1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢህአዴግ የማንነት ጥያቄዎች በህግ አግባብ እንዲፈቱ አደርጋለሁ አለ

ዓርብ፣ መስከረም 25 2011

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) “የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ የማንነት ጥያቄዎችም በህግ አግባብ እንዲፈቱ” አቋም ላይ መድረሱን አስታወቀ። ገዢው ፓርቲ ይህን ያስታወቀው ከረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ ም ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ ሲያጠቃልል ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው። 

https://p.dw.com/p/364NW
Äthiopien Anhänger der Partei EPRDF
ምስል Imago/Xinhua Afrika

ኢህአዴግ የማንነት ጥያቄዎች በህግ አግባብ እንዲፈቱ አደርጋለሁ አለ

በኢትዮጵያ የተዘረጋው ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓት “የኢትዮጵያን አንድነት ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ” በኢህአዴግ የአቋም መግለጫ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ “የፌደራል ስርዓት ግንባታው ጅምር ላይ እንደመሆኑ መጠን የወሰን አከላለሎች፣ ማንንነትን መነሻ ያደረጉ ጥያቄዎች፣ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብቶች ሲጣሱ” እንደሚስተዋሉም ጠቁሟል። ይህ እንዲቆም ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ የአዴፓው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በንባብ አሰምተዋል።

“እነዚህ ችግሮች ከስረ-መሰረታቸው መነቀል የሚገባቸው ችግሮች በመሆናቸው የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች፣ የሚመለከታቸው ህዝቦች ነጻ ፍላጎትን ከግምት ውስጥ ባስገባ፣ በህገ መንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ የዜጎች የትም ቦታ ተዘወውሮ የመኖር፣ የመስራት፣ በቋንቋቸው የመማር እና የመዳኘት፣ ወግ እና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን ዕውቅና እና ውክልና የማግኘት መብት፣ ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸውን እንዲከበሩ እንዲሁም ብሔራዊ ማንነት እና ሀገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲከበሩ አበክረን እንሰራለን” ሲል ኢህአዴግ በአቋም መግለጫው አስታውቋል።

ኢህአዴግ በጉባኤው ማጠቃለያ የአቋም መግለጫውን ይፋ ከማድረጉ በፊት የሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ አከናውኗል። በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሊቀመንበርነት አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት ኢህአዴግን እንዲመሩ በድጋሚ ተመርጠዋል።

የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር የሚመረጠው 180 አባላት ባሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው። በምስጢር በሚሰጠው ድምጽ አሰጣጥ ሦስት አባላት አለመሳተፋቸው ታውቋል። ምርጫውን በሰብሳቢነት ያስፈጸሙት አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ “አጠቃላይ ድምጽ የሰጠው 177 ሰው ነው። ለሊቀመንበርነት ድምጽ ከተሰጠው 177 ድምጽ ውስጥ 176 ለዶ ር አብይ አህመድ ሰጥቷል። ለሊቀመንበርነት አቶ ደመቀ አንድ ድምጽ አግኝተዋል። ምክትል ሊቀመንበርን በተመለከተ ከ177 ውስጥ ለአቶ ደመቀ መኮንን 149፣ ለዶ/ር ደብረጺዮን 15 ተሰጥቷል” በማለት ውጤቱን ሲያሳውቁ የጉባኤው ተሳታፊዎች ደማቅ ጭብጨባ አጅቧቸዋል።

ከሰባት ወር የኢህአዴግ መሪነት በኋላ በድጋሚ በሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገዢውን ፓርቲ እስከሚቀጥለው ጉባኤ እየመሩ ይቆያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደመሪነት ስልጣን የመጡት ከእርሳቸው በፊት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመናቸውን ሳይጨርሱ ከቦታቸው በመልቀቃቸው ነበር። 

ጉባኤውን በስፍራው ሆኖ ከተከታተለው ዘጋቢያችን ዩሃንስ ገብረእግዚያብሔር ጋር የተደረገውን ቃለምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ። 

ዩሃንስ ገብረእግዚያብሔር

አዜብ ታደሰ