1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢራን አሜሪካን ለመበቀል የሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤን ዒላማ ታደርግ ይሆን?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 29 2012

ኢራን የሜጀር ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒ ግድያ ለመበቀል በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች የተለጠለሉባቸውን ሁለት የጦር ሰፈሮች ደብድባለች። ሁለቱ አገሮች የገቡበት መካረር ተባብሶ መርከቦች የሚተላለፉበት የሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤን ዒላማ እንዳይሆን ተንታኞች ሥጋት አላቸው።

https://p.dw.com/p/3Vtd4
Iran | Britischer Tanker Stena Impero
ምስል picture-alliance/Photoshot/ISNA/M. Akhoundi

ውጥረቱ በነዳጅ ዘይት ግብይት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል

አሜሪካ ሜጀር ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒ ከገደለች በኋላ በተቀሰቀሰው ውጥረት ዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያዎች መረጋጋት ተሳናቸው፤ የወርቅ ዋጋ አሻቀበ፤ የአንድ በርሜል የነዳጅ ዘይት ዋጋ 70  ዶላር ደረሰ። ባለፈው መስከረም የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ በኢራን ይደገፋሉ በሚባሉት ሑቲዎች ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ዋጋው ከዚህ ሲደርስ የመጀመሪያ ነው። ኢራን የሜጀር ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒ ግድያን ለመበቀል በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያዎች ላይ ሌላ ጥቃት ልትፈፅም እንደምትችል አሜሪካ አስጠንቅቃለች።

አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባ የጦር ጄኔራሉን ከገደለች በኋላ በዓለም ገበያ የነዳጅ ግብይት መረጋጋት ተስኖታል። ለምሳሌ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው በአምስት በመቶ ገደማ ጨምሯል። አይኤችኤስ ማርኪት በተባለው ኩባንያ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተንታኝ የሆኑት ኤግ ሴኪን እና የተቋሙ ዳይሬክተር ፊራዝ ሞዳድ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው "በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ የኃይል መሠረተ-ልማቶች፤ የነዳጅ ማጣሪያዎች የባሕር ትራንስፖርት እና የአየር መጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ በሑቲዎች አማካኝነት ኢራን ጥቃት ልትፈፅም ትችላለች" ሲሉ ሥጋታቸውን በኢሜይል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ባለያዎቹ እንደሚሉት ኢራን ለጥቃቶቹ ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች እና የጦር መሳሪያ የተገጠመላቸው ሰው አልባ በራሪ ተሽከርካሪዎች ልትጠቀም ትችላለች። ሁለቱም ግን እንዲህ አይነት የኢራን የበቀል እርምጃ ቀጠናውን ወደ ከፋ ቀውስ ሊያመራው እንደሚችል ያሰጋቸዋል።

Karte VAE Straße von Hormus EN

"ባለፈው ግንቦት እና መስከረም 2019 ዓ.ም. ከተፈጸሙት ጥቃቶች ይልቅ አሜሪካ እንዲህ አይነት ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ መኮንን ለመግደል መቁረጧ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ለኢራን የበቀል እርምጃ ምላሽ እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል" ይላሉ ባለሙያዎቹ። 

የኢራን የበቀል እርምጃ በሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሊያነጣጥር ይችላል የሚል ሥጋት አለ። በፐርሺያ እና ኦማን ወሽመጥ መካከል የሚገኘው የሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤ በዓለም የነዳጅ ዘይት ግብይት ቁልፍ ቦታ ያለው መተላለፊያ ነው።

ከዚህ ቀደም ኢራን ለዓለም ገበያ ነዳጅ ከሚያመላልሱ መርከቦች አንድ አምስተኛው የሚያልፉበትን ይኸንንው ባህረ ሰላጤ ልትዘጋ እንደምትችል አስፈራርታ ታውቃለች። ተንታኞች አገሪቱ መተላለፊያውን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ለመቻሏ ችርጣሬ ቢኖራቸውም ከዚህ ቀደም እንዳደረገችው ሁሉ በባህረ ሰላጤው በሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደምትችል ስለሚያውቁ ይሰጋሉ።

ባለፈው ሰኔ በዚያው በሖርሙዝ ባህረ ሰላጤ አቅራቢያ በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች አሜሪካ ኢራንን ወንጅላ ነበር። ኢራን ግን በመርከቦቹ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እጇ እንደሌለበት ገልጻ የአሜሪካንን ክስ አስተባብላለች። ከወር በኋላ በሐምሌ ኢራን ስቴና ኢምፔሮ የተባለ የብሪታኒያ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ መርከብ በቁጥጥሯ ሥር አዋለች። የተሒራን እርምጃ ብሪታኒያ የኢራንን መርከብ በቁጥጥር ሥር በማዋሏ የመልስ ምት ነበር።

ለግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች የጥበቃ አገልግሎት የሚያቀርበው ዲያፕሎስ የተባለ ኩባንያ ዋና የንግድ ሥራ ኃላፊ ዲሚትሪስ ማኒያቲስ "የመርከብ ንግድ ሥራ ኢንዱስትሪው እጅግ ሥጋት ገብቶታል። የጸጥታ ጥበቃ ሰራተኞች ምን ሊመጣ ይችል ይሆን የሚል ፍራቻቸው የሚንጸባረቅበት ማለቂያ የሌለው ውይይት በኩባንያዎቹ እየተደረገ ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

ይሁንና ማኒያቲስ ኢራናውያን በእልህ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ የሚል ሥጋት የላቸውም። "ሊያደርጉት የሚችሉት አስከፊ ነገር ከዚህ ቀደም ስቴና ኢምፔርኖ ላይ እንደሆነው መርከቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ሊሆን ይችላል" ብለዋል

ኢራን የሖርሙዝ ባህረ ሰላጤን ለመዝጋት አሊያም በባሕረ ሰላጤው የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን ለማስተጓጎል የምታደርገው ጥረት በዓለም የነዳጅ ዘይት ግብይት ላይ የከፋ ተፅዕኖ ያሳድራል። ምክንያቱም ለነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከሖርሙዝ ባህረ ሰላጤ የተሻለ መተላለፊያ የለም።

በአሜሪካ የኃይል መረጃ አስተዳደር ባለሥልጣን መሰረት ከሖርሙዝ ባህረ ሰላጤ ውጪ ድፍድፍ ነዳጅ ለማስተላለፍ የሚያስችል ቧምቧ ያላቸው የቀጠናው አገራት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ብቻ ናቸው። ይሁንና የሁለቱ አገሮች የቧምቧ ማስተላለፊያዎች በቀን ማጓዝ የሚችሉት 6.8 ሚሊዮን በርሜል ብቻ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ.ም. በሖርሙዝ ባህረ ሰላጤ በቀን 17.3 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ተጓጉዟል።

ከዚህ መካከል 80 በመቶው ድፍድፍ ነዳጅ ቻይና፣ ሕንድ እና ጃፓንን ለመሳሰሉ የእስያ ገበያዎች የሚቀርብ ነው። በአመቱ 1.4  ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በዚሁ በሖርሙዝ ሰርጥ በኩል የሸመተችው አሜሪካ በኢራን እርምጃ የሚፈጠረው ምስቅልቅል ይኸን ያክል ተፅዕኖ የሚያሳድርባት አይመስልም።

Iran Revolutionsgarden in Teheran
ምስል Getty Images/AFP

ነገር ግን ኢራን የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ በአሜሪካ ጦር የወታደራዊ የባሕር ማጓጓዣ አገልግሎት የሚሰሩ ኮንቴነር ጫኝ መርከቦች ላይ ልታነጣጥር ትችላለች። እንዲህ አይነት መርከቦች የሖርሙዝ ባህረ ሰላጤን በማቋረጥ ወደ ፐርሺያ ወሽመጥ አዘውትረው ይጓዛሉ።

"የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ ወይም ለአሜሪካ ጥቅም የሚሰሩ መርከቦች ከሌሎቹ ከፍ ባለ ደረጃ የየትኛውም የበቀል እርምጃ ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን የለየናቸው ናቸው" ይላሉ ማኒያቲስ። "በርካቶች የማርሻል ደሴቶች ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ መርከቦች አገሪቱ ወደ አሜሪካ ያጋደለች ነች ተብሎ ስለሚታሰብ የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሥጋታቸው ይገልጻሉ" ሲሉ አክለዋል።

በርካታ ተንታኞች በዓለም ገበያ የፍላጎት መቀዛቀዝ እና የፔትሮሊየም ላኪ አገራት ኅብረት (OPEC) አባል ያልሆኑ አገሮች የምርቶቻቸውን መጠን ሊጨምሩ ስለሚችሉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ አሁን ካለው ሊቀንስ ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

ስቴዋርት ግሊክማን የተባሉ የኃይል ጥናት እና ትንተና ባለሙያ "አሁን ባለው ውጥረት ሳቢያ የሚታይ የዋጋ ጭማሪ ዓላፊ ነው የሚል ግምት አለን" ሲሉ ይናገራሉ። ተንታኙ "በእርግጥ የመስፋት ዕድል ያለው ውጥረቱ የፔትሮሊየም ላኪ አገራት ኅብረት (OPEC) አባል ባልሆኑ እንደ ብራዚል፣ ጉያና ወይም በሰሜን ባህር ያሉ አገሮች የምርት መጠን እንዲቀንስ አላደረገም። በእኛ አተያይ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ያለውን የገበያ ፍላጎትም አልቀነሰውም" ብለዋል።

አሹቶሽ ፓንዴይ/እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ