1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ምን ይዞ መጣ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

የኢትዮጵያ ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን አስይዘው ከባንክ እንዲበደሩ የሚፈቅድ አዋጅ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። በአዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ባለመብቶች መሬታቸውን ማከራየት እና ከባለ ሐብቶች ጋር በጋራ ማልማት ጭምር ተፈቅዶላቸዋል።

https://p.dw.com/p/4g9dI
የኢትዮጵያ ገበሬ የታጨደ ስንዴ ይዞ አዳማ
የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የኢትዮጵያ ገበሬዎች እና አርሶ አደሮች በገጠር መሬት ይዞታ ላይ ያላቸውን የተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ የታቀደ ነው ተብሏል። ምስል Stefan Trappe/Imago Images

አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ምን ይዞ መጣ?

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሣምንት ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች መሬታቸውን በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ እንዲበደሩ የሚፈቅድ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አጽድቋል። አዋጁ የጸደቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ አዲስ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ሥራ ላይ ባዋለ በአንድ ወር ገደማ ልዩነት ነው።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 17 ቀን፣ 2016 የጸደቀው ፖሊሲ ግብርናን “ከሌሎች የኤኮኖሚ ዘርፎች ጋር የበለጠ የሚያስተሳስር” እና “በገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት” የሚያግዝ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲው “ትልቁ ማስፈጸሚያ” የገጠር መሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር አዋጅ እንደሆነ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ከማጽደቁ በፊት ባደረገው የመጨረሻ ክርክር ላይ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብብሳቢው አቶ ሰለሞን ላሌ “የይዞታ መብታቸውን አርሶ አደሮቻችን በባንክ አስይዘው ገንዘብ የሚያገኙበት፤ የፋይናንስ እጥረታቸውን የሚሸፍኑበት፤ ምርት እና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ዕድል የሚሰጥ አዋጅ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ በእርግጥ ለውጥ እያመጣ ነው?

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዋጅ ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች በመሬታቸው ያላቸውን የመጠቀም መብት “በዕዳ ዋስትና ማስያዝን” ይፈቅዳል። ይኸ የገጠር መሬት ባለቤቶች ባንኮችን ጨምሮ ከፋይናንስ ተቋማት ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በብድር እንዲያገኙ የሚፈቅድ ነው።

በግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ የሚሠራው መልካ ኢትዮጵያ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የቦርድ ሊቀ-መንበር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ መምህር ዶክተር መለሰ ዳምጤ ሕጉ ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች የሚያስፈልጋቸውን አንገብጋቢ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ መንገድ እንደሚከፍት ያምናሉ።

በአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝኃ ሕይወት መመናነን እና የአፈር ለምነት መጎሳቀል ሳቢያ የኢትዮጵያ ገበሬ እንደወትሮው ሥራውን መከወን ከማይችልበት ደረጃ እንደደረሰ የሚናገሩት ዶክተር መለሰ “ገበሬ ብድር ካላገኘ ማምረት ቀላል አይሆንለትም። እንደ ድሮው በቀላሉ ማምረትን የማይፈቅዱ ሁኔታዎች በብዛት ተፈጥረዋል። ብዙ የአካባቢ ለውጦች ስላሉ ብዙ ሥራ፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞ እና አዲስ ዋና መሥሪያ ቤቶች
የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ገበሬዎች በእርሻቸው የመጠቀም መብታቸውን እንደ ማስያዣ ተጠቅመው እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሉ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ እንዲበደሩ ፈቅዷል። ምስል Eshete Bekele/DW

የብድር አቅርቦት ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች በትንሹ የአፈር ማዳበሪያ፣ ጸረ-አረም እና ጸረ-ተባይ መግዛት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ከፍ ሲል የማረሻ እና የማጨጃ ማሽኖች ለመግዛት፣ ለእርሻ ማሳቸው የመስኖ ግንባታዎች ለማከወን የሚያስፈልጋቸውን ዕድልም የሚከፍት ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ” እንደሆነ ተደንግጓል። መሸጥ እና መለወጥም አይቻልም። በአዲሱ አዋጅ “አርሶ አደሮች በማስያዣ የሚሰጡት በመሬት የመጠቀም መብታቸውን” እንጂ መሬቱን አይደለም።

ገበሬው ወይም አርብቶ አደሩ “ብድሩን መመለስ ባይችል ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አበዳሪው በመሬቱ የሚጠቀምበት የጊዜ ጣሪያ ከ10 ዓመት” እንዳይበልጥ ተደንግጓል።

“የፋይናንስ ተቋማት ሊሸጥ ሊለወጥ የማይቻልን ንብረት ይዞ ገንዘባቸውን አበድሩ ማለት በጣም ከባድ ነገር ነው” የሚሉት ዶክተር መለሰ መንግሥት እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመሳሰሉ ተቋማት እንዲያበድሩ ግፊት ሊያደርግ እንደሚችል ይጠብቃሉ።

የኢትዮጵያ ገበያ ለውጭ ባለወረቶች ሲፈቀድ ባለሙያዎች ተስፋ እና ሥጋት ተሰምቷቸዋል

የኢትዮጵያ ባንኮች የብድር አሰጣጥ በማስያዣ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ያገለለ በመሆኑ የበረታ ወቀሳ የሚቀርብበት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሚያዝያ ይፋ ያደረገው ደረገው ዘገባ የሀገሪቱ ባንኮች የብድር አገልግሎት ለጥቂት ተበዳሪዎች የሚሰጥ እንደሆነ አሳይቷል። በዘገባው መሠረት ባንኮች ከሰጡት 1.9 ቢሊዮን ብር ገደማ 23 በመቶውን የወሰዱት ዐሥር ተበዳሪዎች ብቻ ናቸው።

እስከ 90 በመቶ የሚደርሰውን የግብርና ምርት የሚያመርቱት ባለ አነስተኛ ማሳ ገበሬዎችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በከተሞች የተከማቹት ባንኮች ከሚሰጡት የብድር አቅርቦት የራቁ ሆነው ቆይተዋል።

አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዋጅ ተገፍተው የቆዩት ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች ብድር እንዲያገኙ የሚፈቅድ ቢሆንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ረዳት ፕሮፌሰር መለሰ ዳምጤ እንደሚሉት አተገባበሩ ፈታኝ ነው።

Äthiopien | Sorghum & Teff Farm
በአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝኃ ሕይወት መመናነን እና የአፈር ለምነት መጎሳቀልን የመሳሰሉ ችግሮች የሚፈታተኗቸው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ለሥራቸው ግብዓት እና ቴክኖሎጂ ለመሸመት የብድር አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምስል DW/E. Bekele

የኢትዮጵያ ገበሬዎች ማሳ እጅግ የተበጣጠሰ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር መለሰ “ለዐሥር ሺሕ ገበሬ ያበደረ አንድ ባንክ ዐሥር ሺሕ ገበሬ ሳይመልስ ቢቀር ዐሥር ሺሕ መሬት ሲያስተዳድር ሊኖር ነው ማለት ነው” የሚል ሥጋት አላቸው። ይኸ ለአበዳሪ ተቋማት መሬት የማስተዳደር ኃላፊነት እንደሚያስከትል የገለጹት የሕግ ባለሙያው “አፈጻጸሙ ቀላል አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።

የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ባለ ይዞታዎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን የካፒታል መዋጮ በማድረግ ከባለ ሐብቶች ጋር በሚገቡት ውል መሠረት የልማት ሥራ እንዲያከናውኑ ጭምር ፈቅዷል። በአዋጁ መሠረት መሬት በውርስ ወይም በስጦታ ማስተላለፍ፣ ኩታ ገጠም ማድረግ፣ ይዞታን ማቀራረብ እና መለዋወጥ ይቻላል።

“የመንግሥት ባለቤትነት እንዳለ ሆኖ የመሬት ሕጉ ባለው ነገር ውስጥ ነው ለመጫወት ሙከራ እያደረገ ያለው። ለቀቅ ያለ የማከራየት መብት እንደ መስጠት ብሏል” ያሉት ዶክተር መለሰ በገጠር መሬት ላይ የሚገኝ ንብረት ለመሸጥ መፈቀዱን በአዎንታዊነት ይጠቅሳሉ።

ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንዲያስተናግድ ትፈልጋለች

አብዛኞቹን ጉዳዮች የክልል መንግሥታት የማስፈጸም ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቷቸዋል። ክልሎች ያቋቋሟቸው የገጠር መሬት አስተዳደር ተቋማት እስከ ቀበሌ በተዘረጋ መዋቅራቸው የመሬት አከራዮች እና ተከራዮች፤ ይዞታቸውን መለዋወጥ የሚፈልጉ ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ከባለ ሐብቶች ጋር ማልማት የሚፈልጉ ባለ ይዞታዎችን ማስተናገድ አለባቸው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ውይይት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ “ማንኛውም ሰው የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገ-ወጥ መንገድ የወረረ ከብር 30,000 እስከ 100,000 ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል” ሲሉ አስረድተዋል።

በሰብሳቢው መማብራሪያ መሠረት “ማንኛውም ሰው መሬት የሸጠ ወይም የገዛ እንደሆነ ከ100,000 እስከ 200,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።”

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ