1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያንን ያስተባበረው የ#NoMore ንቅናቄ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18 2014

ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን በመቃወም #NoMore (በቃ) በሚል የጀመሩት ንቅናቄ ሌሎች አፍሪቃውያንንም ያነቃቃ መስሏል። በትዊተር «ፊውቹሪካል» በሚል ስማቸው ይታወቃሉ። በዋናነት ጸረ ዳግም ቅኝ አገዛዝን በመቃወም፤ በተለይም በኢትዮጵያውያን በተጀመረው ንቅናቄ ላይ ከዩጋንዳ በንቃት በመሳተፍ ይታወቃሉ። አነጋግረናቸዋል።

https://p.dw.com/p/43YbP
ምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

«ካልተቆጣጠርናችሁ ማለታቸውንም ትተውም ያከብሩናል»

ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን በመቃወም #NoMore (በቃ) በሚል በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የጀመሩት ንቅናቄ ሌሎች አፍሪቃውያንንም ያነቃቃ መስሏል። በትዊተር «ፊውቸሪካል» በሚል ስማቸው ይታወቃሉ። ዩጋንዳ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ የማኅበራዊ ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ናቸው። በዋናነት ጸረ ዳግም ቅኝ አገዛዝን በመቃወም፤ በተለይም በኢትዮጵያውያን በተጀመረው የ#NoMore ንቅናቄ ላይ በንቃት በመሳተፍ ይታወቃል። ሌሎች በርካታ አፍሪቃውያንም በዚህ ንቅናቄ ተሳታፊ በመሆን አፍሪቃ ውስጥ በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት በመቃወም ላይ ናቸው። 

ምዕራባውያን መንግሥታት በዋናነት ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭት የዘረጉትን ረዥም እጃቸውን ይሰብስቡ የሚለው የአፍሪቃውያን ጥሪ ተበራክቷል።  «ሠላም፤ ስሜ ስቲቨን ጎድዌይ ይባላል። ናይጀሪያዊ ነኝ። ኢትዮጵያ አፍሪቃን ሊቀይር የሚችል አፍሪቃ ላይ የተቃጣ ጦርነትን እየተዋጋች ነው። ከኢትዮጵያ ጎን እሰለፋለሁ። የበቃ ንቅናቄን አሁኑኑ ተቀላቀሉ።» 

የተለያዩ አፍሪቃውያን ተመሳሳይ መልእክታቸውን በቪዲዮ ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጸው እያስተጋቡ ነው። አጠር ያሉ የቪዲዮ መልእክቶቹንም በርካቶች እየተቀባበሉት ነው።  የ#NoMore ወይንም በቃ ንቅናቄ ተሳታፊ የሆነው ደቡብ ሱዳናዊ፦ «ሱዳን ኢትዮጵያ ወደምትኼድበት አቅጣጫ ሁሉ ትከተላለች» ብሏል። ወጣቷ ዩጋንዳዊት ሬቤካም፦ «የበቃ ንቅናቄን አሁኑኑ ተቀላቀሉ» ትላለች። ካሜሩናዊው ክሪስቶፈር በዴሰንም ተመሳሳይ መልእክት አለው።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Mana Vatsyayana/AFP/Getty Images

ባሳለፍነው ሳምንት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን «በቃ» የሚለውን መፈክር አንግበው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ25 በላይ ከተሞች ውስጥ ከጥግ እስከ ጥግ አደባባይ በመትመም ድምፃቸውን አሰምተዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ከሰሜን ደቡብ፤ ከምሥራቅ ምዕራብ አፍሪቃ ድረስ ንቅናቄው ተዳርሷል። የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት ከሚከታተሉ አፍሪቃውያን አንዱ የሆኑት እና በትዊተር «ፊውቸሪካል» በሚል ስም የሚታወቁት ዩጋንዳዊ ንቅናቄው አሁን ቢያስተጋባም ለዐሥርተ ዓመታት ግን ሲብላላ የከረመ ነበር ብለዋል።  

«ከኖ ሞር ንቅናቄ ጀርባ ያለውን አንደምታ ብሎም የሞራል ዋጋ ከተመለከትህ አፍሪቃውያን በአንድነት ተነስተው በቃ ለማለት ሲብላላ መቆየቱን ትረዳለህ። ስለዚህ ሲመስለኝ የኢትዮጵያው ግጭት ከተደበቅንበት ወጥተን በቃ ለኢምፔሪያሊዝም፤ እምቢ ለዳግም ቅኝ ግዛት፤ በአፍሪቃ የውጭ ጣልቃ ገብነት በቃን ለማለት ዕድሉን ሰጥቶናል ማለት እችላለሁ። የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ጉዳዩ ስለ አፍሪቃ ነው።»

ፊውቸሪካል ስለኢትዮጵያ በትጋት መልእክቶችን ከሚያስተጋቡ አፍሪቃውያን የፓን አፍሪቃ አቀንቃኞች አንዱ ነው። ሌሎች አፍሪቃውያንም ስለ አፍሪቃ ጉዳይ በጋራ ድምፅችንን እንድናሰማ ኢትዮጵያ መነቃቃቱን ፈጥራለች ብለውም ያምናሉ። 

«እኔ ዩጋንዳዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ጉዳዩ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ብቻ ቢሆን ኖሮ ይኼን ያህልም ከልቤ በትጋት አልገባበትም ነበር። ለንቅናቄው ያለኝ ቁርጠኝነት የመጣው ይህ ንቅናዌ ለአኅጉሪቱን ያለውን ጠቃሜታ ዋጋ ስለምሰጥ ነው። ወዲያው የተቀላቀልኩት እና ቁርጠኛ የሆንኩት በኢትዮጵያ ልምድ የአኅጉሪቱን ጥያቄ ለመመለስም እድሉን ይሰጠኛል በሚል ስለተገነዘብኩ ነው።»

ሌሎች አፍሪቃውያን ለንቅናቄው ድጋፋቸውን እየሰጡ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዩጋንዳውያኑ ለንቅናቄው ያላቸውን ድጋፍ አንድ ርምጃ ከፍ ወደማድረግም እየተሸጋገሩ  ነው። ፊውቸሪካል ከሌሎች ዩጋንዳውያን ጋር በመሆን በሀገራቸው የሚገኙ የመገናኛ አውታሮች ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እና ስለ ምዕራባውያን እንቅስቃሴ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መመካከር ጀምረዋል። ዩጋንዳዊው ፖለቲከኛ እና የፓን አፍሪቃ አቀንቃኝ ማቱዋ ጆብ ሪቻርድ #NoMore ከሐሽታግ መልእክት ወደ ንቅናቄ ከፍ ማለቱን ከዚህ ቀደም በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ጽሑፋቸው አስነብበዋል። «የኢትዮጵያ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም ተጋድሎ የዩጋንዳ ምዕራፍ የተሰኘ ቡድን ለመመስረት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሰናል»ም ብለዋል በትዊተር ጽሑፋቸው። 

«በቃ» ንቅናቄ ሐሳብን ዩጋንዳ ውስጥ እንዲያስተጋባ በቀዳሚነት አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ፊውቸሪካል እንደ ማቱዋ ጆብ ሪቻርድ ያሉ ሌሎች የፓን አፍሪቃ አቀንቃኞችን ያሰባሰቡት እሳቸው እንደሆኑ እና ሌሎችንም በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጠዋል። ሆኖም ይህ ምእራፍ ወደ ድርጅት ከፍ ቢል ቢሮክራሲው አላፈናፍን ሊለን ይችላል የሚልም ስጋት ገብቷቸዋል። በንቅናቄ ብቻ ተሰባስቦ መቀጠሉ ሳይሻል አይቀርም በሚልም እየተወያዩበት ነው። ድርጅትም ሆነ ንቅናቄ ዋነኛ ዓላማቸው ግን አፍሪቃውያንን ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

«ልክ እንደ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ሁሉ ዩጋንዳ ውስጥም ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ውዥንብር አለ። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ የሚነገረው በዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች ነው። ከፍተኛ የሆነ የቢቢሲ ትረካ ነው የሚደርሰው፤ በከፍተኛ ደረጃ በሲኤንኤን ነው የሚነገረው፤ በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጥለት በአልጀዚራ ትረካ በተቃኘ መልኩ ነው። በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያሉ የመገናኛ አውታሮች የውሸት ትርክትን እንድንገዛቸው ብቻ ሳይሆን ጸረ ኢትዮጵያ በዚያም ጸረ አፍሪቃ መሆናቸውን ለሁላችንም ግልጽ ሆኖልናል።»

እናም ያ በመሆኑ ዩጋንዳውያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ አፍሪቃውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ግጭት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይም ነን ብለዋል። ከሌሎች አፍሪቃውያን ጋር በመሰባሰብም የተሳሳተ ያሉትን ትረካ ለመቀልበስ እና የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን ለመታገል ንቅናቄው የፈጠረው መድረክ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። በሚኖሩበት ዩጋንዳ ኅብረተሰቡ በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት ግንዛቤው አናሳ  የሚባልም ነው ብለዋል። በዋናነት የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ግን ጥሩ ግንዛቤ አላቸው እዚያ ላይ ይበልጥ ትኩረት ሊደረግ ይገባልም ሲሉ አክለዋል። 

አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ራሳቸውን የ«ፓን አፍሪቃ» አቀንቃኝ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረታቸውም እየተሳካ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አብነትም የፓን አፍሪቃ ንቅናቄ የዩጋንዳ ምዕራፍ ሊቀመንበር ማይክ ሙሉካህ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን ጠቁመዋል። በአንድ ወቅት ለዐሥርተ ዓመታት የዩጋንዳ ምክር ቤት አባል እና ለ6 ዓመታት የጤና ሚንስትር የነበሩት ማይክ ሙሉካህ «ኢትዮጵያ በዳግም ቅኝ ገዢዎች እየተረበሸች ነው» ሲሉ ጽፈዋል። «አፍሪቃ እና ዓለም የአፍሪቃ ኅብረት ዋና መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ እንድትረበሽ መፍቀድ የለባቸውም» ሲሉም ጠንከር ያለ መልእክት አስተላልፈዋል። 

«በዕውነቱ ይኼ መጻፉን ስመለከት አዎ የማግባባት ሥራችን ግቡን መትቷል አልኩኝ ለራሴ። ሰዎችም ሚናቸውን እንዲለዩ አስገድዷል። ምክንያቱም ይኼ ታሪካዊ ጦርነት ነው። ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ ናት። እናም ነገሩ ዝም ብለህ መሀል ላይ የምትቆምበት አይደለም።»

መሰል የማነቃቃት ሥራ በሌሎች የአፍሪቃ ክፍሎችም ሲስፋፋ የምዕራባውያን መጠን ያለፈ ጣልቃ ገብነት ገደብ ይበጅለታል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች በተናበበ እና በተቀናጀ መልኩ ስለ ኢትዮጵያ ብሎም ስለአፍሪቃ የሚያስተጋቡትን መመከት የሚቻለው ኅብረተሰቡን በመገናኛ አውታር በማንቃት ነው የሚል ጠንካራ አመለካከትም አላቸው።

ዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች ለአንድ ወገን አድልተው የሚያሰራጩትን መልእክት ለመመከት ከመጣርም አልፎ የራሳችን አፍሪቃዊ ትረካ እንዲኖረን ለመሥራት እንደ «በቃ» ያሉ ንቅናቄዎች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው ሲሉም አክለዋል። መሰል ንቅናቄዎች በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም መንጸባረቁን ጠቁመዋል። ሰሞኑን የቡርኪናፋሶ ነዋሪዎች የሀገሪቱ የቀድሞው ቅኝ ገዢ ከነበረችው ፈረንሳይ ወታደሮች ጋር የገቡት ግብግብ እና ተቃውሞ «በቃ» በሚል የተስተጋባ ነበር። ዩጋንዳዊው ፊውቸሪካል ለአፍሪቃ ተምሳሌት የሆነ ቀደምት የነጻነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ አሸነፈች ማለት መላው አፍሪቃ አሸነፈ ማለት ነው ሲሉም ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ያላትን ጉልህ ሚና አንጸባርቀዋል። 

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

«ኢትዮጵያውያን ለቆሙበት ዓላማ እስከጸኑ ድረስ፤ እኛም በሒደት የመተማመን መንፈሳችን ይጎለብታል። ይህ ጦርነት፣ ይህ ንቅናቄ፣ አፍሪቃ ከምዕራቡ ጋር ያላትን ግንኙነት እና አጠቃላይ ትረካ ይቀይረዋል። ካልተቆጣጠርናችሁ ማለታቸውንም ትተውም ያከብሩናል።»

«በቃ» ንቅናቄ ኢትዮጵያ የምትከበርበት ቢዚያም መላው አፍሪቃ ክብር የሚያገኝበት ነው ብለዋል ዩጋንዳዊው የፓን አፍሪቃ አቀንቃኝ ሐሳባቸው ሲያጠቃልሉ። ለዚያም እንደሌሎቹ አፍሪቃውያን በቁርጠኝነት መረጃ በመስጠት መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ