1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ ለመኪና አምራቾች ፖሊሲ ያስፈልጋታል- የፎልክስቫገን ኃላፊ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 2011

የጀርመኑ ፎልክስቫገን የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ከለያቸው አራት ቁልፍ ገበያዎች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ከጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ጋር የመከሩ ከፍተኛ የኩባንያው ኃላፊ እንደሚሉት ግን ከ10 አመታት በላይ ያገለገሉ መኪኖች እንዲገቡ የምትፈቅደው አገር አምራቾችን የሚደግፍ ፖሊሲ ያስፈልጋታል።

https://p.dw.com/p/377nC
Äthiopischer Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Fistum Arega

ፎልክስቫገን በኢትዮጵያ ገበያ ላይ አይኑን ጥሏል

ባለፈው ጥቅምት ሰባት ቀን፣ 2011 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ያሉት ጀርመናዊው ቶማስ ሼፈር ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የፎልክስቫገን ኩባንያ ወደ አገሪቱ እንዲገባ ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረባቸው አስተውለዋል። የፎክልስቫገን ደቡብ አፍሪቃ ሊቀ-መንበር እና ኩባንያው ከሰሐራ በረሐ በታች ለሚገኙ አገሮች ያቋቋመው ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ቶማስ ሼፈር "ጠቅላይ ምኒስትሩ እጅግ ግልጽ ነበሩ። ስለ ጉዳዩም በቂ መረጃ ያላቸው ይመስላል። ይኸ መልካም ነው። አቀባበላቸው ጥሩ፣ ለመደግፍም ዝግጁ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ትክክለኛ ጥያቄዎች ሲጠይቁ ነበር። ተነሳሽነታቸው እጅግ ከፍ ያለነበር። በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሥራ እንግባ እያሉ ሲወተውቱን ነበር። አሁን ዕቅዱ ካለበት ደረጃ አኳያ ትንሽ ፈጠን ብለዋል። ነገር ግን ተነሳሽነታቸውን ወድጄዋለሁ። ትክክለኛው መንፈስ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ ከቶማስ ሼፈር እና የሥራ ባልደረባቸው ጋር የነበራቸውን ቆይታ አንስተው ነበር። ጠቅላይ ምኒስትሩ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ችላ ብሎ ወደ ርዋንዳ ያቀናው በቀረበለት መስተንግዶ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከኩባንያው ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ፎልክስቫገን በኢትዮጵያ የመኪና ፋብሪካ ለመገንባት ውጥን እንዳለው መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ፎልክስቫገን ወደ አፍሪቃ ገበያ ከገባ ረዥም አመታትን አስቆጥሯል። የደቡብ አፍሪካው ቢሮ ከተከፈተ 58 አመታት ማስቆጠሩን የሚናገሩት ቶማስ ሼፈር በገበያው ያለው ድርሻም ስኬታማ እንደሆነ ያስረዳሉ። ኩባንያው በአህጉሪቱ ለመስፋፋት ሲወጥን  ከለያቸው አራት ቁልፍ ገበያዎች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ቶማስ ሼፈር "በጥሩ ሁኔታ ሊያድጉ ይችላሉ ፣ ወደፊት የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪ ምናልባት ያስፈልጋቸዋል ብለን የገመትናቸውን ገበያዎች ከሁለት አመታት በፊት አጠናን። በዚህ ረገድ በበርካታ ምክንያቶች ከለየናቸው አራት ቁልፍ ገበያዎች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች። አንደኛው አገሪቱ ከአፍሪቃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የሕዝብ ቁጥር የሚገኝባት መሆኗ ነው። መንግሥቱም ቢሆን ወደ ፊት አርቆ የሚያስብ ነው። የባቡር አገልግሎት በመጀመሩ የማጓጓዣ ሥራ እየተቃለለ ይገኛል። ስለዚህ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ወደፊት እየመጡ ካሉት አገሮች መካከል ናት ብለን እንድናምን ያደረጉን በርካታ ምክንያቶች አግኝተናል" ሲሉ ኩባንያቸው ወደ ኢትዮጵያ ካመራበት ውሳኔ ያደረሰውን ገፊ ምክንያት ያስረዳሉ።

Logos AUDI, Volkswagen, BMW, Mercedes Benz und Porsche
ምስል picture-alliance/U. Baumgarten

ሥመ-ጥሩ የጀርመን መኪና አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ አይኑን መጣሉ የታወቀው የጀርመን የልማት ትብብር ምኒስትር ጌርድ ሙለር ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት ነበር። ምኒስትሩ ከቀድሞው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እና የኤኮኖሚ ትብብር ምኒስትር ዶ/ር አብርሐም ተከስተ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ "ፎልክስቫገን በቅርቡ በኢትዮጵያ መኪና መገጣጠም ይጀምራል" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የፖሊሲ ነገር

በኢትዮጵያ ገበያ አይኑን ለጣለው ፎልክስቫገን ግን አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ከፊቱ ተደቅኗል። በአገሪቱ ገበያ ያገለገሉ መኪኖች መብዛታቸውን የታዘቡት ቶማስ ሼፈር በኢትዮጵያ የተመረቱ መኪኖችን የሚደግፍ ፖሊሲ አለመኖሩ ወደፊት ለሚጀምሩት ሥራ ዋነኛ ፈተና እንደሚሆን ተረድተዋል። ኃላፊው የኢትዮጵያን የመኪና ገበያ "የዓለም አቀፍ የመኪና አምራቾችን ቀልብ መግዛት የማይችል እጅግ አነስተኛ" ሲሉ ይገልጹታል።  "ይኸ የሆነው ግን ኢትዮጵያውያን አዲስ መኪና ሳይፈልጉ ቀርተው አይደለም። ችግሩ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚመረቱ መኪኖችን የሚደግፍ ፖሊሲ የለም። በአብዛኛው በኢትዮጵያ ገበያ የሚሸጡ መኪኖች ከመካከለኛው ምሥራቅ፤ ከአሜሪካ ወይም ከአውሮጳ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው። እነዚህ መኪኖች በኢትዮጵያ የተመረቱ አይደሉም። በአገሪቱ የሚፈጠር እሴት የለም" ሲሉ የገበያውን ኹኔታ ይገልጹታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካባቢ ጥበቃ መርሐ-ግብር (UNEP) በቅርቡ ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ጎዳናዎች የሚሽከረከሩ መኪኖች ቁጥር በየአመቱ በ10 ከመቶ ጭማሪ ያሳያል። በዚሁ ዘገባ መሠረት እስከ 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች መካከል 80 ከመቶው ከውጭ የተሸመቱ ናቸው። ኢትዮጵያ ከ10 አመታት በላይ ያገለገሉ መኪኖች በገበያቸው እንዲሸጡ ከሚፈቅዱ 24 አገሮች መካከል አንዷ ነች። በዚህ ጎራ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን የመሳሰሉ አገሮች ይገኛሉ።

ቶማስ ሼፈር እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያ ያገለገሉትን ከመሸመት ይልቅ በአገር ውስጥ የሚያመርቱትን ልታበረታታ ይገባል። ገበያውን ቀረብ ብለው በማጥናት ላይ የሚገኙት ሼፈር "ኢትዮጵያ ለሥራ ፈጠራ የሚያግዛት፣ ለወጣቶች ትምህርት እና ሥልጠና የሚያቀርብ የአውቶሞቲቭ ኢንደስትሪ ከፈለገች ዘርፉን የሚደግፍ ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል። ደቡብ አፍሪቃ ከ600 እስከ 700 ሺሕ መኪኖች በአመት ታመርታለች። ከውጭ የሚገባው ያገለገለ መኪና መጠን በደቡብ አፍሪካ ዜሮ ነው።  ምክንያቱም አያስፈልግም። በአገሪቱ ገበያ የሚሸጡ መኪኖች እዚያው የተመረቱ አሊያም ከውጭ አስፈላጊው ግብር ተከፍሎባቸው የገቡ ግን ደግሞ አዲስ ናቸው። ስለዚህ ምንም አይነት የመዋዕለ ንዋይ ሥራ ከመጀመራችን በፊት የተወሰኑ መሠረታዊ ጉዳዮች መልስ ሊሰጣቸው ይገባል" የሚል አቋም አላቸው። ይኸው የፖሊሲ ጉዳይ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ከፎልክስቫገን ኩባንያ ተወካዮች ጋር በፅህፈት ቤታቸው ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኝበት ሼፈር ተናግረዋል።

Bildergalerie VW Käfer in Äthiopien
ምስል Reuters/T. Nigeri

ፎልክስቫገን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገባ የሚሰማራባቸውን አራት የሥራ ማዕቀፎች ለይቷል። ሼፈር "የመጀመሪያው ማዕቀፍ የመኪና መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ይሆናል። ሁለተኛው የኢትዮጵያ መንግሥት የአቅራቢዎችን ቀልብ ለመሳብ ፍላጎት አለው። እነዚህ ኩባንያዎች ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ይፈልጋል። በዚህም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎቱ አለን። ይኸ ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ጋር ተመሳሳይ ነው። በጥሩ ዕቅድ የሆነ ቦታ ይጀመራል ከዚያ ቀስ በቀስ ያድጋል። እኛ በአቅርቦቱ በኩል እየረዳናቸው ነው። ሶስተኛው የስልጠና እና የትምህርት ማዕቀፍ ነው። ጀርመን በቴክኒክ እና ሙያዊ ሥልጠና እጅግ ጥሩ ልምድ አላት። መንግሥትም በዚህ ለመተባበር እጅግ ፈቃደኛ ነው። በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የሰለጠነ እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል የሥራ ኃይል መፍጠር ማለት ነው። አራተኛው ሰዎች መኪኖች ሊከራዩ የሚችሉባቸው ዘመናዊ አገልግሎቶች ማቅረብ ይሆናል" ሲሉ የኩባንያቸውን ውጥን አብራርተዋል።  ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚኖረው መዋዕለ-ንዋይ መቼ፣ የት እና እንዴት እንደሚጀመር የሚወስነውን ሰነድ እያዘጋጀ ሲሆን ፣ ሼፈር እንዳሉት በዚህ አመት መጨረሻ ተጠናቆ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ መኪና የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ቁጥር ሲጨምር ቢታይም ከገበያው ፍላጎት አኳያ አሁንም በቂ አይመስልም። ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጋር የተወያዩት ሼፈር "እንደ ርዋንዳ እና ኬንያ ባሉ አገሮች አስቀድመን ሥራ የጀመርንበት ምክንያት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን የሚሹ መሪዎች በመኖራቸው ነው። የመኪና አምራች ኢንድስትሪውን ቀልብ መሳብ ለአገሮቻቸው ምጣኔ ሐብት እና ለሥራ ፈጣራ አስፈላጊ መሆኑን ተረድተውታል። ለዚያም ነው ደቡብ አፍሪቃ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮጳ ዘርፉን ለበርካታ አመታት ሲደግፉ የቆዩት። በደቡብ አፍሪቃ የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪው ከአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን 8 በመቶ ድርሻ አለው" ሲሉ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም "ጠቅላይ ምኒስትሩ ተረድተዋል፤ በውይይታችን ግልፅ እና ለመደገፍ ዝግጁ ነበሩ። ስለ ዕቅዳችን እና እንዴት አብረን መስራት እንዳለብን ነግረናቸዋል። እርሳቸውም ደግፈውታል። በየጊዜው ሥራችን ስለደረሰበት ደረጃ እንድናሳውቃቸው ጠይቀዋል" ሲሉ ስለ ውይይታቸው ቶማስ ሼፈር ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ