1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የተቃርኖዎች ቅይጥ ምድር

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሐምሌ 23 2010

የመሐንዲስ ስመኘዉ አሳዛኝ አሟሟት የቀሰቀሰዉ ቁጣ፤ ቁጭት እና ጥያቄ ከአዲስ አበባ ቤተ-ክርስቲያን እስከ ጎንደር አዉራ ጎዳናዎች፤ ከዋሽግተን አዳራሽ እስከ መቀሌ አደባባይ ተንፀባርቋል።ዋሽግተን ዉስጥ ደስታ፤ከቁጭት፤ ቁጣ ከበጎ ተስፋ ሲቀየጡ፤ መቀሌ ላይ ቁጣዉ የሥጋት ማድመቂያ መሆኑ ነዉ አነጋጋሪዉ።

https://p.dw.com/p/32LAk
Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

ኢትዮጵያ፤ ለዉጥ እና ፍንገጣ

ሐሙስ፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቤተ-ክርስትያን መሪዎች የ26 ዘመን ጠብ ክፍፍላቸዉን አስወግደዉ ዕረቀ-ሠላም ማዉረዳቸዉን ከትልቂቱ የዓለም ከተማ ዋሽግተን፤ለሕዝባቸዉ ለማብሰር ሲዘጋጁ፤ በተከበረዉ መስቀል ስም የተሰየመዉ የኢትዮጵያ ትልቅ አደባባይ የትልቅ ግድቧ ትልቅ መሐዲስ ደም ፈሰሰበት።ብስራት እና መርዶ።አርብን ዘለልነዉ።ቅዳሜ።ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊዉ የአዲሱን ጠቅላይ ሚንስር የሠላም፤ፍቅር ትብብር ድልድይን የመገንባት አዲስ መልዕክት ለመስማት ባንድ ሲታደም፤ መቀሌ ያለፉ መሪዎችዋ ያለፈ ዘመን መርሕ ተቀነቀነባት። ምስል ፎቷቸዉ ናኘባት።ሳምንቱም አበቃ።ኢትዮጵያ የብስራት-መርዶ፤ የአዲስ-አሮጌ፤ የአንድ-ብዙ ስብጥር ምድርነቷ ማነጋገሩ ግን ቀጠለ።                                         

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በተገኙበት በዋሽግተኑ ስብሰባ የኢትዮጵያን ዉበት፤የሕዝቧን አንድነት፤ የመተባበሩን አስፈላጊነት በግጥሟ ያወደሰችዉ አንጋፋዋ ከያኒ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ እንደምትለዉ ያለፈዉ 27 ዓመት ኢትዮጵያ እንደ ሐገር እሷም እንደ ዜጋ ዝቅ-ያሉ፤ የወረዱ እና የተበደሉበት ዘመን ነበር።የዚያ ዘመን ፍፃሜ ብስራት፤የአዲስ ዘመን ብርቀት ጭላንጭል  ሲታይ አለመደገፍ በአንጋፋዋ የኪነት ሰዉ እምነት የጤና አይሆንም።

                           

Äthiopien Addis Abeba Simegnew Bekele tot aufgefunden
ምስል Reuters/T. Negeri

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ ለዉጥ ለዓለም ፀሐይ የ«ሕይወት ዘመን ጥሪ ሰሚ አገኘ» ዓይነት ነዉ።የኒዮርኩ ኢዮና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፈሰር ደረሰ ገበየሁ በበኩላቸዉ የለዉጡ መሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ  የወሰዱት እርምጃ እና የሚገቡት ቃል ኢትዮጵያዉያንን ቢያስደስት አይደንቅም።                                             

አዲስ አበባ እና ዋሽግተን ላይ ሁለት ሲኖዶስ መሥርተዉ ለ27 ዘመናት ሲወጋገዙ የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ታርቀዋል።ጠቅላይ ሚንስትር አዐብይ አሕመድ የግንቦት ሰባትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ባደረጉት ዉይይት፤ በዉይይቱ የተሳተፉ እንዳሉት፤ በሠላም ለመስራት ተስማምተዋል።

የኃይማኖት መሪዎቹ እርቅ እና  የፖለቲከኞቹ ሥምምነት፤ የዶክተር ዐብይ የልዩነትን ግንብ የማፍረስ ወይም የመደመር መርሕ ባለፈዉ ሳምንት ዋሽግተን ላይ ገቢር ለመሆኑ አብነቶች ናቸዉ።የልዩነት ግንብ የመፍረሱ አብነት ዋሽግተን ላይ ደምቆ-ሲፈካ አዲስ አበባ ሐዘን እንዳረበባት፤ ቀቢፀ-ተስፋ እንዳጠላባት ነበር።

  የኢትዮጵያ ምናልባት የአፍሪቃ ግዙፍ ግድብ ዋና ሥራ-አስኪያጅ መሐንዲስ ስመኘዉ በቀለ መደመር ሲሰበክ ተቀነሱ።ለምን? የብዙ ሚሊዮኖች ጥያቄ።ላሁኑ ከሐዘን፤ እልሕ ቁጣ፤ጥርጣሬ  ባለፍ መልስ የለም።                     

የመሐንዲስ ስመኘዉ አሳዛኝ አሟሟት የቀሰቀሰዉ ቁጣ፤ ቁጭት እና ጥያቄ ከአዲስ አበባ ቤተ-ክርስቲያን እስከ ጎንደር አዉራ ጎዳናዎች፤ ከዋሽግተን አዳራሽ እስከ መቀሌ አደባባይ ተንፀባርቋል።ዋሽግተን ዉስጥ ደስታ፤ከቁጭት፤ ቁጣ ከበጎ ተስፋ ሲቀየጡ፤ መቀሌ ላይ ቁጣዉ የሥጋት ማድመቂያ መሆኑ ነዉ አነጋጋሪዉ።

የመቀሌ ሕዝብ ባለፈዉ ቅዳሜ አደባባይ የወጣዉ፤ የሰልፉ አዘጋጆች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠላም ለማዉረድ ያደረጉትን ሥምምነት ለመደገፍ ነዉ።

እርግጥ ነዉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር  ዐብይ አሕመድ እና የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ሠላም ለማዉረድ በመወሰናቸዉ አመስግነዋቸዋል።

ምክትል ርዕሠ-መስተዳድሩም ሆኑ ሌላዉ ሠልፈኛ  በለበሷቸዉ ቲሸርቶች ወይም ባርኔጣዎች ላይ የተለጠፉት ፎቶዎች ግን  ሠላም ያወረዱት ሳይሆን ጦርነት ያዋጉት መሪዎች ነዉ።ምክትል ርዕሠ-መስተዳድሩ ሁለቱን መሪዎች ባመሰገኑበት ንግግራቸዉ ከተስፋ ይልቅ ሥጋት እና አደጋ መኖሩን ተናግረዋል።

Äthiopien | Presskonferen der Orthodoxen Kirche
ምስል G. Tedla HG

                            

የፎቶ እና የንግግሩ መልዕክት ለሩቁ ታዛቢ ግራ አጋቢ ነዉ። ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፀሐፍት ደግሞ የትችት፤ወቀሳ ምክንያት ነዉ የሆነዉ።ረዳት ፕሮፌሰር ደረሰ ገበየሁ እንደሚሉት ደግሞ የመሐንዲስ ስመኘዉሞት እና የመቀሌዉ ሰልፍ መልዕክት ሳይመሳሰል አይቀርም።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚብሔር  ግን በተለይ በመቀሌዉ ሠልፍ እና ንግግር ላይ የሚሰነዘረዉን ወቀሳ እና ትችት አይቀበለዉም።መታየት ያለበት፤ ዮሐንስ እንደሚለዉ፤  የሰልፉ ዓላማ ነዉ።                          

በቅዳሜዉ ሠልፍም በሆነ በአዘቦቱ እንቅስቃሴ በሌላዉ የኢትዮጵያ ክፍል የሚታየዉ ዓይነት የለዉጥ ጉጉት፤የመተባበር፤ የሰላም እና የዴሞክራሲ ተስፋ ትግራይ ዉስጥ ብዙም አይታይም።ረዳት ፕሮፌሰር ደረሰ ገበየሁ ለትግራይ ልሒቃን አጭር መልዕክት አላቸዉ።አንጋፋዋ ከያኒ ዐለም ፀሐይ ወዳጆ፤ የአዲስ አበባዉ ዓይነት ግድያ፤የመቀሌዉ ፍንገጣ፤ ሥጋት፤ዉዝግብን የሽግግር ወቅት ክስተት ትለዋለች።

ረዳት ፕሮፌሰር ደረሰም  ይስማማሉ።ብቻ ሳምንቱ አለፈ።የተስፋ-ቀቢፀ ተስፋ፤ የመርዶ-ብስራቱ ቅይጥ፤ የሥጋት-መረጋጋቱö የመተባበር-ማፈንገጡ ዝንቅ የሚያልፍበት ጊዜ አለመቃረቡ ነዉ እዉነቱ።   

Äthiopien Beerdigung von Semegnew Bekele in Addis Abeba
ምስል DW/G. T. Hailegiorgis

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ