1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢሮብ አሁንም በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ስር ነዉ-ነዋሪዎች

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

በተለይም ወጣቶች ከአካባቢው እየታፈኑ ወደ ኤርትራ እንደሚወሰዱ በቅርቡ በኤርትራ ቁጥጥር ስር ካለው አከባቢ ወጥተው የመጡት አቶ ሐጎስ ጠቁመዋል። "25 ወጣቶች ታፍነው ተወስደዋል። አንዴ ሰንዓፈ ናቸው፣ ሌላ ግዜ አስመራ ታስረው ይገኛሉ ይባላል። እስካሁን ግን ስላሉበት ሁኔታ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4PYnZ
Irob, East Tigray, Äthiopien
ምስል Million Haileslassie/DW

ኢሮብ፤ ሰብአዊ ርዳታ፣ሕክምና፣ስልክና መብራት የለም-ነዋሪዎች

የኤርትራ ጦር ይቆጣጠራቸዋል በሚባሉት በምስራቅ ትግራይ በተለይም በኢሮብ ወረዳ በሁለት ዓመቱ ጦርነት ለተጎዳዉ ሕዝብ እስካሁን ሰብአዊ ርዳታ አለመድረሱን የወረዳዉ ነዋሪዎች አስታወቁ።የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ አምሰተኛ ወሩ ተገባድዷል።ይሁንና  ነዋሪዎችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደሚሉት በኢሮብ ወረዳ  በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ የሕክምና፣የስልክና  የመብራት መሰረታዊ አገልግሎቶች አልተጀመሩምም።

የሰላም ስምምነቱ ተፈርሞ ጦርነቱ ከቆመ አምስት ወራት ቢያልፉም፣ የኤርትራ ጦር ዘልቆ ገባባቸው የተባሉ የኢሮብ ወረዳ አካባቢዎች አሁንም ተቆጣጥሯቸው እንዳለ፣ በአካባቢው የሚገኝ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ ይሁን የተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶች ማግኘት እንዳልቻለ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ገልፀዋል። ያነጋገርናቸው ከኢሮብ ወረዳ ረዥም ርቀት በእግራቸው ተጉዘው የስልክ አገልግሎት ወዳለበት ዓዲግራት የመጡ የብሄረሰቡ ተወላጆች እንደሚሉት፣ የኤርትራ ጦር ተቆጣጥሯቸው ባሉ የኢሮብ ወረዳ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ግፍ ይፈፀማል፣ ረሀብ ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራዊ ቀውሶች ተከስተዋል። አካባቢው ከሁለት ዓመታ በላይ ለሚሆን ግዜ በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ስር ስለመሆኑ የነገሩን በቅርቡ ከኢሮብ ወረዳ እንዳልጌዳ አካባቢ ተነስተው በእግር ዓዲግራት መድረሳቸው የነገሩን የብሄረሰቡ ተወላጅ አቶ ሐጎስ ተስፋይ፣ ቀድሞ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት የነበሩ አሁን የኤርትራ ጦር ተቆጣጥሯቸው ባለው የኢሮብ ወረዳ አካባቢዎች ከሰላም ስምምነቱ በኃላም ቢሆን በረሃብና ሕክምና እጦት ምክንያት በርካታ ዜጎች እየሞቱ መሆኑ ይገልፃሉ። "ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ኢሮብ ወረዳ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ስለሆነ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ብቻ ሳይሆን ከዛ በፊትም ቢሆን እርዳታ አልደረሰም" ብለዋል።

ሌላዋ ያነጋገርናት የብሄረሰቡ ተወላጅ እና በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅላ አሁን ላይ ዓዲግራት ያለችው ልዋም አስፍሃ፥ ወደ ኢሮብ አካባቢ የሚገባ ሰብአዊ እርዳታ እንደሌለ፣ ስልክ ይሁን ሌላ የግንኙነት መስመር እንዲሁም ትራንስፖርት አለመኖሩ አረጋግጣልናለች። እንደ ያነጋገርናቸው አቶ ሐጎስ ተስፋይ ገለፃ "ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት በኢሮብ የሚኖር ህዝብ የመጥፋት አደጋ ላይ ነው" ይላሉ። 

ከኢሮብ አካባቢዎች አንዱ
ከኢሮብ አካባቢዎች አንዱምስል Million Haileslassie/DW

ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እጦት እና መሰረታዊ አገልግሎቶች መዘጋት በተጨማሪ፣ በተለይም ወጣቶች ከአካባቢው እየታፈኑ ወደ ኤርትራ እንደሚወሰዱ በቅርቡ በኤርትራ ቁጥጥር ስር ካለው አከባቢ ወጥተው የመጡት አቶ ሐጎስ ጠቁመዋል። "25 ወጣቶች ታፍነው ተወስደዋል። አንዴ ሰንዓፈ ናቸው፣ ሌላ ግዜ አስመራ ታስረው ይገኛሉ ይባላል። እስካሁን ግን ስላሉበት ሁኔታ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም" ብለዋል።

በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ በአጠቃላይ የኤርትራ ጦር በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች፥ በተለይም ደግሞ በኢሮብ እና አካባቢው በዜጎች ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደሚፈፀም ማረጋገጡ ለዶቼቬለ ገልጿል። የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱ ሉአላዊነት የማስከበር ስራው አልከወነም ብለው ወቅሰዋል። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ በቅርቡ ከተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ሰጥተውት በነበረ መግለጫ፣ አስተዳደራቸው በውጭ ሃይሎች የተያዙ ግዛቶች ማስመለስ እና የትግራይ ግዛታዊ አንድነት የማረጋገጥ ስራ ቀዳሚ አጀንዳው እንደሚያደርግ ጠቁመው ነበር።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር