1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2011

የዩናይትድ ስቴትስ፣የተባበሩት መንግስታት፣ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ባለፉት 27 ዓመታት ያደረጉት ዉጊያ የአፍሪቃ ቀንዷን ሐገር ሠላም ማስከበር አልቻለም።የአፍሪቃ መሪዎች ግን ጦራቸዉን እያዋጉ ኪጋሊ፤አዲስ አበባና ዛሬ ደግሞ ኒያሚ ላይ «የጠመንጃዉን ላንቃ ለመዝጋት» ፣«አፍሪቃን በንግድ ለማስተሳሰር»--- ይላሉ።ካንጀት ይሆን?

https://p.dw.com/p/3LfIS
African Development Week
ምስል DW/Getachew Tedla

የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ፣አጀንዳ 2063፣ የአሸባብ የቀድሞ አባላት

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ኒያሚ-ኒዠር የሚደረገዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከሚነጋገርባቸዉ ርዕሶች ዋናዉ አጀንዳ 2063 የተሰኘዉ የሕብረቱ ትልቅ ዕቅድ ነዉ።የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት፣ የትልቁ ዕቅድ ዋና ዋና ነጥቦችን ምንነት፣ ገቢራዊ ከመሆን-አለመናቸዉ ጋር አሳብጥሮ ይቃኛል።የአሸባብ የቀድሞ ታጣቂዎች አስተያየትም የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን አካል ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

 

ኒያሚ-ኒዠር የተሰየመዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለ3 ቀናት የሚመክርበት «አጀንዳ 2063» የመሠረተ ልማት አዉታርግንባታን፣ትምሕርትን፣ ሳይንስን፣ቴክኖሎጂን፣ ባሕልንና ሠላምን ማስረፅን የሚመለከቱ 14 ዋና ዋና ዕቅዶች አሉት።

ከእንግዲሕ በሚቆጠረዉ 44 ዓመታት ዉስጥ ገቢር ይሆናሉ የተባሉት ዕቅዶች ከተሳኩ፣ የዕቅዶቹ አስረቃቂ -አፅዳቂዎች እንደሚሉት «የምንመኛት አፍሪቃ ትገነባለች።»ይሳካ ይሆን? ላሁኑ «አያያዙን አይተሕ….» ዓይነ ነዉ መልሱ።የዶቸ ቬለዋ ሲልያ ካታሪና ፍሮሕሊሽ፣ «አያያዙን ለማየት» በቅርቡ ገቢር ሊሆንያለመዉን ዕቅድ ቁጥር አምስትን አብነት አድርጋዋለች።

ዕቅድ ቁጥር አምስት ሠላምን ለማስፈ።ሠላም ለማስፋን እስከ 2020 (ዘመኑ በሙሉ  እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ድረስ የጦር መሳሪያ ግጭቶች ይቆማሉ።የጠመንጃ ልሳኖች ይዘጋሉ-በዕቅዱ አገላለፅ።2020 ሊብት መንፈቅ ቀረዉ።ከሰሜን ሊቢያ እስከ እስከ ደቡብ ምሥራቅ አፍሪቃ ኮንጎ፣ ከምሥራቅ  አፍሪቃ ሶማሊያ ወይም ደቡብ ሱዳን እስከ ምዕራብ ማሊ ያሉ መንግሥታት፣አማፂያን፣ፅንፈኞች «የሚነጋገሩት» ግን በጠመንጃ ቋንቋ ነዉ።የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ደሱ መረሳ «ዕቅዱ አልያዘም» ባይናቸዉ።

                                            

«ዕቅዱ በ2020 ተኩስ እንዲቆም ነበር።2020 እየተቃረብን ነዉ።ጠመንጃዎቹም አሁንም እንደተኮሱ ነዉ»

ኮንጎዊዉ የፖለቲካ አዋቂ ዴዜሬ አሶግባቪም «ሠላም ማስፈን ለሌሎቹ ዕቅዶች ሁሉ መሠረት ነዉ።» ይላሉ፣  «የጠመንጃዉን አፍ ሥለ መዝጋት ያልተለፈፈ ቃል፣ ያልተደረገ ስብሰባ፣ ዉይይት፣ ዉሳኔም የለም።» ቀጠሉ  አሶግባቪ።

                                        

Angola Eisenbahnlinie bei Benguela
ምስል picture-alliance/dpa/K. Ludbrook

«በአሐጉሪቱ የጠመንጃዉን ላንቃ ለማዘጋት ብዙ ተወርቷል።ብዙ ስብሰባ ተደርጓል።ብዙ ዉሳኔዎች ፀድቀዋል።ያሁኑ የአፍሪቃ ሁኔታ ሲታይን ግን ጠመንጃዉ አፉን አልዘጋም።እንዲያዉም በተቃራኒዉ ብዙ የጦር መሳሪያ ግጭቶችና ችግሮች ጎልተዉ ይታያሉ።ሠላም ማስፈን ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ይጠይቃል።»

ጠመንጃዉ ይጮኻል።ሕይወትም ይጠፋል፣ ዑደቱ ቀጥሏል።ዕቅዱም።የአፍሪቃ አሐጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA በምሕፃሩ) ምስረታ ዉል ሌላዉ።ዉሉን ባፀደቁት 24 የአፍሪቃ ሐገራት ዘንድ ስምምነቱ ካለፈዉ ግንቦት ማብቂያ ጀምሮ ገቢር ሆኗል። ግዙፏ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ናጄሪያ ዛሬ በተጀመረዉ ጉባኤ ላይ ሰነዱን ለመፈረም ቃል ገብታለች።ቃሉ ገቢር ከሆነ ለአፍሪቃ ሕብረት በጠቃላይ ላሁኑ ጉባኤ በተለይ  ታላቅ ስኬት ነዉ።አሶግባቪም ከዕቅዶቹ ሁሉ የተሰካዉ ይሉታል።

«ይሕ ጉባኤ፣የአፍሪቃን ነፃ የንግድ ቀጠና ሥለማወጅ ነዉ።ይሕ ማለት በእኔ እምነት በአጀንዳ 2063 የተጠቀሰዉን የአሐጉሪቱን የንግድ ዕቅድ ገቢር ለማድረግ አንድ ታላቅ እመርታ ነዉ።የአፍሪቃ አሐጉር ነፃ የንግድ ቀጠና ሙሉ በሙሉ ገቢር ሆነ የአሐጉሪቱ መፃኤ ዕዉነታ ሙሉ በሙሉ ይለወጣል።»

የሁሉም የአፍሪቃ ሐገራት የንግድ ቀጠናዉን ሰነድ ካፀደቁት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያገላብጥ፣ 1.5 ቢሊዮን ሸማች የሚያሳትፍ ከዓለም ትልቁን የንግድ ቀጠና መሰረቱ ማለት ነዉ።እና አሶግባቪ እንዳሉት የአፍሪቃ ዕዉነት በርግጥ ይለወጣል።ግን እንዴት?

3 ቢሊዮኑ ዶላር እንዲገላበጥ፣ ሕዝቡ አምርቶ እንዲሸጥ፣ሸጦ እንዲሸምት ካንዱ ሐገር ወደሌላዉ በቻለና በፈለገዉ ጊዜ መንቀሳቀስ፣ምርት ሸቀጦቹን በፍጥነት መላክና መቀበል መቻል አለበት።የዕቅዱ አስረቃቂ አፅዳቂዎች ለዚሕም ብልሐት አብጅተዉለታል።

አፍሪቃ አቀፍ ፓስፖርት ማዘጋጀት አንዱ ነዉ።ሁለተኛዉ አፍሪቃዊዉ ሁሉ ያለ ቪዛ ካንዱ ሐገር ወደ ሌላዉ በነፃነት መግባት፣ መዉጣት፣ በየደረሰበት መስራት፣መኖር እንዲችል መፍቀድ ነዉ።

«አሐጉራዊ ወይም ብሔራዊ ፓስፖርት መኖር አለመኖር ብዙም ትርጉም የለዉም።ዋናዉ ነገር የአሐጉሪቱ ነፃ የንግድ ቀጠና ገቢር ከሆነ ሰዎች ከቦታ፣ ቦታ ከአንዱ ሐገር ወደ ሌላዉ፣ ከየሐገሮቻቸዉ ድንበሮች አልፈዉ በመላዉ አፍሪቃ እንደልባቸዉ መንቀሳቀስ መቻል አለባቸዉ።»ይላሉ ደሱ መረሳ

አምና መጋቢት ኪጋሊ-ሩዋንዳ በተደረገዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ አፍሪቃዉያን ያለ ቢዛ አንዱ ሐገር ወደሌላዉ እንዲዘዋወሩ የሚፈቅደዉን ሰነድ 27 ሐገራት ፈርመዋል።ገቢራዊነቱ ግን እስካሁን ያዉ ዝም-ዝም እንደተባለ ነዉ።ዝምታዉ ይከብዳል ተስፋ አስቆራጭ ግን አይደለም።

በጣም ከባዱ የመገናኛ (ትራንስፖርት) ጉዳይ ነዉ።ሸቀጥና ሰዎችን ከስፍራ ሥፍራ ለማመለስ የአፍሪቃ ሐገራት እስካሁን ያሏቸዉ የዓየር፣የየብስ እና የባሕር መስመሮች ለሁሉም ክፍት እንዲሆኑ ተጨማሪም እንዲገነቡ አጀንዳ 2063 ይጠይቃል።

የአየር ትራንስፖርትን በተመለከተ እስካሁን ካንዱ የአፍሪቃ ሐገር ወደ ሌላዉ ለመብረር የቅኝ ገዢዎችን መስመር ተከትሎ በአዉሮጳ ሐገራት በኩል የሚደረገዉ ጥምዝ ጉዞ እንዲቀር ተወስኗል።ሁሉም የአፍሪቃ አዉሮፕላን ማረፊያዎች የሁሉንም አየር መንገዶች አዉሮፕላኖች እንዲያስተናግዱ የሚጠይቅ ሰነድም 23 መንግሥታት አምና መጋቢት ኪጋሊ ላይ ፈርመዉ ነበር።

Afrikanischer Reisepass
ምስል picture-alliance/Godong

ከፊርማዉ በኋላ የተባለ ወይም የተደረገ ነገር ካለ ከባይ አድራጊዉ ዉጪ የሚያዉቀዉ የለም።አጀንዳ 2063፣ 54ቱን የአፍሪቃ ሐገራት የሚያገናኛ የባቡር ሐዲድ መረብ ለመዘርጋት አቅዷል።12 ሺሕ ኪሎ ሜትር ተጨማሪ ሐዲድ ይዘረጋል።አሶግባቪ «የማይቻል የለም» ይላሉ «ግን አንድ ነገር ይጠይቃል።» ጠንካራ አመራር።

                                

«እነዚሕን መሰል ትልሞች በሌሎች አሐጉራት ተግባራዊ ሆነዋል። አዉሮጳ ላይ ገቢር ሆነዋል።አሜሪካ፣በሌሎችም የአለም ክፍሎች ሥራ ላይ ዉለዋል።አፍሪቃም ገቢር የማይሆኑበት ምክንያት የለም።የሚስፈልገዉ ጠንካራ አመራር ነዉ።ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነዉ።አሐጉሪቱ ጠንካራ መሪዎች ካገኘች፣ አዎ! የአጀንዳ 2063 ዕቅዶች ገቢር ይሆናሉ።»

2063 ሩቅ ነዉ።ብቻ የአሶግባቪ ምኞት ዕዉን እንዲሆን እየተመኘን ሁለተኛ ርዕሳችንን እንቃኝ።ሁለተኛዉ ርዕሠ ከሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ የከዱ የቀድሞ ጀሌዎቹ አሉት የተባለዉ ነዉ።

በሶማሊ ላንድ የዶቸ ቬለዋ ዘጋቢ ሜላኒ ኩራ ዳባል እንደምትለዉ ደቡባዊ ሶማሊያ ጁባላንድ ዉስጥ 86 የቀድሞ አልሸባብ ተዋጊዎች የሠፈሩበትን ማቆያ ጣቢያ ጎብታለች።አብዛኞቹ በ24 እና በ29 ዐመታት መካከል የሚገኝ ወጣቶች ናቸዉ።ሁሉም ወንዶች።ሁለቱን አነጋግራቻዋለች።ዘጋቢዋ እንደምትለዉ የወጣቶቹን ትክክለኛ ስምና ያሉበትን ሥፍራ፣ምስላቸዉንም ለደህንነታቸዉ ስትል ይፋ ማድረጉን አልፈለገችም።ለመጀመሪያዉ ኢሳ፣ ለሁለተኛዉ አሕመድ የሚል ቅፅል  ስም አዉጥታላቸዋለች።

«ሰዎች መጀመሪያ አሸባብን የተቀላቀሉት በኃይማኖት ምክንያት ነበር።አሸባብዎች ኃይማኖትን ለማስከበር መቆማቸዉን ይናገሩ ነበር።ይሕ ግን ማታለያ ነዉ።የዋሕ ሰዎችን ያለምንም ምክንያት ይገድላሉ»

ኢሳ ነዉ እንዲሕ ባዩ።20 ዓመቱ ነዉ።አሕመድ ይቀጥላል።24 ዓመቱ ነዉ።«በሚያደርሱት ጥቃት ሙስሊሞችን ጭምር ይገድላሉ።ወገኖቼ ሲገደሉ ሳይ፣ለመሸሽ ወሰንኩ።»

አብዛኞቹ የአሸባብ የቀድሞ ተዋጊዎች በሐገሪቱ ገጠራማና ደሐ አካባቢ ተወልደዉ ያደጉ ናቸዉ።አሸባብን የሚቀየጡትም እነ አሕመድ እንደሚሉት በኃይማኖት ብቻ ሳይሆን ገንዘብ እናገኛለን በሚል ተስፋ ጭምር ነዉ።አሕመድ እንደ አብዛኞቹ ብጤዎቹ በሕይወቱ ሁለተኛ እድሉን ለመሞከር በእደ ጥበብ እየሰለጠ ነዉ።«በማሕበረሰቡ ዉስጥ እንዴት እንደምኖር አላዉቅም ነበር።እዚሕ ግን እራሴን እንዴት መደገፍ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።»

አሕመድ ነዉ እንዲሕ ባዩ።እነ አሕመድ ከሚገኙበት አካባቢ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር (AMISOM) እና የአሸባብ ሸማቂዎች አሁን ይዋጋሉ።ኢትዮጵያዊዉ የተዋጊዉ ጦር አዛዥ (ማዕረጋቸዉ አልተጠቀሰም) ብርሐኑ ጥላሁን በርሔ እንደሚሉት ጦራቸዉ በርካታ መንደሮችን ከአሸባብ እጅ ማርኳል።አዛዡ «ነፃ አወጣን» ነዉ የሚሉት።«ባለፉት ሁለትና ሶስት ወራት ብዙ ተዋግተናል።በርካታ አካባቢዎችንም ከአሸባብ ነፃ አዉጥተናል።ተጨማሪ አካባቢዎችን ከአሸባብ ነፃ አዉጥተን ለሶማሊያ መንግስት ጦር የምንስረክብበትን ስልትም እያረቀቅን ነዉ።»

Kindersoldat Somalia Mogadischu
ምስል picture-alliance/dpa

ኢሳና አሕመድ ከእንግዲሕ ካሸባብ ወጥመድ አንገባም ባይ ናቸዉ።እራሳቸዉን ለመርዳት፣ ሐገርና ሕዝባቸዉን ለመካስ እንደሚጥሩም ይናገራሉ።

የሶማሊያ ጠንካራ መንግስት ከፈረሰ ዘንድሮ 27 ዓመቱ።የዩናይትድ ስቴትስ፣የተባበሩት መንግስታት፣ የኢትዮጵያ፣ አሁን ደግሞ የአፍሪቃ ጦር ባለፉት 27 ዓመታት ያደረጉት ዉጊያ የአፍሪቃ ቀንዷን ሐገር ሠላም ማስከበር አልቻለም።የአፍሪቃ መሪዎች ግን ሶማሊያ ጦራቸዉን እያዋጉ ኪጋሊ፤አዲስ አበባና ዛሬ ደግሞ ኒያሚ ላይ «የጠመንጃዉን ላንቃ ለመዝጋት» ፣«አፍሪቃን በንግድ ለማስተሳሰር» ፣ «ሕዝቧን ለማበልፀግ፣ አጀንዳ 2063» ይላሉ።ካንጀት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ