1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪካ እየተራባ ከሚሔደው የኮሮና ቫይረስ የሥርጭት ጠባይ አምልጣለች- የዓለም ጤና ድርጅት

ቅዳሜ፣ መስከረም 16 2013

እስከ አርብ መስከረም 15 ቀን ብቻ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በአፍሪካ 34 ሺሕ 706 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ባሰባሰበው መረጃ መሠረት 1 ሚሊዮን 439 ሺሕ 657 ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል። በአሜሪካ ብቻ 202 ሺሕ 827 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን ሲያጡ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል

https://p.dw.com/p/3j2Xs
Südafrika Coronavirus Handschuhausgabe
ምስል picture-alliance/AP Photo/T. Hadebe

አፍሪካ በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደታየው እየተራባ ከሚሔደው የኮሮና ቫይረስ የሥርጭት ጠባይ ማምለጧን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ። በአንድ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ የአኅጉሪቱ ሞቃታማ እና ርጥብ የአየር ጠባይ ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምቷል።

እስከ ትናንት አርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በአፍሪካ 34 ሺሕ 706 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ባሰባሰበው መረጃ መሠረት 1 ሚሊዮን 439 ሺሕ 657 ሰዎች እስከ ትናንት አርብ ድረስ በአፍሪካ በኮሮና ተይዘዋል። 

ይኸ ከሌሎች አኅጉሮች አኳያ አነስተኛ ነው። በልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ብቻ 203 ሺሕ 789 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን ሲያጡ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን የጆን ሖፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ቋት ያሳያል። 

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ከኮንጎ ብራዛቪል ባወጣው መግለጫ "በአፍሪካ የኮቪድ-19 ስርጭት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ባለፉት ሁለት ወራት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር" ብሏል።

"ባለፉት አራት ሳምንታት 77 ሺሕ 47 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን በቀደሙት አራት ሳምንታት 131 ሺሕ 647 ነበር" ያለው የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ኮሮና የበረታባቸውን አገራትም ዘርዝሯል።

WHO - Ebola-Lage im Kongo | Matshidiso Moeti
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ማትሺዲሶ ሞቲ ምስል picture-alliance/dpa/KEYSTONE/S. Di Nolfi

ወረርሽኙ በበረታባቸው አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ ባለፉት ሁለት ወራት በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።

ሮይተርስ ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ ብዛት ከተስፋፋባቸው 50 አገራት አንዷ ናት። በኢትዮጵያ እስከ አርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ 72 ሺሕ 173 ሰዎች በወረርሽኙ ሲያዙ 1 ሺሕ 155 ሰዎች ኮሮና ባስከተለው ሕመም ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ክፉኛ የተጎዳች የአፍሪካ አገር ነች። እስከ አርብ ድረስ በደቡብ አፍሪካ 667 ሺሕ 049 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ 16 ሺሕ 283 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ቦታ ተፋፍገው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ ሞቃታማው እና ርጥብ የአየር ጠባይ እንዲሁም ከአኅጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸው በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመቀነሱ አስተዋጽዖ ሊኖራቸው እንደሚችል ገልጿል።

ድርጅቱ በመግለጫው እንዳለው "ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በኮሮና ከተያዙ 91 በመቶው ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶው የሕመሙን ምልክት የማያሳዩ" ናቸው።

በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ በቀጣናው ያሉ መንግሥታት የወሰዷቸው የሕብረተሰብ ጤና እርምጃዎች ውጤት ነው ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ማትሺዲሶ ሞቲ ባለፈው ሐሙስ በኢንተርኔት በተደረገ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።