1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ አዳኝ ያጣች ሐገር

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2014

የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋርን ሕዝብ የፈጀዉ --- ጦርነት፣ መተከልን ያንገረገበዉ ግድያ፣ሰሜን ሸዋን ያነፈረዉ ጥቃት ገለል-ቀለል ማለቱ አስገምግሞ ሳበቃ ደዋ ጨፋ ላይ የተዋለዉ ዘግናኝ ግፍ ፈጋ።ሰሞኑን ጋምቤላ፣ዴምቢዶሎ፣ ጊምቢ ላይ የረገፈዉ አስከሬን ሲቆጠር፣የክሳይ ንዳጅ አመድ ሲዛቅ ጊምቢ መዳረሻ ዳግም ተንፈቀፈቀች።

https://p.dw.com/p/4CxlS
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ኢትዮጵያ አዳኝ ያጣች ሐገር

የኢትዮጵያ መንግስትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪዎች ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን ባለፈዉ ሳምንት በየፊናቸዉ አስታዉቀዋል።ሁለቱ ወገኖች ባለፈዉ መጋቢት ያወጁት የሰብአዊነት ተኩስ አቁም ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ባይሆንም አሁንም  እንደተጠበቀ ነዉ።ይሁንና ቀጥታዉ ዉጊያ ጋብ ቢልም ሁለቱ ወገኖች ለዉጊያ የሚያደርጉት ዝግጅት፣ በተለይ ከሕወሓት ጋር የጋራ ትብብር የመሰረተዉ የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም ኦነግ ሸኔ  የሚያደርሰዉ ጥቃትም እንደቀጠለ ነዉ።አንዳድ ታዛቢዎች እንደሚሉት የዉጊያ ዝግጅቱ፣  ግድያና ግጭቱ ካልቆመ ድርድሩ ዉጤት አያመጣም ይላሉ።ሌሎች ደግሞ የድርድሩን ሐሳብ «ጊዜ መግዢያ ወይም የዉጪዉን ጫና ማስተንፈሻ» በማለት ይገልፁታል።የየአካባቢዉ ጥቃት እንዴትነት፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ዕዉነትና የድርድሩ ሐሳብ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

ጎንደር በጠረራ ፀኃይ ለተነረሸኑ ነዋሪዎችዋ ሶደቃ አዉጥታ ሳትጨርስ  እንቶሊ ያለአበሳቸዉ ለተገደሉ ወገኖችዋ አረገደች።ወለጋ ላይ የሰፈረዉ የዘር-ጥላቻ-ዛር ዘንድሮም እንዳምና ሐቻምናዉ ለም፣ዉብ ምድሯን በደም፣ በየዋሕ፣ንፁሐን ገበሬዎቿ ደም እያጎደፈዉ ነዉ።ደቡብ ኢትዮጵያ ደራሼ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጉጂ፣ኮንሶ ሌላምጋ የተቋጠረዉ የጎሳ፣ የግዛት፣ የሥልጣን ነቀርሳ በየጊዜዉ እያመረቀዘ መቶዎችን ይፈጃል።

ኢትዮጵያ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ አምና ነሐሴ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ እንዳሉት ኢትዮጵያዉያንን የሚያስተሳስረዉ ማሕበራዊ መን እየተበጠሰ ነዉ።

Äthiopien Bürgerkrieg, Reportage aus Abaala, an der Grenze zwischen Tigray und Afar
ምስል Mariel Müller/John Irungu/DW

 «ትግራይ የነበሩት  የጦር ግንባሮች አሁን አማራና አፋር ክልሎች ደርሰዋል።ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ሌሎች ተዋኞች ሁሉን አቀፍ ክተት በማወጅና በየአካባቢዉ ያሉ ታጣቂዎች በማንቀሳቀስ ዉጊያዉን እየተቀየጡ ነዉ።ጠብ ቀስቃሽ ንግግሮችና ሰዎችን በጎሳ መፈረጅ የሐገሪቱን ማሕበራዊ መንን እየበጠሰዉ ነዉ።»

ትልቁ የዓለም ዲፕሎማት ዋሹ ማለት ያስዋሻል።ያሉትን ካሉ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀረዉ።ኢትዮጵያ ግን ዘንድሮም እንደአምናዉ ቁል ቁል እየዘቀጠች ነዉ። የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋርን ሕዝብ የፈጀዉ  በስደት፣ መደፈር ያሰቃየዉ፣ የደሐ ጥሪቱን ያከሰለዉ  ጦርነት፣ መተከልን ያንገረገበዉ ግድያ፣ሰሜን ሸዋን ያነፈረዉ ጥቃት ገለል-ቀለል ማለቱ አስገምግሞ ሳበቃ ደዋ ጨፋ ላይ የተዋለዉ ዘግናኝ ግፍ ፈጋ።ሰሞኑን ጋምቤላ፣ዴምቢዶሎ፣ ጊምቢ ላይ የረገፈዉ አስከሬን ሲቆጠር፣የክሳይ ንዳጅ አመድ ሲዛቅ  ጊምቢ መዳረሻ ዳግም ተንፈቀፈቀች።

ባሕርዳር በዘመቻ ያሰረቻቸዉን ተጠርጣሪዎች ስትቆጥር፣ አዲስ አበባ በታሰሩ ጋዜጠኞች ሙግት ስትባትል፣ አርሲ፣ ጋሌማ ላይ የፖሊስና የወረዳ ሹማምንቷን ሕይወት በታጣቂዎች ጥይት ተቀማች።ደም ተግታ፣ ደም የሚጠማት፣ሙታንዋን ሳትቀብር ሙት የሚከመርባት ወለጋ ጊምቢ አጠገብ እንደገና መቶዎች ተጨፈጨፉባት-ቅዳሜ።ፈጣሪን መማለጂያ፣ መፀለያ፣ቤተ እምነቶች ከደካሞች መሸሺጊያነት ወደ ደካሞች መሰዊያ ጋጣነት ተቀየሩባት።

ለምን? መልስ የለሽ-ማብቂያ የለሽ ጥያቄ።የዓለም አቀፉ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ሰጪ ተቋም (IDEA-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ባልደረባ ዶክተር አደም ካሴ ማሕበረሰባዊ ዉድቀት ይሉታል-ቀዉሱን።አስፈሪም።

                                 

ዕዉቁ የጆኦ ፖለቲካ አዋቂና የፖለቲካ ሐያሲ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ2002 ባሳተሙት መፅሕፋቸዉ የኢትዮጵያን ምስቅልቅል ለማስወገድ ከጠቆሟቸዉ ሁለት መፍትሔዎች«ይሕንን አማራጭ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስልኝም» ያሉት አንዱ አማራጭ  «ወደ ሶማሊያ አስከፊ ሁኔታ ከመግባታችን በፊት ለአዉሮጳ ወይም ለአሜሪካ ወይም ለተባበሩት መንግስታት ሐገሪቱን በኮንትራት ሰጥተን---» ይላሉ።

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ከ10 ዓመት በኋላ ዘንድሮ የሚሆነዉን ቢያዩ-ቢሰሙ ምን ይሉ?ብቻ ጋዜጠኛ ዜናነሕ መኮንንም ባንድ ዉይይታችን « የዕግር ኳስ ተጫዎች ወይም አሰልጣኝ ከዉጪ እንደምንቀጥረዉ ሁሉ መሪዎችን በኮንትራት ብንቀጥርስ----ዓይነት » ያለኝን አስታዉሳለሁ።ቢጨንቀዉ።

ኢትዮጵያ ዘር፣ኃይማኖ፣የፖለቲካ ማሕበራትን እየመረጡ ለደረሰዉ ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉ፣ የዉጪ መንግስታት፣ ድርጅቶችና ተቋማትን ለየችግሮቹ ሁሉ የሚያወግዙ፣ገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎችን የሚያራክሱ ባለስልጣናት፣ አቀንቃኞች፣ የኃይማኖት ሰባኪዎች፣ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አጫፋሪዎች ሞልቶ ተርፏታል።

ኬኔዲን መጥቀስ አያስፈልገኝም ግን ከዉግዘት መጠቋቆሙ ባሻገር  «ለሐገርና ሕዝቤ እኔ ምን አደረኩ?የቱጋና ለምን ተሳሳትኩ? ጠበኞችን እንዴት ልሸምግል፣ ወይም ለጋራዉ ችግር የጋራ መፍትሔ ልፈልግ» የሚል ኢትዮጵያዊ ድምፁ አለመሰማቱ  በርግጥ ከሚያስፈራዉ ነገር ሁሉ በላይ ሊያስፈራ ይገባል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በየግጭት ጦርነቱ ካለቀና ከሚያልቅባት ሕዝብ በተጨማሪ የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት 30 ሚሊዮን ሕዝቧ የምግብ ምፅዋት ጠባቂ ነዉ።አንድ ሚሊዮኑ አስቸኳይ ርዳታ ካላገኘ ይሞታል።ሕጻናት አሁንም በምግብ እጦት ሞተዋል።

ኢትዮጵያን ሰቅዘዉ የያዝዋት የዕልቂት-ፍጅት፣ የጥፋት-ዉድመት፣ የችግር-ችጋር ሰንሰለቶች በዕለት እንዳልተከሰቱ ሁሉ መፍትሔያቸዉም በዉሎ አይገኝም።ይሁንና የብዙ ኪሎ ሜትሮቹ ጉዞ በእርምጃ እንደሚጀመር ሁሉ 19ኝ ወራት ያስቆጠረዉን ጦርነት ለማስቆም ከአዲስ አበባና ከመቀሌ የተሰማዉ የድርድር ፍላጎት ዶክተር አደም እንደሚሉት የተስፋ ጭላንጭል ፈንጣቂ ነዉ።

                                   

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እስካሁን በሚስጥር ወይም በስማበለዉ እየተደራደሩ መሆናቸዉን የተለያዩ ወገኖች ዘግበዋል።አፍሪካን ኮንፊደሻል የተባለዉ መፅሔትማ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓ,ብይ አሕመድና የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በስልክ መነጋገራቸዉን፣ የሁለቱ የጦር መኮንኖች ስለምርኮኛ ልዉዉጥ መወያየታቸዉን ጭምር ዘግቦ ነበር።ይሁንና ሁለቱ ወገኖች በሚስጥር ተነጋገሩ የሚለዉን ዘገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ «ተረት» ብለዉታል።

Äthiopien ehrt seine Polizeikräfte
ምስል Wang Ping/XinHua/dpa/picture alliance

ሊቀመንበር ደብረፅዮንም ፓርቲያቸዉ ካወጀዉ ጊዚያዊ ተኩስ አቁም ሌላ ከመንግስት ጋር የተደረገ ስምምነትም ሆነ ድርድር የለም ብለዋል።ሕወሓት ባለፈዉ ማክሰኞች ባሰራጨዉ ግልፅ ደብዳቤ «ግልፅ፣ ያልወገነና በመርሕ ላይ የተመሰረተ» ባለዉ ድርድር ለመካፈል ፈቃደኛ ነዉ።ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ገና በኮሚቴ የሚያስጠናዉ የመደራደሪያ ነጥብ በሕወሓት በኩል በቅድመ ሁኔታዎች የተሞላ ነዉ።

ሕወሓት ከደረደራቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች  «ወራሪ» ያላቸዉ ኃይላት ከምዕራባዊ ትግራይ እንዲወጡ የጠየቀበት አንዱ ነዉ።የትግራይ ኃይል የሚባለዉ ታጣቂ ቡድንም ትጥቁን እንደማይፈታ፣የአፍሪቃ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የኦሎሴጎን ኦባሳንጆ ሽምግልና እንደማይቀበልም  አስታዉቋል።

Äthiopien Bürgerkrieg, Reportage aus Abaala, an der Grenze zwischen Tigray und Afar
ምስል privat

ከድርድር በፊት የሚደረደሩት ቅድመ ሁኔታዎች ገና በወጉ ያልታየዉን የሰላም ተስፋ ያጨናጉለዋል የሚል ስጋት ማሳደሩ አልቀረም።አንዳድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ ሁለቱ ወገኖች የድርድሩን ሐሳብ የተቀበሉት አንድም ጊዜ ለመግዢያ፣ ሁለትም የዉጪዉን ጫና ለማስተንፈሺያ ነዉ።የዴሞክራሲና የሕግ አዋቂዉ ዶክተር አደም ካሴ እንደሚሉት ግን ድርድሩ ከተጀመረ የቅድመ ሁኔታዎቹ ጥያቄ እየለሰለሰ፣ የተደራዳሪዎች ድብቅ ፍላጎትም እየተቀየረ መምጣቱ ይቀርም።

                                        

በጦርነቱ ከኤርትራ እስከ ኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ኦነግ ሸኔ ያሉ ኃይላት ካንዱ ወይም ከተቃራኒዉ ወግነዉ ተዋግተዋል።ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገዉ ድርድር ሒደትና ዉጤቱ የየተሳታፊዎቹን ፍላጎት ከሚያረካ እንዲሆን ተደራዳሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አደራዳሪዎችም ጭምር ሊጠነቀቁ ይገባል።በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተዋለዉ ግፍም ሊነዘነጋ አይገባም።ወንጀለኞች በሕግ መጠየቅ አለባቸዉ።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለዉን ሒደት በቅርብ የሚከታተለዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም ምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ፣የገንዘብ ጉልበቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከተጠቀመበት ታዛቢዎች እንደሚሉት ድርድሩ ቢያስቸግርም ለፍሬ መብቃቱ አይቀርም።ያዉ ተስፋ ነዉ መቼም።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ