አፍሪቃ በጎርጎሪዮሳዊው 2019
ባገባደድነው በ2019 ኮንጎ ኤቦላንና በተመድ ላይ የተነሳን ተቃውሞ ስትታገል ነበር፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተቀብለዋል። የውኃ መጥለቅለቅ ምሥራቅ አፍሪቃን ጎድቷል። በተለያዩ ሃገራትም ምርጫዎች ተካሂደዋል። ይህ የፎቶ ዘገባ ከሞላ ጎደል በ2019 አፍሪቃን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስቃኘናል።
ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ሰላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት የኖቤል የሰላም ሽልማት የተበረከተላቸው በመገባደድ ላይ ባለው በ2019 ነው። ዐቢይ ሥልጣን እንደያዙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ፈተዋል። ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባትን የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ለማረጋጋት እየሠሩ ነው። በዚያም ላይ የምጣኔ ሃብት መሻሻያዎችን በማካሄድ ላይ ናቸው። ከካቢኔያቸው ግማሾቹም ሴቶች ናቸው።
ፌሊክስ ቺሴኬዲ አዲሱ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት
በጎርጎሮሳዊው 2019 መጀመሪያ ላይ ነበር አዲሱ የኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቺሴኪዲ ሥልጣን የያዙት። ለሥልጣን ያበቃቸው የተመሰቃቀለው ምርጫ ውጤት አወዛግቧል። ቺሴኬዲ መሠረታዊ ለውጦች ለማምጣት ቃል ገብተው ነበር፤ አማጽያንን ለመውጋትም ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ከአንድ ዓመት በኋላ የለውጡ ተስፋ ደብዝዟል። ቺሴኬዲ ሀገሪቱን ለ18 ዓመታት የመሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የጆሴፍ ካቢላ አሻንጉሊት ነው የሚባሉት።
የቡሃሪ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን
በ2019 ነበር ሙሃማዱ ቡሃሪ ከ3 ሚሊዮን በላይ ድምጽ አግኝተው ነው ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ያሸነፉት። ቡሃሪ በተለይ ድህነት እና ጸጥታ ላይ አትኩረዋል። ጸጥታ አንዱ አፋጣኝ ትኩረታቸው እንዲሆን ያስገደደው አሸባሪው ሚሊሽያ ቦኮ ሃራም በሰሜን ናይጀሪያ የሚፈጽመው ጥቃት መቀጠሉ ነው።በናይጀሪያ በአርብቶ አደሮች እና በገበሬዎች መካከል በሚነሱ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ። ማሊ እና ኒዠር ውስጥም ተመሳሳይ ችግር አለ።
ኢዳይ እና ኬኔት ማዕበል በምሥራቅ አፍሪቃ
በጎርጎሮሳዊው 2019 ምሥራቅ አፍሪቃ በሁለት ማዕበሎች ተመታለች። ማዳጋስካር፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባብዌ፣ ማላዊ፣ ታንዛንያ እና ኮሞሮስ በመጋቢት እና በሚያዚያ የተከሰቱት የነዚሁ ማዕበሎች ሰለባዎች ነበሩ። በአደጋው የ1400 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በርካቶችም የደረሱበት አልታወቀም። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መኖሪያቸውን አጥተዋል። ማዕበሉ ባጠቃቸው ሃገራት ደግሞ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል።
የሱዳን አብዮት
የሱዳንዋ አላ ሳለህ የሱዳኑ አብዮት ተምሳሌት ናት። የምግብ ዋጋ መናር እና የኤኮኖሚ ማሽቆልቆል ነበር በመላው ሱዳን ተቃውሞ ያስነሳው። በአመጹ ሰበብ ለ30 ዓመታት ሱዳንን የመሩት ፕሬዝዳንት ኦመር አል በሽር ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ከሥልጣን ተወገዱ። ወታደሩ እና ሲቪሎች የመሰረቱት የሽግግር መንግሥት ለምርጫው መንገዱን እየጠረገ ነው። በሱዳኑ ተቃውሞና አመጽ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።
የአፍሪቃ ዋንጫ አስገራሚ ክስተቶች
የማዳጋስካር ቡድን በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ያልተጠበቀ ውጤት ማምጣት ከ2019 አስገራሚ ጉዳዮች መካከል ነው። ቡድኑ ከናይጀሪያ እና ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ተፋልሞ ሩብ ፍፃሜ መድረሱ አጀብ ያሰኘ ነበር። አልጀሪያ እና ሴኔጋል ለፍጻሜ በደረሱበት በዚህ ውድድር ሴኔጋል ዋንጫውን ወስዷል። ካሜሩን ልታስተናግድ የነበረው ይህ ውድድር በሀገሪቱ ፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በግብፅ እንዲካሄድ ተደርጓል።
ኮንጎን ያናወጠው ኤቦላ
ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2018 አንስቶ በሀገሪቱ የተከሰተውን ከፍተኛ የኤቦላ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ስትታገል ቆይታለች። በሀገሪቱ በኤቦላ ከተያዙት ከ3300 በላይ ሰዎች 2/3ው ሕይወታቸው አልፏል። ዩጋንዳ ከኮንጎ ጋር በሚያዋስናት በካሴሴ ቀበሌ ተከስቶ የነበረው የኤቦላ ወረርሽኝ ማብቃቱን በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2019 አረጋግጣለች። በሙከራ ላይ ያለው የኤቦላ ክትባት ውጤት እያሳየ ነው። በኤቦላ ለተያዙት ሕክምና የሚሰጠው መድኃኒትም ተስፋ ሰጭ ይመስላል።
አወዛጋቢው የሞዛምቢክ ምርጫ
በ2019 በሞዛምቢክ በተካሄደው ምርጫ ፕሬዝዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ በአብላጫ ድምጽ ዳግም አሸንፈዋል። ውጤቱን እንደማይቀበል ያሳወቀው ተቃዋሚው ፓርቲ ሬናሞ፣ ኒዩሲና ፓርቲያቸው ከፍተኛ የምርጫ ማጭበርበር አካሂደዋል ሲል ከሷል። ገዥው ፓርቲ ፍሬሊሞ እና ሬናሞ እስከ ጎርጎሮሳዊው 1992 ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ደም አፋሳሽ ጦርነት አካሂደዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች በነሐሴ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም አሁንም በሀገሪቱ ውጥረት እንደሰፈነ ነው።
አዲሷ የኢትዮጵያ ክልል ሲዳማ
በዚህ ዓመት በኅዳር በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ 98.5 በመቶ መራጮች በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር የነበረው የሲዳማ ዞን፣ ክልል እንሁን ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ሕዝቡ በዚህ ውሳኔ የተፈጥሮ ሐብቱን የመጠቀም፣ የፖለቲካ መብቱን የማስከበር እና ባህላዊ መለያውን የማጠናከር ተስፋ ሰንቋል። ሌሎች በደቡብ ክልል የሚገኙ 10 ዞኖችም የክልል እንሁን ጥያቄ አቅርበዋል።
አዲሱ የጊኒቢሳው ፕሬዝዳንት ማን ይሆናል?
የጊኒቢሳው ምርጫ ውጤት ገና አልለየለትም ።ሆኖም ሥልጣን ላይ ያሉት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆሴ ማርዮ ቫዝ ተሸንፈዋል። በጎርጎሮሳዊው ታኅሣሥ 29፣ 2019 የመለያ ምርጫ ይካሄዳል። የምርጫ ፉክክሩም በተወዳጁ በዶሚኒጎ ሲሞስ ፔሬይራ እና ኡማሩ ሲሶኮ ኤምባሎ መካከል ነው የሚሆነው። በፕሬዝዳንት ቫዝ እና በሀገሪቱ ፓርላማ መካከል ሲካሄድ የቆየው ውዝግብ የመንግሥት ተቋማትን አሽመድምዷል፣ የኤኮኖሚ ቀውስን አስከትሏል። አዲሱ ፕሬዝዳንት በ2020 እነዚህን ችግሮች ማስወገድ ይኖርባቸዋል።
ጥቃት ኮንጎ በሚገኘው የተመድ የሰላም ተልዕኮ ላይ
ተቃዋሚ ሰልፈኞች ባለፈው ኅዳር በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዋ ቤኒ ከተማ የሚገኘውን የተመድ ካምፕ ጥሰው ሲገቡ የከተማዋን ምክር ቤት ደግሞ አቃጥለዋል። ሰልፈኞቹ ይህን ያደረጉት የተመድ ተልዕኮ ከአማጽያን ጥቃት ፈጽሞ አልተከላከለልንም በማለት ነው። «የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች» የሚባለው ጽንፈኛው ሚሊሽያ እስካሁን በአካባቢው በርካታ ሰዎችን ገድሏል፤ አግቷል። የቤኒው ትግል ቀጥሏል።
አመጽ በዚምባብዌ
በዚምባብዌ ጎርጎሪዮሳዊው 2019 የተጀመረው እና የሚያበቃው በተቃውሞ ነው። የዋጋ ግሽበቱ ከ400 በመቶ በላይ ደርሷል። በግሮሰሪዎች እና በሱቆች ውስጥ የምግብ እጥረት በመኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጥተው ምሬታቸውን ገልጸዋል። የደሞዝ ጭማሪ እና የተሻለ የሥራ ሁኔታ ጥያቄ ካቀረቡ የሀገሪቱ 1550 የመንግሥት ሠራተኛ ሐኪሞች 211 ከሥራ ተባረዋል። እነርሱ እንደሚሉት ከ200 ዶላር የሚያነስው የወር ደሞዛቸው ኑሯቸውን ለመግፋት በቂ አይደለም። ኂሩት መለሰ/ ሸዋዬ ለገሠ