1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በህወሓት ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎች ልትመረምር ነው

ቅዳሜ፣ ጥር 22 2013

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ "በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህወሓት አመራሮች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመረምር ግብረ-ኃይል እንዲቋቋም ስላደረግን፤ ይኸ ግብረ-ኃይል ላለፉት 27 አመታት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ይኸ ቡድን የፈጸመውን ወንጀል የሚመረምርበት፣ የዘረፈውን ሐብት ለሀገር የሚያስመልስበት ሁኔታ እንዲኖር እንሰራለን" ብለዋል

https://p.dw.com/p/3ocDh
Logos TOLF  EPRDF

ኢትዮጵያ ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረባቸው አመታት ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን ልትመረምር መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ። 

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና የፌድራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ ለሶስት ወራት የተካሔደ የምርመራ ውጤትን አስመልክቶ ትናንት አርብ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ምርመራው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት የተደረጉ ዝግጅቶች እና በማይ ካድራ የተፈጸመውን "የጅምላ ጭፍጨፋ" ያካተተ ነው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥቃት ተፈጽሞ የትግራይ ክልል ከፌድራል መንግሥቱ ውጊያ ውስጥ ከመግባቱም በፊት ህወሓት መራሹ አስተዳደር በሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራ እና ስድስት ምክትል አዛዦች ያሉትን የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ ለማዋቀሩ በምርመራ እንደተደረሰበት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።  

"የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ ወይም ደግሞ መከላከያ ካውንስል ካቋቋመ በኋላ ስምንት ዕዞች ያሉት ስምንት ግምባሮችን ነው ለማደራጀት የሞከረው። በስምንት ግምባሮች 23 ሬጅመንቶች ያሏቸው አደረጃጀቶች ሰርተዋል። ይኸ ለልዩ ኃይሉ ብቻ ነው። ከመከላከያ የተመለሱ፣ ጡረተኛ የነበሩ የከዱ እነዚህን ብቻ የያዘ ነው። ሚሊሺያውን የያዘ አይደለም" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ አብራርተዋል።  

Karte - Äthiopien, Tigray - EN
በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ በርካቶችን በዚያው በክልሉ ሲያፈናቅሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወደ ሱዳን እንዲሰደሱ አስገድዷል

ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት 23 የካቢኔ አባላት መካከል 13 በተገኙበት እና ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሔደ ስብሰባ አቶ ፍቃዱ እንዳሉት "በየትኛውም ሰዓት ጦርነት ሊጀምሩ የሚችሉ መሆኑን ተሰብስበው" ለመወሰናቸው በምርመራው ማረጋገጫ ሰነድ ተገኝቷል። ይኸ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ከአስር ቀናት ገደማ በፊት መሆኑ ነው። 

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ እንዳሉት በኤፈርት ሥር የሚገኙ ድርጅቶች ምሽጎች በመቆፈር ተሳትፎ ማድረጋቸው በምርመራው ተረጋግጧል።  በትናንትናው መግለጫ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. "ተቀራራቢ በሚባል ሰዓት በመቶ ቦታዎች ጥቃት መፈጸሙን ምርመራችን አሳይቷል" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። 

በትግራይ መስተዳድር እና በፌድራል መንግሥቱ መካከል በይፋ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ስዩም መስፍን እና አባይ ጸሐዬን ጨምሮ የህወሓት ከፍተኛ ሹማምንት መገደላቸውን ጦሩ አስታውቋል። አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የፓርቲው መሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። 

የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ እንደተናገሩት 96 የህወሓት አመራሮችን ጨምሮ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 349 ተጠርጣሪዎች መካከል 124 በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ይኸ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌድራል ፖሊስ አባላት የነበሩ የጸጥታ አስከባሪዎችን ይጨምራል። 

ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ "በድምሩ 349 ተጠርጣሪዎች ከፌድራል ፖሊስም በተወሰነ ደረጃ ያሉበት፣ መከላከያም ያሉበት እና የፓርቲ እና የፖለቲካ ቁልፍ አመራሮች ያሉበትን መያዣ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ሥርዓት እና ሕጉን በተከተለ መንገድ በማውጣት የማደን ሥራ ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌድራል ፖሊስ ጋር በመሆን ሌሎች የጸጥታ አካሎችን በማሳተፍ ጭምር የማደን ሥራው ሲከናወን ቆይቷል። በዚህ መሠረት 124 ተጠርጣሪዎች እስካሁን በሔድንበት ርቀት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ሌሎች በተደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከጥቅም ውጪ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው" ሲሉ ተደምጠዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ እንዳሉት በህወሓት ተፈጽመዋል የተባሉ "ወንጀሎችን እና ጥፋቶችን" የሚመረምር ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል። ግብረ-ኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቱ ሲሆን ፌድራል ፖሊስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ያካተተ ነው። 
አቶ ፍቃዱ ጸጋ "በሒደት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህወሓት አመራሮች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመረምር ግብረ-ኃይል እንዲቋቋም ስላደረግን፤ ይኸ ግብረ-ኃይል ላለፉት 27 አመታት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ይኸ ቡድን የፈጸመውን ወንጀል የሚመረምርበት፣ ይኸ ቡድን የዘረፈውን ሐብት በተቻለ መጠን ለሀገር የሚያስመልስበት ሁኔታ እንዲኖር የመሥራት ሥራ እንሰራለን" ብለዋል። 
 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ