1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ታንሠራራ ይሆን?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2013

ልጅ-ካዋቂ፣ ሴት-ከወንድ፣ በሽተኛ-ከጤነኛ፤ ሳይለይ በዘሩ ብቻ እየለዩ ሰዉን የመግደሉ ጭካኔ የኢትዮጵያዊያንን እዉቀት፣እድገት፣ሰብአዊነት፣ ኃይማኖተኝነትም እያጠያያቀ ነዉ።የካለን ኮሌጅ ዩናይትድ ስቴትስ ባልደረባ  ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ «ሜካናይዝድ» ይሉታል-ግድያዉን። ርፍረፋ።

https://p.dw.com/p/3sbUB
Äthiopien Bahir Dar | Proteste gegen Ermordung und Vertreibung von ethnischen Amharas
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የኢትዮጵያ በነበረችበት ትቀጥል ይሆን?


ኢትዮጵያን ካለችበት ፖለቲካዊ ምስቅልቅል፣ ጎሳዊ ግድያ-ግጭት የከተተዉ ምድነዉ? መፍትሔስ አለዉ ይሆን? ከዚሕ በፊት ብዙዎች፣ ብዙ ጊዜ ጠይቀናል።ምስቅልቅል፣ ግጭት ግድያዉ ግን ባሰ እንጂ አልቀነሰም።ዛሬም እንደገና እንጠይቅ። ሁለት ጥያቄ፣ አራት ተናጋሪዎች ሶስት መልስ። አብራችሁኝ ቆዩ።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ ሞስኮ በሚመላለሱበት በ1960ዎቹ ማብቂያ ባንዱ ጉዟቸዉ ከያዟቸዉ ሰነዶች አንዱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ካርታ ነበር።«ካርታዉ» መንግስቱ እንዳሉት፣ መንግሥታቸዉ «ፀረ አብዮት» የሚላቸዉ ኃይላት የሚቆጣጠሩትን ወይም ጥቃት የሚያደርሱበትን አካባቢ የሚያሳይ ነዉ።
አዘጋጆቹ ብልጦች ናቸዉ።ኢትዮጵያ ከያኔዋ ሶቭየት ሕብረት ጠቀም ያለ ጦር መሳሪያ እንድታገኝ አስበዉ  «ፀረ ሕዝቦች» የሚሏቸዉ ተቃዋሚዎቻች የሚቆጣጠሩ ወይም የሚያጠቁትን አካባቢ ጨመርመር አድርገዉ ምልክት አድርገዉበታል።ሁሉም ምልክቱ በቀይ ቀለም ነዉ የተደረገዉ።
ሊቀመንበር መንግስቱ ለሶቭየቱ ሕብረቱ መሪ ለሊዮኔድ ብሬዥኔቭ በቃል የሚያስረዱትን ካስረዱ በኋላ የሚሉትን በስዕል ለማረጋገጥ ያን ካርታ ጠረፄዛ ላይ ሲያነጥፉት ከጥቂት አካባቢዎች በስተቀር የኢትዮጵያ ግዛቶች በሙሉ ቀይ በቀይ ተለቅልቀዋል።ፀረ-አብዮተኞች ተቆጣጥረዉታል ወይም እያጠቁት ነዉ ማለት ነዉ ትርጉሙ።
ብሬዥኔቭ ካርታዉን እንዳዩ እንግዳቸዉን ጠየቁ «ጓድ ሊቀመንበር ይሕን ሁሉ ሥፍራ ፀረ-አብዮተኞች ከያዙት አብዮተኖቹ (የመንግስት ኃይላት)  ያላችሁት የትነዉ?» ብለዉ።በአርባ አምስተኛ ዓመቱ ዘንድሮም ብዙ ኢትዮጵያዉያን «መንግስት ያለዉ የትነዉ?» እያሉ ነዉ ትግራይ ፈርሳለች።መተማ መዳራሻ ለሱዳን ገብራለች።ቋራ በቅማት ሸማቂዎች ታዉካለች።መተከል፣ ካማሺ፣ ወለጋ አስከሬን ይቀበር፣ ቁስለኛ ይቆጠር፣ ተፈናቃይ ይሰላባቸዋል።
ደቡብ ኢትዮጵያ- ጌድዮ፣ ሲዳማ፣ ቡርጂ፣ ጉጂ አካባቢ ስንጠራ፣ ዘር ዘንርዝረን አስከሬን ስንቆጥር፤ ተፈናቃይ ስናሰላ ሶስት ዓመት አስቆጥረን ዛሬም ጉራፈርዳ፣ አማሮ እንላለን።ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከሐማሬይሳ እስከ መተሐራ የተገደሉ፣ የተፈናቀሉ፣ የተዘረፉ በሚሊዮን ቆጥረን ነበር ዘንድሮም የአፋርና ኢሳ ዉጊያ የሚያረግፍ-የሚያፈናቅለዉን ኢትዮጵያዊ እንቆጥራለን።
ልጅ-ካዋቂ፣ ሴት-ከወንድ፣ በሽተኛ-ከጤነኛ፤ ሳይለይ በዘሩ ብቻ እየለዩ ሰዉን የመግደሉ ጭካኔ የኢትዮጵያዊያንን እዉቀት፣እድገት፣ሰብአዊነት፣ ኃይማኖተኝነትም እያጠያያቀ ነዉ።የካለን ኮሌጅ ዩናይትድ ስቴትስ ባልደረባ  ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ «ሜካናይዝድ» ይሉታል-ግድያዉን። ርፍረፋ።
በሕይወት የተረፉ ተፈናቃዮች፣ የርዳታ ድርጅቶችና ታዛቢዎች  «መንግስት የትነዉ?» ብለዉ ሲጠይቁ አጣዬም ጋየች።በርግጥት መንግስት አለ? ባይኖርስ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ ይሕን ያክል ጨካኝ ያደረገዉ ምን ይሆን? ፋሲል እጅጉ በኖርዌዉ የአርክቲክ ዩኒቨርስቲ መምሕር ናቸዉ።
ዛሬ ነበር ነዉ የሚባል።አርጎባዉ፣ አማራዉ፣ ኦሮሞዉ፣ ትንሽ ራቅ ቢልም አፋሩ «ሷሒብ» (ወዳጅ እንደማለት ነዉ) ዛሬ አንዱ ገዳይ ሌላዉ ሟች ነዉ።አንዱ ተሰዳጅ ሌለኛዉ አሳዳጅ ነዉ።
እና መንግስት አለ? 
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቀጥታ ተጠይቀዉ በቀጥታ የሰጡት መልስ መኖር አለመኖሩን አናዉቅም።በቀደም በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ግን አጣዬን ይሁን ወለጋን፣ ካማሺን ይሁን ገዋኔን፣ መተከልን እንደበል አማሮን የሚያበጣብጠዉ፣ የዘር መጥፎ ደዌ  የዛሬ 50 ዓመቱ ፖለቲካ ዉርስ ቅርስ  ነዉ።
ይሆን ይሆን? የቀድሞዉ የኢሕዴን መሪና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ ግን ዋና ተጠያቂ የሚያደርጉት መንግስትን ነዉ።
ግድያ፣ ጥፋት፣ ዉድመቱን ለማስቆም መንግስት  ሁነኛ እርምጃ አለመዉሰዱ ፕሮፌሰር መሐመድ እንደሚሉት «የከሸፈ» መንግስትነቱን ጠቋሚ ነዉ።አቶ ያሬድ ሁኔታዉን «አስፈሪ» ይሉታል።መንግስትን ደግሞ የግጭት ትርምሱ አካል ተብሎ የሚጠረጠር።ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለዉ የሚሰጉ እንዳሉ ሁሉ ሰጊዎችን «ሟርተኞች» እያሉ የሚያበሻቅጡ ብዙዎች ናቸዉ።ሰጊዎቹ ግን ኢትዮጵያ መፍረስ የጀመረችዉ ሰሜን ክፍለ ግዛትዋን ከነወደቦቹ በ1983 ስታጣ ነዉ ነዉ-ይላሉ።እነዚያኞቹ ለዚሕም መልስ አላቸዉ ግን ያዉ «ሟርተኞች» የሚል ዉግዘት ነዉ። ሐቅም ሆነ ሟርት የድሕረ-1983ቷ ኢትዮጵያ  ከከፋ ጥፋት ወይም ስጋተኞች  እንደሚሉት ከመፍረስ የምትድንበት ብልሐት ይኖር ይሆን? ረዳት ፕሮፌሰር ፋሲል እጅጉ መንግስት፣ በርግጥ  መንግስት መሆን አለበት ባይ ናቸዉ።
አቶ ያሬድ ጥበቡ የሳቸዉ ትዉልድ በ1960ዎቹ  የጮኸለትን ግን ያለቀበትን እንደ መፍትሔ ይጠቁማሉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በቀደም እንዳሉት ግን ከምርጫ ዉጪ ሌላዉን አማራጭ የሚቀበሉት አይመስሉም።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ የምርጫዉን አማራጭ «አማራጭ» አይሉትም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Weltspiegel 01.03.2021 | Äthiopien Tigray | Trauer um Toten
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed Parlament
ምስል Yohannes Gebireegziabher/DW

 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ