራ ወታደሮቿ፣ ከርዕሠ መስተዳድር አምባቸዉ መኮንን እስከ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ፣ ከአማራ የሰላምና የደሕንነት ኃላፊ ከብርጌድየር ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌ በጡረታ እስከ ተገለሉት ሌትናንት ጄኔራል ገዛኢ አበራን ለማፍራት ስንት ዘመን ጠበቀች?

https://p.dw.com/p/3L0Oh
Äthiopien Addis Ababa Sicherheitskräfte nach Putschversuch
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

መፈንቅለ መንግስት ወይስ ሌላ ፤ለምን?

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን ከስልጣን ለማስወገድ ግንቦት 1981 የተሞከረዉን መፈንቅለ መንግሥት ከመሩት አንዱ በተለይም የአስመራዉን ያስተባበሩት ጄኔራል ደምሴ ቡልቴ ነበሩ። ጄኔራሉ ከብዙ አመታት በፊት በመሠረቱትና ባደራጁት የአየር ወለድ ጦር እንደተገደሉ የብሪታንያዉ ዓለም አቀፍ ማሰራጪያ ጣቢያ (BBC) ጋዜጠኛ «ኢትዮጵያ የጦር መሐንዲሷን ገደለች» ብሎ ነበር። ከያኔ እስከ አምና የተሞከሩ መፈንቅለ መንግስታትንም ሆነ የተገደሉ የጦር ወይም የፖለቲካ መሐንዲሶችን በርግጥ በትክክል አናዉቅም።ካምና እስከ ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ ለባለስልጣናት የተቃጣ የግድያ ሙከራ የዋሕ ሰልፈኞችን መግደል፣ማቁሰል፤ማሸበሩ ግን እናዉቃለን።ቢያንስ አንድ መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ነግረናዉናልም።ቅዳሜ ኢትዮጵያ የፖለቲካና በ 40 ዘመን ዉጊያ፣የጦር አመራር የተፈተኑ የጦር «መሐንዲሶችዋን» ገደለች።የመገዳደል ዑደት፣ የፖለቲካ ጅልነት፣ ርግማን ወይስ? ብዙ ጊዜ ተጠይቋል? እንደገና ይጠየቃልም። እንደገና እንጥይቅ

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እስከ ቃል አቀባያቸዉ፣ከክልል አስተዳዳሪዎች እስከ መገናኛ ዘዴዎቻቸዉ እንዳሉት ቅዳሜ ባሕርዳርና አዲስ አበባ የሆነዉ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትር ፅሕፈት ቤት የፕረስ ሴክሪተሪያት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁት ትናንት በሰጡን ቃለ መጠይቅ የተደራጀ፣የተቀናጀ እና በዕቅድ የተመራ ብለዉታል ሴራዉን ።ገለልተኛ የሚባሉ መገናኛ ዘዴዎች በቀጥታ «መፈንቅለ መንግስት» ከማለት ይልቅ መንግሥት «መፈንቅለ ያለዉ» ማለትን መርጠዋል።ካነጋገርናቸዉ ታዛቢዎች አንዳዶቹ «ክልላዊ መፈንቅለ መንግሥት»፣ሌሎቹ ደግሞ «ግድያ» ብቻ ማለቱን ይመርጣሉ። አማራ መስተዳድር የሚንቀሳቀሰዉ ተቃዋሚዉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን በምሕፃሩ) ቃል አቀባይ ክርስቲያን ታደለ ግን መፈንቅለ መንግሥት ማለቱን አለማለቱንም አልፈቀዱትም።«የግድያ ወንጀል» ይሉታል።

 መፈንቅለ መንግሥት፣ ክልላዊ መፈንቅለ መንግሥት፣ ግድያ፣ የግድያ ወንጀል ተባለም ሌላ አንድ ነገር ሐቅ ነዉ።ፖለቲከኞች፣የፀጥታ ሐላፊዎች፣ የጦር ጄኔራሎች፣ ወታደሮች እና የልዩ ኃይል አባላት ተገድለዋል።አጠያያቂ፣ አነጋጋሪ፣ ሰበብ ምክንያት አፈላላጊዉ ጉዳይም ይህ ነዉ።

ኢትዮጵያ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሟ፣ ከባለአራት ኮኮቡ ጄኔራል ከሰዓረ መኮንን እስከ ተራ ወታደሮቿ፣ ከርዕሠ መስተዳድር አምባቸዉ መኮንን እስከ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ፣ ከአማራ የሰላምና የደሕንነት ኃላፊ ከብርጌድየር ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌ በጡረታ እስከ ተገለሉት ሌትናንት ጄኔራል ገዛኢ አበራን ለማፍራት ስንት ዘመን ጠበቀች? ስትስ አወጣች? ሌላ መልስ የለሽ ጥያቄ።

Äthiopien Addis Ababa nach Putschversuch
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

ብቻ ለፖለቲካ ዛር ቆሌዋ የጄኔራሎችዋችን፣ ዶክተሯን፣ የሕግ አዋቂዋን፣የካድሬ አደራጇን፣ ቁጥሩ በይፋ ያልተነገረ ወጣት ወታደሯን ደም «ጪዳ» አደረገች።ምን ይሆን ምክንያቱ? በኪል (ብሪታኒያ) ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አወል ቃሲም ትክክለኛዉን ምክንያት የሚያዉቁት ገዳይ አስገዳዮች ወይም መንግስት ነዉ ይላሉ።እንደ ታዛቢ ግን ቀጠሉ።

                             

ከማዕከላዊ ጎንደር እስከ ሰሜን ሸዋ አጣዬ፣ ከከሚሴ እስከ እስከ በኒ ሻንጉል ጉሙዝ ድንበር በየጊዜዉ አማራ መስተዳድርንና አጎራባቾቹን ሲያብጥ የነበረዉን ግጭት፣ግድያና ሁከት የክልሉ ይሁን የፌደራሉ መንግሥታት በቅጡ መቆጣጠር አልቻሉም።ርዕሠ ከተማ ባሕርዳር ከጭነት መኪና ሾፌር እስከ ተራ መንገደኛ ሲገደል፣ ሲዘረፍ፤ሲሸማቀቅባት፣ ከባጃጅ ሾፌሮች እስከ ፖሊሶች በዘራፊነት ሲሰማሩባት፣ የፖሊስ ወይም የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አዛዦች የጦር መሳሪያ «ሲቸረችሩባት» የአማራ ክልል ይሁን የፌደራሉ መንግሥት ፖለቲከኞች በርግጥ የትነበሩ?።ወይስ ለመጠፋፋት ይዶልቱ ነበር እንበል ይሆን? እንደገና ጥያቄ?

«መፈንቅለ መንግሥት» የተባለዉን ሴራ የመሩና ያቀነባበሩ የተባሉት ብርጌድየር ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌ ከዚሕ ቀድም መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ አሲረዉ ነበር በሚል ወንጀል ለበርካታ ዓመታት ታስረዉ የተፈቱት ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም በፊት ነበር።እሳቸዉ በተወነጀሉበት የመፈንቅለ መንግሥት ሴራን በካሸፉ ሒደትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተቃጡ መፈንቅለ መንግስታት የጠፋ ሕይወት ስለመኖር አለመኖሩ በግልፅ የተነገረ ነገር የለም።

በዚሕም ምክንያት ኢትዮጵያ በመፈንቅለ መንግሥት ይሁን በፖለቲካ ሴራ፣ ባንድ ጊዜ የበርካታ ባለስልጣናት ሕይወት ሲጠፋባት ከ1981ዱ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወዲሕ የቅዳሜዉ የመጀመሪያዉ ነዉ። ግድያዉ ለኢትዮጵያ ታላቅ ተሐድሶ፣ ለአፍሪቃ አብነት፣ ለዓለም ዴሞክራሲ ተስፋ ለተባለዉ ፖለቲካዊ ለዉጥ ደግሞ ዶክተር አወል እንደሚሉት «ትልቅ ችግር ፈጣሪ» ነዉ።

Äthiopien TV Ansprache Premier Abiy Ahmed nach Putschversuch
ምስል AFP/Ethiopian TV

አምና አዲስ አበባ አደባባይ በወጣ ሕዝብ መሐል ቦምብ ፈነዳ፤ ሰዎች ተገደሉ፣ቆሰሉ፣ ተረበሹም።ጥቂት ቆይቶ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቤተ-መንግስት በጦር ኃይል ባልደረቦች ተወረረ። ከዚያ በፊት እና በኋላ ከሰሜን ጎንደር እስከ ጌድኦ፣ ከበኒ ሻንጉል እስከ ጂጂጋ፣ ከወለጋ እስከ ቡራዩ በተደረጉ ግጭቶች በርካታ ሕዝብ ሞቷል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቅሏል።ለነበረዉ ችግር መፍትሔ ሳይበጅ ኢትዮጵያ እንደገና አንጋፋ የጦር መኮንኖችዋን፣ ፖለቲከኞችዋንና ወታደሮችዋን «ደፋች» ።ሌሎቹን ወሕኒ ዶለች። እንደገና ዶክተር አወል።ከእንግዲሕስ? እስኪ ቸር ያሰማን እንበል።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ